ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 2:1-17

  • “የዓመፅ ሰው” (1-12)

  • ጸንተው እንዲቆሙ የተሰጠ ማሳሰቢያ (13-17)

2  ይሁን እንጂ ወንድሞች፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገኘትና+ ከእሱ ጋር ለመሆን አንድ ላይ መሰብሰባችንን+ በተመለከተ ይህን እንለምናችኋለን፤  በመንፈስ በተነገረ ቃል* ወይም በቃል መልእክት ወይም ደግሞ ከእኛ የተላከ በሚመስል ደብዳቤ አማካኝነት የይሖዋ* ቀን+ ደርሷል ብላችሁ በማሰብ የማመዛዘን ችሎታችሁ በቀላሉ አይናወጥ፤+ ደግሞም አትደናገጡ።  ማንም ሰው በምንም መንገድ አያሳስታችሁ፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ክህደቱ+ ሳይመጣና የጥፋት ልጅ የሆነው የዓመፅ ሰው+ ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣም።+  እሱ አምላክ ነኝ እያለ በማወጅ በአምላክ ቤተ መቅደስ ይቀመጥ ዘንድ አምላክ ተብሎ ከሚጠራ ወይም ከሚመለክ ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው።  ያኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች እነግራችሁ እንደነበር አታስታውሱም?  በገዛ ራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን የሚያግደው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።  እርግጥ ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ አሁንም እየሠራ ነው፤+ ሆኖም ሚስጥር ሆኖ የሚቆየው አሁን አግዶት ያለው ነገር ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው።  ከዚያ በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ+ የሚያስወግደውና የእሱ መገኘት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ+ እንዳልነበረ የሚያደርገው ዓመፀኛ ይገለጣል።  ሆኖም የዓመፀኛው መገኘት የሰይጣን ሥራ+ ሲሆን ይህም የሚፈጸመው በተአምራት፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሁሉ+ 10  እንዲሁም ለማታለል ማንኛውንም ዓይነት የክፋት ዘዴ+ በመጠቀም ነው። ወደ ጥፋት እያመሩ ያሉት ሰዎች ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር በውስጣቸው ስለሌለ ይህ ሁሉ እንደ ቅጣት ይደርስባቸዋል። 11  በዚህም ምክንያት አምላክ ሐሰት የሆነውን ያምኑ ዘንድ አታላይ በሆነ ተጽዕኖ ተሸንፈው እንዲስቱ ይፈቅዳል፤+ 12  ይህን የሚያደርገው እውነትን ከማመን ይልቅ በዓመፅ ስለሚደሰቱ ሁሉም እንዲፈረድባቸው ነው። 13  ይሁን እንጂ በይሖዋ* የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ እናንተን በመንፈሱ በመቀደስ+ እንዲሁም በእውነት ላይ ባላችሁ እምነት መዳን እንድታገኙ ከመጀመሪያው አንስቶ ስለመረጣችሁ+ አምላክን ስለ እናንተ ሁልጊዜ ለማመስገን እንገፋፋለን። 14  የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር እንድታገኙ፣ እኛ በምናውጀው ምሥራች አማካኝነት ለዚህ ዓላማ ጠርቷችኋል።+ 15  ስለዚህ ወንድሞች ጸንታችሁ ቁሙ፤+ እንዲሁም ከእኛ በተላከ የቃል መልእክትም ሆነ ደብዳቤ የተማራችኋቸውን ወጎች አጥብቃችሁ ያዙ።+ 16  በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደን፣+ በጸጋም አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ+ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ 17  ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር እንድታደርጉና እንድትናገሩ ያጽኗችሁ።*

የግርጌ ማስታወሻዎች

የቃላት መፍቻው ላይ “መንፈስ” የሚለውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ያበርቷችሁ።”