የዮሐንስ ወንጌል 19:1-42

  • ኢየሱስ ተገረፈ፤ ሰዎችም አፌዙበት (1-7)

  • ጲላጦስ በድጋሚ ኢየሱስን ጠየቀው (8-16ሀ)

  • ኢየሱስ በጎልጎታ በእንጨት ላይ ተቸነከረ (16ለ-24)

  • ኢየሱስ ለእናቱ አስፈላጊውን ዝግጅት አደረገላት (25-27)

  • ኢየሱስ ሞተ (28-37)

  • ኢየሱስ ተቀበረ (38-42)

19  ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ ገረፈው።+  ወታደሮቹም የእሾህ አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ እንዲሁም ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤+  ወደ እሱ እየቀረቡም “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ነበር። ደግሞም በጥፊ ይመቱት ነበር።+  ጲላጦስም ዳግመኛ ወደ ውጭ ወጥቶ “ምንም ጥፋት እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እነሆ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው።+  በመሆኑም ኢየሱስ የእሾህ አክሊል እንደደፋና ሐምራዊ ልብስ እንደለበሰ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም “እነሆ፣ ሰውየው!” አላቸው።  ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ ባዩት ጊዜ “ይሰቀል! ይሰቀል!”*+ እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “እኔ ምንም ጥፋት ስላላገኘሁበት ራሳችሁ ወስዳችሁ ግደሉት”* አላቸው።+  አይሁዳውያኑም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ደግሞ ራሱን የአምላክ ልጅ ስላደረገ+ በሕጉ መሠረት መሞት አለበት”+ ሲሉ መለሱለት።  ጲላጦስ ያሉትን ነገር ሲሰማ ይበልጥ ፍርሃት አደረበት፤  ዳግመኛም ወደ ገዢው መኖሪያ ገብቶ ኢየሱስን “ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው?” አለው። ኢየሱስ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም።+ 10  ስለሆነም ጲላጦስ “መልስ አትሰጠኝም? ልፈታህም ሆነ ልገድልህ* ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው። 11  ኢየሱስም “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር። ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኃጢአት ያለበት ለዚህ ነው” ሲል መለሰለት። 12  ከዚህ የተነሳ ጲላጦስ ኢየሱስን መፍታት የሚችልበትን መንገድ ያስብ ጀመር፤ አይሁዳውያኑ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” እያሉ ጮኹ።+ 13  ጲላጦስ ይህን ከሰማ በኋላ ኢየሱስን ወደ ውጭ አውጥቶ የድንጋይ ንጣፍ በተባለ ቦታ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጋባታ ይባላል። 14  ጊዜው የፋሲካ* የዝግጅት ቀን+ ነበር፤ ሰዓቱ ደግሞ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። ጲላጦስም አይሁዳውያኑን “እነሆ፣ ንጉሣችሁ!” አላቸው። 15  እነሱ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!”* እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም “ንጉሣችሁን ልግደለው?” አላቸው። የካህናት አለቆቹም “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ሲሉ መለሱ። 16  በዚህ ጊዜ እንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።+ እነሱም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት። 17  ኢየሱስም የመከራውን እንጨት* ራሱ ተሸክሞ የራስ ቅል ቦታ+ ወደተባለ ስፍራ ወጣ፤ ይህ ቦታ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ይባላል።+ 18  በዚያም በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤+ ከእሱም ጋር ሁለት ሰዎችን የሰቀሉ ሲሆን ኢየሱስን በመካከል አድርገው አንዱን በዚህ ሌላውን በዚያ ጎን ሰቀሉ።+ 19  በተጨማሪም ጲላጦስ ጽሑፍ ጽፎ በመከራው እንጨት* ላይ አንጠለጠለው። ጽሑፉም “የአይሁዳውያን ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር።+ 20  ኢየሱስ በእንጨት ላይ የተቸነከረበት ቦታ በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ብዙ አይሁዳውያን ይህን ጽሑፍ አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክኛ ነበር። 21  ይሁን እንጂ የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን “እሱ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁዳውያን ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት። 22  ጲላጦስም “እንግዲህ የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ። 23  ወታደሮቹ ኢየሱስን በእንጨት ላይ ከቸነከሩት በኋላ መደረቢያዎቹን ወስደው እያንዳንዱ ወታደር አንድ አንድ ቁራጭ እንዲደርሰው አራት ቦታ ቆራረጧቸው፤ ከውስጥ ለብሶት የነበረውንም ልብስ ወሰዱ። ሆኖም ልብሱ ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለስፌት የተሠራ ነበር። 24  ስለዚህ እርስ በርሳቸው “ከምንቀደው ዕጣ ተጣጥለን ለማን እንደሚደርስ እንወስን” ተባባሉ።+ ይህም የሆነው “መደረቢያዎቼን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ፤ በልብሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።+ ወታደሮቹም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። 25  ይሁንና ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት* አጠገብ እናቱ፣+ የእናቱ እህት፣ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊቷ ማርያም ቆመው ነበር።+ 26  ስለዚህ ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር+ በአቅራቢያው ቆመው ሲያያቸው እናቱን “አንቺ ሴት፣ ልጅሽ ይኸውልሽ!” አላት። 27  ከዚያም ደቀ መዝሙሩን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው። ደቀ መዝሙሩም ከዚያ ሰዓት አንስቶ ወደ ራሱ ቤት ወሰዳት። 28  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሁሉም ነገር እንደተፈጸመ አውቆ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ”+ አለ። 29  በዚያም የኮመጠጠ ወይን ጠጅ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር። በመሆኑም ወይን ጠጁ ውስጥ የተነከረ ሰፍነግ፣* በሂሶጵ* አገዳ ላይ አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።+ 30  ኢየሱስ የኮመጠጠውን ወይን ጠጅ ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!”+ አለ፤ ራሱንም ዘንበል አድርጎ መንፈሱን ሰጠ።*+ 31  ዕለቱ የዝግጅት ቀን+ ስለነበር አይሁዳውያን በሰንበት (ያ ሰንበት ታላቅ ሰንበት* ስለነበር)+ አስከሬኖቹ በመከራ እንጨቶቹ ላይ ተሰቅለው እንዳይቆዩ+ ሲሉ እግራቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ ጲላጦስን ጠየቁት። 32  ስለዚህ ወታደሮቹ መጥተው ከእሱ ጋር የተሰቀሉትን የመጀመሪያውን ሰውና የሌላኛውን ሰው እግሮች ሰበሩ። 33  ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ቀደም ብሎ መሞቱን ስላዩ እግሮቹን አልሰበሩም። 34  ሆኖም ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤+ ወዲያውም ደምና ውኃ ፈሰሰ። 35  ይህን ያየው ሰውም ምሥክርነት ሰጥቷል፤ ምሥክርነቱም እውነት ነው፤ እናንተም እንድታምኑ ይህ ሰው የሚናገራቸው ነገሮች እውነት እንደሆኑ ያውቃል።+ 36  ይህም የሆነው “ከእሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም”+ የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። 37  ደግሞም ሌላ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “የወጉትን ያዩታል”+ ይላል። 38  ይህ ከሆነ በኋላ፣ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ጠየቀ፤ ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን* ይፈራ ስለነበር+ ይህን ለማንም አልተናገረም። ጲላጦስ ከፈቀደለት በኋላ መጥቶ የኢየሱስን አስከሬን ወሰደ።+ 39  ቀደም ሲል በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስም+ 30 ኪሎ ግራም* ገደማ የሚሆን የከርቤና የእሬት* ድብልቅ * ይዞ መጣ።+ 40  የኢየሱስንም አስከሬን ወስደው በአይሁዳውያን የአገናነዝ ልማድ መሠረት ጥሩ መዓዛ ባላቸው በእነዚህ ቅመሞች ተጠቅመው በበፍታ ጨርቅ ገነዙት።+ 41  እሱ በተገደለበት* ቦታ አቅራቢያ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልት ስፍራው ውስጥ ደግሞ ገና ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር።+ 42  ዕለቱ አይሁዳውያን ለበዓሉ የሚዘጋጁበት ቀን+ ስለነበርና መቃብሩም በአቅራቢያው ይገኝ ስለነበር ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል! እንጨት ላይ ይሰቀል!”
ወይም “እንጨት ላይ ስቀሉት!”
ወይም “በእንጨት ላይ ልሰቅልህ።”
እዚህ ላይ “ፋሲካ” የሚለው ቃል ለሰባት ቀናት የሚከበረውን የቂጣ በዓል ጨምሮ የፋሲካን ሳምንት ያመለክታል።
ወይም “እንጨት ላይ ስቀለው!”
ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።
ወይም “ሞተ።”
የቂጣ በዓል የሚከበርበት የመጀመሪያው ቀን ምንጊዜም የሰንበት ቀን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ይህ ሰንበት ከሳምንቱ የሰንበት ቀን ጋር ሲገጣጠም ደግሞ ታላቅ ሰንበት ተብሎ ይጠራል።
የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።
ወይም “100 የሮማውያን ፓውንድ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሽቶ ለመሥራት የሚያገለግል ጥሩ መዓዛ ያለው ንጥረ ነገር የሚገኝበትን ዛፍ ያመለክታል።
“ጥቅልል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንጨት ላይ በተሰቀለበት።”