ነህምያ 1:1-11
1 የሃካልያህ ልጅ የነህምያ*+ ቃል ይህ ነው፦ በ20ኛው ዓመት በኪስሌው* ወር በሹሻን*+ ግንብ* ነበርኩ።
2 በዚህ ጊዜ ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው ሃናኒ+ በይሁዳ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለተረፉት አይሁዳውያን ቀሪዎችና+ ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኳቸው።
3 እነሱም እንዲህ አሉኝ፦ “ከምርኮ ተመልሰው በአውራጃው ውስጥ የሚገኙት ቀሪዎች በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፤ መሳለቂያም ሆነዋል።+ የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ፈራርሰዋል፤+ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል።”+
4 እኔም ይህን ስሰማ ቁጭ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ለቀናትም በሰማይ አምላክ ፊት ሳዝን፣ ስጾምና+ ስጸልይ ቆየሁ።
5 ከዚያም እንዲህ አልኩ፦ “የሰማይ አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅና ታማኝ ፍቅር የምታሳይ ታላቅና የምትፈራ አምላክ ነህ፤+
6 እባክህ ዛሬ ወደ አንተ የማቀርበውን የአገልጋይህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ወደ እኔ ያዘንብል፤ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ እኛ እስራኤላውያን በአንተ ላይ የፈጸምነውን ኃጢአት እየተናዘዝኩ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤላውያን ቀን ከሌት እየጸለይኩ ነው።+ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤት ኃጢአት ሠርተናል።+
7 ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠሃቸውን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ባለማክበር+ በአንተ ላይ መጥፎ ድርጊት እንደፈጸምን ምንም ጥርጥር የለውም።+
8 “እባክህ አገልጋይህን ሙሴን እንዲህ በማለት ያዘዝከውን ቃል* አስታውስ፦ ‘ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የምትፈጽሙ ከሆነ በሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ።+
9 ወደ እኔ ተመልሳችሁ ትእዛዛቴን ብትጠብቁና ብትፈጽሙ ግን ሕዝቦቻችሁ እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ቢበተኑ እንኳ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤+ እንዲሁም ስሜ እንዲኖርበት ወደመረጥኩት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’+
10 እነሱ በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የዋጀሃቸው አገልጋዮችህና ሕዝቦችህ ናቸው።+
11 ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ጸሎትና ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙ አገልጋዮችህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህን አዘንብል፤ እባክህ ዛሬ አገልጋይህ እንዲሳካለት አድርግ፤ ይህም ሰው ይራራልኝ።”+
እኔም የንጉሡ መጠጥ አሳላፊ ነበርኩ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ያህ ያጽናናል” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “በሱሳ።”
^ ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
^ ወይም “ለአገልጋይህ ለሙሴ የሰጠኸውን ማስጠንቀቂያ።”