ኢዮብ 38:1-41
38 ከዚያም ይሖዋ ከአውሎ ነፋስ ውስጥ ለኢዮብ መለሰለት፦+
2 “ሐሳቤን የሚሰውርናያለእውቀት የሚናገር ይህ ማን ነው?+
3 እስቲ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ንገረኝ።
4 ምድርን በመሠረትኩ ጊዜ አንተ የት ነበርክ?+
ማስተዋል አለኝ የምትል ከሆነ ንገረኝ።
5 የምታውቅ ከሆነ፣ መለኪያዎቿን የወሰነ፣ወይስ መለኪያ ገመድ በላይዋ ላይ የዘረጋ ማን ነው?
6 የምድር ምሰሶዎች የተተከሉት ምን ላይ ነው?የማዕዘኗን ድንጋይ ያኖረስ ማን ነው?+
7 አጥቢያ ከዋክብት+ በአንድነት እልል ሲሉ፣የአምላክም ልጆች ሁሉ*+ በደስታ ሲጮኹ አንተ የት ነበርክ?
8 ባሕሩ ከማህፀን አፈትልኮ በወጣ ጊዜ፣በር የዘጋበት ማን ነው?+
9 ደመና ባለበስኩት ጊዜ፣በድቅድቅ ጨለማም በጠቀለልኩት ጊዜ፣
10 በላዩም ድንበሬን በወሰንኩ ጊዜ፣መቀርቀሪያዎችና በሮች ባደረግኩለት ጊዜ፣+
11 ደግሞም ‘እስከዚህ ድረስ መምጣት ትችላለህ፤ ከዚህ ግን አታልፍም፤የኩሩው ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ ባልኩ ጊዜ+ አንተ የት ነበርክ?
12 ለመሆኑ ንጋትን አዘህ ታውቃለህ?ወይስ ጎህ ስፍራውን እንዲያውቅ አድርገሃል?+
13 የማለዳ ብርሃን ወደ ምድር ዳርቻዎች እንዲሄድ፣ክፉዎችንም ከላይዋ እንዲያራግፍ ያዘዝከው አንተ ነህ?+
14 ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ትለወጣለች፤ገጽታዎቿም እንደሚያምር ልብስ ጎልተው ይታያሉ።
15 የክፉዎች ብርሃን ግን ከእነሱ ተወስዷል፤ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል።
16 ወደ ባሕሩ ምንጮች ወርደሃል?ወይስ ጥልቁን ውኃ መርምረሃል?+
17 የሞት በሮች+ ተገልጠውልሃል?የድቅድቅ ጨለማንስ* በሮች አይተሃል?+
18 ምድር ምን ያህል ሰፊ እንደሆነች አስተውለሃል?+
ይህን ሁሉ የምታውቅ ከሆነ ተናገር።
19 ብርሃን የሚኖረው በየት አቅጣጫ ነው?+
የጨለማ ስፍራስ የት ነው?
20 ወደ ክልሉ ልትወስደው ትችላለህ?ወደ ቤቱስ የሚወስደውን ጎዳና ታውቃለህ?
21 በዚያን ጊዜ ተወልደህ ስለነበር፣ዕድሜህም ትልቅ ስለሆነ* ይህን ሳታውቅ አትቀርም!
22 አመዳዩ ወደተከማቸበት መጋዘን ገብተሃል?+የበረዶውንስ ግምጃ ቤት አይተሃል?+
23 ይህም ለመከራ ጊዜ፣ለውጊያና ለጦርነት ቀን ያስቀመጥኩት ነው።+
24 ብርሃን* የሚሰራጨው ከየት አቅጣጫ ነው?የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ የሚነፍሰው ከየት ነው?+
25 ለዶፍ መውረጃን፣ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመናም መንገድን ያዘጋጀ ማን ነው?+
26 አንድም ሰው በሌለበት ቦታ፣ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ የሚያዘንበው፣+
27 የወደመውን ጠፍ መሬት የሚያረካው፣ሣርንም የሚያበቅለው ማን ነው?+
28 ዝናብ አባት አለው?+ጠልንስ የወለደው ማን ነው?+
29 በረዶ የሚወጣው ከማን ማህፀን ነው?የሰማዩንስ አመዳይ የወለደው ማን ነው?+
30 ውኃዎች በድንጋይ የተሸፈኑ ያህል እንዲሆኑ፣የጥልቁ ውኃም ገጽ ግግር በረዶ እንዲሆን የሚያደርገው ማን ነው?+
31 የኪማ ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልታስር፣ወይስ የከሲል ኅብረ ከዋክብትን* ገመድ ልትፈታ ትችላለህ?+
32 ኅብረ ከዋክብትን* በወቅቱ ልታወጣ፣ወይስ የአሽ ኅብረ ከዋክብትን* ከነልጆቹ ልትመራ ትችላለህ?
33 ሰማያት የሚመሩባቸውን ሕጎች ታውቃለህ?+ወይስ የሰማያትን* ሕጎች በምድር ላይ ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ?
34 ጎርፍ ይሸፍንህ ዘንድ፣ድምፅህን ወደ ደመናት ማንሳት ትችላለህ?+
35 የመብረቅ ብልጭታዎችን መላክ ትችላለህ?
እነሱስ አንተ ጋ ቀርበው ‘ይኸው መጥተናል!’ ይሉሃል?
36 በደመናት ውስጥ* ጥበብ ያኖረው፣+በሰማይ ለሚከናወነውስ ክስተት* ማስተዋልን የሰጠው ማን ነው?+
37 ደመናትን ለመቁጠር የሚያስችል ጥበብ ያለው ማን ነው?ወይስ የሰማይን የውኃ ማሰሮዎች ሊደፋ የሚችል ማን ነው?+
38 አፈሩ ቦክቶ እንዲጋገር፣የምድር ጓሎችም እንዲጣበቁ ሊያደርግ የሚችል ማን ነው?
39 ለአንበሳ አድነህ ግዳይ ልታመጣለት፣ወይስ የተራቡ የአንበሳ ግልገሎችን ልታጠግብ ትችላለህ?+
40 እነሱ በዋሻቸው ውስጥ አድፍጠው፣ወይም በጎሬአቸው አድብተው ሳለ ይህን ልታደርግ ትችላለህ?
41 ጫጩቶቿ ወደ አምላክ ሲጮኹ፣የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፣ለቁራ መብል የሚያዘጋጅ ማን ነው?+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።
^ ወይም “የሞት ጥላንስ።”
^ ቃል በቃል “ቀኖችህ (ብዙ ስለሆኑ)።”
^ “መብረቅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ በቶረስ ኅብረ ከዋክብት የታቀፉ ፐልያዲስ የሚባሉ ከዋክብት ሊሆኑ ይችላሉ።
^ የኦርዮን ኅብረ ከዋክብት ሊሆን ይችላል።
^ የታላቁ ድብ ኅብረ ከዋክብት (ኧርሳ ሜጀር) ሊሆን ይችላል።
^ “የእሱን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “በሰው ውስጥ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “ለአእምሮ” ማለትም ሊሆን ይችላል።