ዳንኤል 9:1-27

 • ዳንኤል ያቀረበው የኑዛዜ ጸሎት (1-19)

  • ኢየሩሳሌም ለ70 ዓመት ባድማ ትሆናለች (2)

 • ገብርኤል ወደ ዳንኤል መጣ (20-23)

 • በትንቢት የተነገሩ 70 ሳምንታት (24-27)

  • መሲሑ ከ69 ሳምንታት በኋላ ይገለጣል (25)

  • መሲሑ ይቆረጣል (26)

  • ከተማዋና ቅዱሱ ስፍራ ይጠፋሉ (26)

9  በከለዳውያን መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመውና የሜዶናውያን ተወላጅ የሆነው የአሐሽዌሮስ ልጅ ዳርዮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣+  አዎ፣ በዘመነ መንግሥቱ የመጀመሪያ ዓመት እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ኤርምያስ በተነገረው የይሖዋ ቃል ላይ በተጠቀሰው መሠረት ኢየሩሳሌም ፈራርሳ የምትቆየው+ ለ70 ዓመት+ እንደሆነ ከመጻሕፍቱ* አስተዋልኩ።  በመሆኑም ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ ፊቴን አዞርኩ፤ ማቅ ለብሼና በራሴ ላይ አመድ ነስንሼ በጸሎትና በጾም ተማጸንኩት።+  ወደ አምላኬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ደግሞም ተናዘዝኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ+ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤+  እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ በደል ፈጽመናል፤ ክፋት ሠርተናል እንዲሁም ዓምፀናል፤+ ከትእዛዛትህና ከድንጋጌዎችህ ዞር ብለናል።  ለነገሥታታችን፣ ለመኳንንታችን፣ ለአባቶቻችንና ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በስምህ የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።+  ይሖዋ ሆይ፣ ጽድቅ የአንተ ነው፤ እኛ ግን ይኸውም የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲሁም በቅርብም ይሁን በሩቅ ባሉ አገራት ሁሉ የበተንካቸው የእስራኤል ቤት ሰዎች በሙሉ ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ኀፍረት* ተከናንበናል፤ ምክንያቱም እነሱ ለአንተ ታማኝ ሳይሆኑ ቀርተዋል።+  “ይሖዋ ሆይ፣ እኛ፣ ነገሥታታችን፣ መኳንንታችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኃጢአት በመሥራታችን ኀፍረት* ተከናንበናል።  ምሕረትና ይቅር ባይነት የአምላካችን የይሖዋ ነው፤+ እኛ በእሱ ላይ ዓምፀናልና።+ 10  የአምላካችንን የይሖዋን ቃል አልታዘዝንም፤ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት አማካኝነት የሰጠንን ሕጎችም አላከበርንም።+ 11  የእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፤ ቃልህን ባለመታዘዝም ለአንተ ጀርባቸውን ሰጥተዋል፤ በዚህም የተነሳ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ በሆነው በሙሴ ሕግ የተጻፈውን እርግማንና መሐላ በእኛ ላይ አወረድክ፤+ በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና። 12  በእኛ ላይ ታላቅ ጥፋት በማምጣት በእኛ ላይና እኛን በገዙት ገዢዎቻችን ላይ* የተናገረውን ቃል ፈጸመብን፤+ በኢየሩሳሌም ላይ እንደተፈጸመው ያለ ነገር ከሰማይ በታች ታይቶ አያውቅም።+ 13  በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው ይህ ሁሉ ጥፋት ደረሰብን፤+ ያም ሆኖ ከበደላችን በመመለስና ለእውነትህ* ትኩረት በመስጠት የአምላካችንን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አልተማጸንም።+ 14  “በመሆኑም ይሖዋ በትኩረት ሲከታተል ቆይቶ ጥፋት አመጣብን፤ አምላካችን ይሖዋ በሥራው ሁሉ ጻድቅ ነውና፤ እኛ ግን ቃሉን አልታዘዝንም።+ 15  “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በኃያል እጅ ያወጣህና+ እስከዚህ ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግክ አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣+ እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል። 16  ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ጽድቅ ሥራህ መጠን፣+ እባክህ ቁጣህንና ንዴትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ይኸውም ከቅዱስ ተራራህ መልስ፤ ምክንያቱም በኃጢአታችንና አባቶቻችን በፈጸሙት በደል የተነሳ ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ሁሉ ዘንድ መሳለቂያ ሆነዋል።+ 17  አሁንም አምላካችን ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ ይሖዋ ሆይ፣ ለራስህ ስትል ለፈረሰው+ መቅደስህ ሞገስ አሳይ።+ 18  አምላኬ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ! ዓይንህን ገልጠህ በስምህ በተጠራችው ከተማችን ላይ የደረሰውን ጥፋት ተመልከት፤ ልመናችንን በፊትህ የምናቀርበው ከእኛ ጽድቅ የተነሳ ሳይሆን ከታላቅ ምሕረትህ የተነሳ ነው።+ 19  ይሖዋ ሆይ፣ ስማ። ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በል።+ ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረት ስጥ፤ እርምጃም ውሰድ! አምላኬ ሆይ፣ ለራስህ ስትል አትዘግይ፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና።”+ 20  እኔም ገና እየተናገርኩና እየጸለይኩ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኃጢአት እየተናዘዝኩ እንዲሁም በአምላኬ ቅዱስ ተራራ+ ላይ ሞገሱን እንዲያደርግ አምላኬን ይሖዋን እየለመንኩ፣ 21  አዎ፣ እየጸለይኩ ሳለ፣ ቀደም ሲል በራእዩ+ ላይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣+ በጣም ተዳክሜ ሳለ የምሽቱ የስጦታ መባ በሚቀርብበት ጊዜ ወደ እኔ መጣ። 22  እሱም እንዲህ በማለት እንዳስተውል ረዳኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ አሁን ጥልቅ ማስተዋልና የመረዳት ችሎታ ልሰጥህ መጥቻለሁ። 23  ልመናህን ገና ማቅረብ ስትጀምር ትእዛዝ ተሰጥቷል፤ እኔም ልነግርህ መጥቻለሁ፤ ምክንያቱም አንተ እጅግ የተወደድክ* ነህ።+ ስለዚህ ለጉዳዩ ትኩረት ስጥ፤ ራእዩንም አስተውል። 24  “መተላለፍን ለማስቆም፣ ኃጢአትን ለመደምሰስ፣+ በደልን ለማስተሰረይ፣+ የዘላለም ጽድቅ ለማምጣት፣+ ራእዩንና ትንቢቱን* ለማተም+ እንዲሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ለመቀባት ለሕዝብህና ለቅድስቲቱ ከተማህ+ 70 ሳምንታት* ተወስኗል። 25  ኢየሩሳሌምን ለማደስና መልሶ ለመገንባት+ ትእዛዝ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ መሪ+ የሆነው መሲሕ*+ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ 7 ሳምንታትና 62 ሳምንታት እንደሚሆን እወቅ፤ አስተውልም።+ ኢየሩሳሌም ትታደሳለች፤ ዳግመኛም ትገነባለች፤ አደባባይዋና የመከላከያ ቦይዋ እንደገና ይሠራል፤ ይህ የሚሆነው ግን በአስጨናቂ ወቅት ነው። 26  “ከ62ቱ ሳምንታት በኋላ መሲሑ ይቆረጣል፤*+ ትቶት የሚያልፈው ምንም ነገር አይኖርም።+ “የሚመጣውም መሪ ሠራዊት፣ ከተማዋንና ቅዱሱን ስፍራ ያጠፋል።+ ፍጻሜው በጎርፍ ይሆናል። እስከ ፍጻሜውም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተወስኗል።+ 27  “እሱም ለብዙዎች ቃል ኪዳኑን ለአንድ ሳምንት ያጸናል፤ በሳምንቱም አጋማሽ ላይ መሥዋዕትንና የስጦታ መባን ያስቀራል።+ “ጥፋት የሚያመጣውም በአስጸያፊ ነገሮች ክንፍ ላይ ሆኖ ይመጣል፤+ ጥፋት እስኪመጣም ድረስ የተወሰነው ነገር በወደመው ነገር ላይ ይፈስሳል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቅዱሳን መጻሕፍቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የፊት ኀፍረት።”
ቃል በቃል “የፊት ኀፍረት።”
ቃል በቃል “በእኛ ላይ በፈረዱት በፈራጆቻችን ላይ።”
ወይም “ለታማኝነትህ።”
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”
ቃል በቃል “ነቢዩን።”
የዓመታት ሳምንታትን ያመለክታል።
ወይም “ቅቡዕ።”
ወይም “ይገደላል።”