አንደኛ ዜና መዋዕል 15:1-29

  • ሌዋውያን ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት (1-29)

    • ሜልኮል ዳዊትን ናቀችው (29)

15  ዳዊትም፣ በገዛ ከተማው ለራሱ ቤቶችን መገንባት ቀጠለ፤ ደግሞም የእውነተኛው አምላክ ታቦት የሚቀመጥበትን ስፍራ አዘጋጀ፤ ድንኳንም ተከለ።+  በዚያን ጊዜም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “ከሌዋውያን በስተቀር ማንም ሰው የእውነተኛውን አምላክ ታቦት መሸከም የለበትም፤ የይሖዋን ታቦት እንዲሸከሙና ምንጊዜም እንዲያገለግሉት ይሖዋ የመረጠው እነሱን ነውና።”+  ከዚያም ዳዊት የይሖዋን ታቦት ወዳዘጋጀለት ስፍራ እንዲያመጡ መላውን የእስራኤል ሕዝብ በኢየሩሳሌም ሰበሰበ።+  ዳዊት የአሮንን ዘሮችና+ ሌዋውያኑን+ ሰበሰበ፦  ከቀአታውያን መካከል አለቃውን ዑሪኤልንና 120 ወንድሞቹን፣  ከሜራራውያን መካከል አለቃውን አሳያህንና+ 220 ወንድሞቹን፣  ከጌርሳማውያን መካከል አለቃውን ኢዩኤልንና+ 130 ወንድሞቹን፣  ከኤሊጻፋን+ ዘሮች መካከል አለቃውን ሸማያህንና 200 ወንድሞቹን፣  ከኬብሮን ዘሮች መካከል አለቃውን ኤሊዔልንና 80 ወንድሞቹን፣ 10  ከዑዚኤል+ ዘሮች መካከል አለቃውን አሚናዳብንና 112 ወንድሞቹን ሰበሰበ። 11  በተጨማሪም ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና+ አብያታርን+ እንዲሁም ሌዋውያኑን ዑሪኤልን፣ አሳያህን፣ ኢዩኤልን፣ ሸማያህን፣ ኤሊዔልን እና አሚናዳብን ጠራ፤ 12  እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤት መሪዎች ናችሁ። እናንተና ወንድሞቻችሁ ራሳችሁን ቀድሱ፤ የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ታቦትም ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ አምጡ። 13  በመጀመሪያው ጊዜ ታቦቱን ሳትሸከሙ በመቅረታችሁ+ የአምላካችን የይሖዋ ቁጣ በእኛ ላይ ነድዶ ነበር፤+ ይህ የሆነው ትክክለኛውን መመሪያ ባለመከተላችን ነው።”+ 14  ስለዚህ ካህናቱና ሌዋውያኑ የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ታቦት ለማምጣት ራሳቸውን ቀደሱ። 15  ከዚያም ሌዋውያኑ ሙሴ በይሖዋ ቃል መሠረት እንዳዘዘው የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በመሎጊያዎቹ አድርገው በትከሻቸው ላይ ተሸከሙ።+ 16  ከዚያም ዳዊት በሙዚቃ መሣሪያዎች ይኸውም በባለ አውታር መሣሪያዎች፣ በበገና+ እና በሲምባል+ ታጅበው በደስታ ይዘምሩ ዘንድ ዘማሪ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን እንዲሾሙ ለሌዋውያኑ አለቆች ነገራቸው። 17  በመሆኑም ሌዋውያኑ የኢዩኤልን ልጅ ሄማንን፣+ ከወንድሞቹም መካከል የቤራክያህን ልጅ አሳፍን፣+ እንዲሁም ወንድሞቻቸው ከሆኑት ከሜራራውያን መካከል የቁሻያህን ልጅ ኤታንን+ ሾሙ። 18  ከእነሱ ጋር በሁለተኛው ምድብ ያሉት ወንድሞቻቸው ይገኙ ነበር፤+ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ ዘካርያስ፣ ቤን፣ ያአዚዔል፣ ሸሚራሞት፣ የሂኤል፣ ዑኒ፣ ኤልያብ፣ በናያህ፣ ማአሴያህ፣ ማቲትያህ፣ ኤሊፌሌሁ፣ ሚቅኔያህ፣ በር ጠባቂዎቹ ኦቤድዔዶም እና የኢዔል። 19  ዘማሪዎቹ ሄማን፣+ አሳፍ+ እና ኤታን ከመዳብ በተሠራ ሲምባል+ እንዲጫወቱ ተመደቡ፤ 20  ዘካርያስ፣ አዚዔል፣ ሸሚራሞት፣ የሂኤል፣ ዑኒ፣ ኤልያብ፣ ማአሴያህ እና በናያህ ደግሞ በአላሞት* ቅኝት+ በባለ አውታር መሣሪያዎች ይጫወቱ ነበር፤ 21  ማቲትያህ፣+ ኤሊፌሌሁ፣ ሚቅኔያህ፣ ኦቤድዔዶም፣ የኢዔል እና አዛዝያ ደግሞ በሸሚኒት* ቅኝት+ በገና ይጫወቱና የሙዚቀኞች ቡድን መሪ ሆነው ያገለግሉ ነበር። 22  የሌዋውያን አለቃ የሆነው ኬናንያ+ ሥራውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ታቦቱን የማጓጓዙን ሥራ በበላይነት ይከታተል ነበር፤ 23  ቤራክያህ እና ሕልቃና ታቦቱ የተቀመጠበትን ቦታ በር ይጠብቁ ነበር። 24  ካህናቱ ሸባንያህ፣ ዮሳፍጥ፣ ናትናኤል፣ አማሳይ፣ ዘካርያስ፣ በናያህ እና ኤሊዔዘር በእውነተኛው አምላክ ታቦት ፊት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት ይነፉ ነበር፤+ ኦቤድዔዶም እና የሂያህ ታቦቱ የተቀመጠበትን ቦታ በር በመጠበቅም ያገለግሉ ነበር። 25  ከዚያም ዳዊትና የእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲሁም የሺህ አለቆቹ የይሖዋን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከኦቤድዔዶም+ ቤት በታላቅ ደስታ ለማምጣት ሄዱ።+ 26  የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያን፣ እውነተኛው አምላክ ስለረዳቸው ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ሠዉ።+ 27  ዳዊት፣ ታቦቱን የተሸከሙት ሌዋውያን ሁሉ፣ ዘማሪዎቹ እንዲሁም ታቦቱን የማጓጓዙ ሥራ ኃላፊና የዘማሪዎቹ አለቃ የሆነው ኬናንያ እጅጌ የሌለው ምርጥ ልብስ ለብሰው ነበር፤ በተጨማሪም ዳዊት ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ ነበር።+ 28  መላው የእስራኤል ሕዝብ በቀንደ መለከት፣ በመለከትና+ በሲምባል ድምፅ ታጅቦ ባለ አውታር መሣሪያዎችንና በገናን+ ከፍ ባለ ድምፅ እየተጫወተ በእልልታ+ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት አመጣ። 29  ይሁንና የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በመጣ ጊዜ+ የሳኦል ልጅ ሜልኮል+ በመስኮት ሆና ወደ ታች ተመለከተች፤ ንጉሥ ዳዊት ሲዘልና በደስታ ሲጨፍር አይታ በልቧ ናቀችው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች