ዘካርያስ 1:1-21

  • ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ የቀረበ ጥሪ (1-6)

    • ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’ (3)

  • ራእይ 1፦ በአደስ ዛፎች መካከል የቆሙት ፈረሰኞች (7-17)

    • ‘ይሖዋ እንደገና ጽዮንን ያጽናናል’ (17)

  • ራእይ 2፦ አራት ቀንዶችና አራት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች (18-21)

1  ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣+ በስምንተኛው ወር የይሖዋ ቃል ወደ ኢዶ ልጅ፣ ወደ ቤራክያህ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ*+ እንዲህ ሲል መጣ፦  “ይሖዋ በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ነበር።+  “እንዲህ በላቸው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ወደ እኔ ተመለሱ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”’  “‘የቀደሙት ነቢያት “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘እባካችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ራቁ’* ይላል በማለት የነገሯቸውን አባቶቻችሁን አትምሰሉ።”’+ “‘እነሱ ግን አልሰሙም፤ ለእኔም ትኩረት አልሰጡም’+ ይላል ይሖዋ።  “‘አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያቱስ ለዘላለም መኖር ችለዋል?  ይሁን እንጂ አገልጋዮቼ የሆኑትን ነቢያትን ያዘዝኳቸው ቃልና ድንጋጌ በአባቶቻችሁ ላይ ደርሶ የለም?’+ በመሆኑም ወደ እኔ ተመልሰው እንዲህ አሉ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በወሰነው መሠረት እንደ መንገዳችንና እንደ ሥራችን አደረገብን።’”+  ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣+ ሺባት* በተባለው በ11ኛው ወር፣ ከወሩም በ24ኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ኢዶ ልጅ፣ ወደ ቤራክያህ ልጅ፣ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦  “በሌሊት ራእይ አየሁ። አንድ ሰው ቀይ ፈረስ እየጋለበ ነበር፤ እሱም በሸለቆው ውስጥ በሚገኙት የአደስ ዛፎች መካከል ቆመ፤ ከበስተ ኋላውም ቀይ፣ ቀይ ቡኒና ነጭ ፈረሶች ነበሩ።”  እኔም “ጌታዬ ሆይ፣ እነዚህ እነማን ናቸው?” አልኩ። ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ “እነዚህ እነማን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” ሲል መለሰልኝ። 10  ከዚያም በአደስ ዛፎቹ መካከል ቆሞ የነበረው ሰው “እነዚህ በምድር ላይ እንዲመላለሱ ይሖዋ የላካቸው ናቸው” አለ። 11  እነሱም በአደስ ዛፎቹ መካከል ቆሞ ለነበረው የይሖዋ መልአክ “በምድር ላይ ተመላለስን፤ እነሆም መላዋ ምድር ጸጥታና እርጋታ ሰፍኖባታል”+ አሉት። 12  የይሖዋም መልአክ እንዲህ አለ፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ በእነዚህ 70 ዓመታት የተቆጣሃቸውን+ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ምሕረትህን የምትነፍጋቸው እስከ መቼ ነው?”+ 13  ይሖዋም ሲያነጋግረኝ ለነበረው መልአክ ደግነት በተሞላባቸውና በሚያጽናኑ ቃላት መለሰለት። 14  ከዚያም ሲያነጋግረኝ የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፦ “እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ለኢየሩሳሌምና ለጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ።+ 15  ዘና ብለው በተቀመጡት ብሔራት ላይ እጅግ ተቆጥቻለሁ፤+ ምክንያቱም በመጠኑ ብቻ ተቆጥቼ+ እያለ እነሱ ግን ከልክ ያለፈ እርምጃ ወሰዱ።”’+ 16  “ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘“ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት እመለሳለሁ፤+ የገዛ ቤቴም በውስጧ ይገነባል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “በኢየሩሳሌምም ላይ የመለኪያ ገመድ ይዘረጋል።”’+ 17  “በድጋሚ እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከተሞቼ እንደገና መልካም ነገር ይትረፈረፍባቸዋል፤ ይሖዋም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፤+ ኢየሩሳሌምንም እንደገና ይመርጣል።”’”+ 18  ከዚያም ቀና ብዬ ስመለከት አራት ቀንዶች አየሁ።+ 19  በመሆኑም ሲያነጋግረኝ የነበረውን መልአክ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። እሱም “እነዚህ ይሁዳን፣+ እስራኤልንና+ ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው”+ ሲል መለሰልኝ። 20  ከዚያም ይሖዋ አራት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች አሳየኝ። 21  እኔም “እነዚህ የመጡት ምን ሊያደርጉ ነው?” ስል ጠየቅኩ። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ፣ ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እስኪሳነው ድረስ ይሁዳን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው። እነዚህ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ደግሞ እነሱን ለማሸበር፣ ይሁዳን ይበታትኗት ዘንድ በምድሯ ላይ ቀንዶቻቸውን ያነሱትን የብሔራቱን ቀንዶች ለመጣል ይመጣሉ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ተመለሱ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።