ዘኁልቁ 27:1-23

  • የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች (1-11)

  • ኢያሱ ሙሴን እንደሚተካ ተነገረው (12-23)

27  ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ቤተሰቦች የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የጊልያድ ልጅ፣ የሄፌር ልጅ የሆነው የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች+ ቀረቡ። የሴት ልጆቹም ስም ማህላ፣ ኖኅ፣ ሆግላ፣ ሚልካ እና ቲርጻ ነበር።  እነሱም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በሙሴ፣ በካህኑ በአልዓዛር፣ በአለቆቹ+ እንዲሁም በመላው ማኅበረሰብ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፦  “አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ ይሁንና እሱ በይሖዋ ላይ ለማመፅ ከተባበሩት ከቆሬ ግብረ አበሮች+ አንዱ አልነበረም፤ እሱ የሞተው በራሱ ኃጢአት ነው፤ ወንዶች ልጆችም አልነበሩትም።  ታዲያ አባታችን ወንድ ልጅ ስለሌለው ብቻ ስሙ ከቤተሰቡ መካከል ለምን ይጥፋ? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስት ስጡን።”  ስለዚህ ሙሴ ጉዳያቸውን በይሖዋ ፊት አቀረበ።+  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች ትክክል ናቸው። በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስታቸውን ውርስ አድርገህ ልትሰጣቸው ይገባል፤ የአባታቸውም ውርስ ለእነሱ እንዲተላለፍ ማድረግ አለብህ።+  እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፦ ‘አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ውርሱ ለሴት ልጆቹ እንዲተላለፍ ማድረግ አለባችሁ።  ሴት ልጅ ከሌለው ደግሞ ውርሱን ለወንድሞቹ ትሰጣላችሁ። 10  ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ለአባቱ ወንድሞች ትሰጣላችሁ። 11  አባቱ ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ከቤተሰቡ መካከል ቅርብ ለሆነው የሥጋ ዘመዱ ትሰጣላችሁ፤ እሱም ርስት አድርጎ ይወስደዋል። ይህም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን የተደነገገ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።’” 12  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደዚህ ወደ አባሪም ተራራ+ ውጣና ለእስራኤላውያን የምሰጠውን ምድር ተመልከት።+ 13  ካየኸውም በኋላ እንደ ወንድምህ እንደ አሮን+ አንተም ወደ ወገኖችህ ትሰበሰባለህ፤*+ 14  ምክንያቱም ማኅበረሰቡ በጺን ምድረ በዳ ከእኔ ጋር በተጣላ ጊዜ ከውኃዎቹ ጋር በተያያዘ በፊታቸው ሳትቀድሱኝ በመቅረታችሁ ትእዛዜን ተላልፋችኋል።+ እነዚህም በጺን ምድረ በዳ+ በቃዴስ+ የሚገኙት የመሪባ ውኃዎች+ ናቸው።” 15  ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ 16  “የሰው* ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆነው ይሖዋ በማኅበረሰቡ ላይ አንድ ሰው ይሹም፤ 17  እሱም የይሖዋ ማኅበረሰብ እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንዳይሆን በፊታቸው የሚወጣና የሚገባ እንዲሁም እነሱን መርቶ የሚያወጣና የሚያስገባ ይሆናል።” 18  በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መንፈስ ያለበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት።+ 19  ከዚያም በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቁመው፤ በፊታቸውም ሹመው።+ 20  መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲሰማውም+ ከሥልጣንህ* የተወሰነውን ስጠው።+ 21  እሱም በኡሪም+ አማካኝነት የይሖዋን ፍርድ በሚጠይቅለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል። እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት እስራኤላውያን እንዲሁም መላው ማኅበረሰብ በእሱ ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእሱ ትእዛዝ ይገባሉ።” 22  በመሆኑም ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ። ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበረሰብ ፊት አቆመው፤ 23  ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በተናገረውም መሠረት+ እጆቹን በእሱ ላይ በመጫን ሾመው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ቃል በቃል “የሥጋ።”
ወይም “ከክብርህ።”