ኤርምያስ 50:1-46

  • በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (1-46)

    • ከባቢሎን ሽሹ (8)

    • እስራኤል ወደ ምድሩ ይመለሳል (17-19)

    • የባቢሎን ውኃ ይደርቃል (38)

    • ባቢሎን የሚኖርባት አይገኝም (39, 40)

50  ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ስለ ባቢሎን+ ይኸውም ስለ ከለዳውያን ምድር የተናገረው ቃል ይህ ነው፦   “በብሔራት መካከል ይህን ተናገሩ፤ ደግሞም አውጁ። ምልክት* አቁሙ፤ ይህን አውጁ። ምንም ነገር አትደብቁ! እንዲህም በሉ፦ ‘ባቢሎን ተይዛለች።+ ቤል ኀፍረት ተከናንቧል።+ ሜሮዳክ በፍርሃት ርዷል። ምስሎቿ ተዋርደዋል። አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቿ* ተሸብረዋል።’   ከሰሜን አንድ ብሔር በእሷ ላይ ተነስቷልና።+ እሱም ምድሪቷን አስፈሪ ቦታ ያደርጋታል፤በእሷ ውስጥ የሚኖር ሰው የለም። ሰውም ሆነ እንስሳ ሸሽቷል፤አካባቢውን ለቀው ሄደዋል።”  “በእነዚያ ቀናትና በዚያ ጊዜ” ይላል ይሖዋ፣ “የእስራኤል ሕዝብም ሆነ የይሁዳ ሕዝብ በአንድነት ይመጣሉ።+ እያለቀሱ ይሄዳሉ፤+ በአንድነትም አምላካቸውን ይሖዋን ይፈልጋሉ።+  ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤+ ፊታቸውንም ወደዚያ አቅጣጫ አዙረው ‘ኑ፣ ከይሖዋ ጋር የማይረሳ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን እንግባ’ ይላሉ።+  ሕዝቤ የጠፉ በጎች መንጋ ሆኗል።+ የገዛ እረኞቻቸው እንዲባዝኑ አድርገዋቸዋል።+ ወደ ተራሮች ነዷቸው፤ እነሱም በየተራራውና በየኮረብታው ተቅበዘበዙ። ማረፊያ ቦታቸውን ረሱ።  ያገኟቸውም ሁሉ ዋጧቸው፤+ ጠላቶቻቸውም ‘በይሖዋ ይኸውም የጽድቅ መኖሪያና የአባቶቻቸው ተስፋ በሆነው በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠሩ እኛ በደለኞች አይደለንም’ ብለዋል።”   “ከባቢሎን መካከል ወጥታችሁ ሽሹ፤ከከለዳውያንም ምድር ውጡ፤+መንጋውንም እንደሚመሩ እንስሳት* ሁኑ።   እነሆ፣ እኔ ከሰሜን ምድር የታላላቅ ብሔራትን ጉባኤ አስነስቼበባቢሎን ላይ አመጣባታለሁና።+ እነሱም እሷን ለመውጋት ይሰለፋሉ፤በዚያም በኩል ትያዛለች። ፍላጻዎቻቸው እንደ ተዋጊ ፍላጻዎች ናቸው፤ወላጆችን የወላድ መሃን ያደርጋሉ፤+ዓላማቸውን ሳይፈጽሙ አይመለሱም። 10  የከለዳውያን ምድር ትበዘበዛለች።+ የሚበዘብዟትም ሁሉ እስኪበቃቸው ድረስ ይመዘብሯታል”+ ይላል ይሖዋ። 11  “እናንተ እጅግ ደስ ብሏችኋልና፤+የገዛ ርስቴን ስትመዘብሩ ሐሴት አድርጋችኋል።+ በለምለም ሣር ላይ እንዳለች ጊደር ፈንጭታችኋልና፤እንደ ድንጉላ ፈረሶችም አሽካክታችኋል። 12  እናታችሁ ለኀፍረት ተዳርጋለች።+ የወለደቻችሁም እጅግ አዝናለች። እነሆ፣ ከብሔራት ሁሉ ያነሰች፣ውኃ የሌለባት ምድረ በዳና በረሃ ሆናለች።+ 13  ከይሖዋ ቁጣ የተነሳ ሰው የማይኖርባት ምድር ትሆናለች፤+ሙሉ በሙሉ ባድማ ትሆናለች።+ በባቢሎን በኩል የሚያልፍ ሁሉ በፍርሃት አፍጥጦ ይመለከታታል፤ከደረሱባትም መቅሰፍቶች ሁሉ የተነሳ ያፏጫል።+ 14  እናንተ ደጋን የምትወጥሩ* ሁሉ፣ባቢሎንን ለመውጋት በዙሪያዋ ተሰለፉ። ፍላጻ ወርውሩባት፤ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠራች+አንድም ፍላጻ አታስቀሩ።+ 15  በዙሪያዋ ሁሉ ቀረርቶ አሰሙ። እጇን ሰጥታለች። ዓምዶቿ ወድቀዋል፤ ቅጥሮቿ ፈርሰዋል፤+ይህ የይሖዋ በቀል ነውና።+ እሷን ተበቀሏት። እንዳደረገችው አድርጉባት።+ 16  ዘር የሚዘራውንናበመከር ወቅት ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አስወግዱ።+ ከጨካኙ ሰይፍ የተነሳ እያንዳንዱ ወደ ገዛ ሕዝቡ ይመለሳል፤እያንዳንዱም ወደ ገዛ ምድሩ ይሸሻል።+ 17  “የእስራኤል ሕዝብ የባዘነ በግ ነው።+ እንዲባዝን ያደረጉት አንበሶች ናቸው።+ በመጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፤+ ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* አጥንቱን ቆረጣጠመው።+ 18  ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ በአሦር ንጉሥ ላይ እንዳደረግኩት ሁሉ በባቢሎን ንጉሥና በምድሩ ላይ እንዲሁ አደርጋለሁ።+ 19  እስራኤልንም ወደ መሰማሪያው እመልሰዋለሁ፤+ እሱም በቀርሜሎስና በባሳን ይሰማራል፤+ በኤፍሬምና+ በጊልያድ+ ተራሮችም ላይ እስኪጠግብ ድረስ ይመገባል።’”* 20  “በእነዚያ ቀናትና በዚያ ጊዜ” ይላል ይሖዋ፣“የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤ሆኖም አይገኝም፤የይሁዳም ኃጢአት አይገኝም፤እንዲተርፉ ያደረግኳቸውን ይቅር እላቸዋለሁና።”+ 21  “በመረታይም ምድር ላይ ውጣ፤ በጰቆድ+ ነዋሪዎችም ላይ ተነሳ። ነዋሪዎቹ ይጨፍጨፉ፤ ሙሉ በሙሉም ይጥፉ”* ይላል ይሖዋ። “ያዘዝኩህንም ሁሉ አድርግ። 22  በምድሪቱ ላይ የጦርነትናየታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል። 23  የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ተቆረጠ! እንዴትስ ተሰበረ!+ ባቢሎን በብሔራት መካከል እንዴት መቀጣጫ ሆነች!+ 24  ባቢሎን ሆይ፣ በአንቺ ላይ ወጥመድ ዘርግቻለሁ፤ ደግሞም ተይዘሻል፤አንቺ ግን አልታወቀሽም። ተገኘሽ፤ እንዲሁም ተያዝሽ፤+የተቃወምሽው ይሖዋን ነውና። 25  ይሖዋ ግምጃ ቤቱን ከፍቷል፤የቁጣ የጦር መሣሪያዎቹንም ያወጣል።+ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋበከለዳውያን ምድር የሚሠራው ሥራ አለና። 26  ከሩቅ ቦታ መጥታችሁ በእሷ ላይ ውጡ።+ ጎተራዎቿን ክፈቱ።+ እንደ እህል ክምር ከምሯት። ፈጽማችሁ አጥፏት።+ አንድም ሰው አታስቀሩላት። 27  ወይፈኖቿን ሁሉ እረዱ፤+ወደ እርድ ቦታ ይውረዱ። ቀናቸው ይኸውም የሚመረመሩበት ጊዜስለደረሰ ወዮላቸው! 28  የአምላካችንን የይሖዋን በቀል፣ስለ ቤተ መቅደሱ ሲል የወሰደውን የበቀል እርምጃ+ በጽዮን ለማወጅከባቢሎን ምድር የሚሸሹናአምልጠው የሚሄዱ ሰዎች ድምፅ ይሰማል። 29  ቀስተኞችን፣ ደጋን የሚወጥሩትንም* ሁሉበባቢሎን ላይ ጥሩ።+ በዙሪያዋም ስፈሩ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ። እንደ ሥራዋ መልሱላት።+ እሷ እንዳደረገችው ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉባት።+ በይሖዋ ላይ ይኸውም በእስራኤል ቅዱስ ላይየእብሪት ድርጊት ፈጽማለችና።+ 30  በመሆኑም ወጣቶቿ በአደባባዮቿ ይወድቃሉ፤+በዚያም ቀን ወታደሮቿ ሁሉ ይጠፋሉ”* ይላል ይሖዋ። 31  “አንቺ ዓመፀኛ፣+ እነሆ፣ እኔ በአንቺ ላይ ተነስቻለሁ”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤“ቀንሽ ይኸውም አንቺን ተጠያቂ የማደርግበት ጊዜ ይመጣልና። 32  አንቺ ዓመፀኛ ተሰናክለሽ ትወድቂያለሽ፤የሚያነሳሽም አይኖርም።+ ከተሞችሽንም በእሳት አነዳለሁ፤በዙሪያሽም ያለውን ሁሉ ይበላል።” 33  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ተጨቁነዋል፤ማርከው የወሰዷቸውም ሁሉ ጠፍረው ይዘዋቸዋል።+ እነሱን ለመልቀቅ ፈቃደኞች አልሆኑም።+ 34  ይሁንና የሚቤዣቸው ብርቱ ነው።+ ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።+ ለምድሪቱ እረፍት ለመስጠትና+የባቢሎንን ነዋሪዎች ለማሸበር+ያላንዳች ጥርጥር ይሟገትላቸዋል።”+ 35  “በከለዳውያን፣ በባቢሎን ነዋሪዎች፣ በመኳንንቷእንዲሁም በጥበበኞቿ ላይ ሰይፍ ተመዟል” ይላል ይሖዋ።+ 36  “ከንቱ ነገር በሚናገሩ ሰዎች* ላይ ሰይፍ ተመዟል፤ እነሱም የሞኝነት ድርጊት ይፈጽማሉ። በተዋጊዎቿ ላይ ሰይፍ ተመዟል፤ እነሱም በሽብር ይዋጣሉ።+ 37  በፈረሶቻቸው፣ በጦር ሠረገሎቻቸውናበመካከሏ በሚኖሩ ድብልቅ ሕዝብ ሁሉ ላይ ሰይፍ ተመዟል፤እነሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ።+ ውድ በሆኑ ሀብቶቿ ላይ ሰይፍ ተመዟል፤ እነሱም ይዘረፋሉ።+ 38  ውኃዎቿ ይበከላሉ፤ ይደርቃሉም።+ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናትና፤+አስፈሪ በሆኑት ራእዮቻቸው የተነሳ እንደ እብድ ያደርጋቸዋል። 39  ስለዚህ የበረሃ ፍጥረታት ከሚያላዝኑ እንስሳት ጋር ይኖራሉ፤በእሷም ውስጥ ሰጎኖች ይኖራሉ።+ ከዚህ በኋላ የሚኖርባት አይገኝም፤ከትውልድ እስከ ትውልድም ማንም አይቀመጥባትም።”+ 40  “አምላክ ሰዶምንና ገሞራን+ እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉትን ከተሞች በደመሰሰ ጊዜ+ እንደሆነው ሁሉ” ይላል ይሖዋ፣ “በዚያ ማንም አይኖርም፤ አንድም ሰው በዚያ አይቀመጥም።+ 41  እነሆ፣ አንድ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል፤አንድ ታላቅ ብሔርና ታላላቅ ነገሥታት+ከምድር ዳርቻዎች ይነሳሉ።+ 42  ቀስትና ጦር ይይዛሉ።+ ጨካኝና ምሕረት የለሽ ናቸው።+ ፈረሶቻቸውን እየጋለቡ ሲመጡድምፃቸው እንደሚጮኽ ባሕር ነው።+ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣ አንቺን ለመውጋት በአንድ ልብ ሆነው ይሰለፉብሻል።+ 43  የባቢሎን ንጉሥ ስለ እነሱ ወሬ ሰምቷል፤+እጆቹም ይዝለፈለፋሉ።+ ጭንቀት ይይዘዋል፤ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት ይሠቃያል። 44  “እነሆ፣ አንድ ሰው፣ እንደ አንበሳ በዮርዳኖስ ዳርቻ ከሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ጥሻዎች ወጥቶ አስተማማኝ በሆነው መሰማሪያ ላይ ይመጣል፤ እኔ ግን ወዲያውኑ ከእሷ አባርራቸዋለሁ። የተመረጠውን በእሷ ላይ እሾማለሁ።+ እንደ እኔ ያለ ማነው? ማንስ ሊሟገተኝ ይችላል? በእኔ ፊት ሊቆም የሚችል እረኛ የትኛው ነው?+ 45  ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ ይሖዋ በባቢሎን ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔና*+ በከለዳውያን ምድር ላይ ያሰበውን ሐሳብ ስሙ። ከመንጋው መካከል ትናንሽ የሆኑት ተጎትተው መወሰዳቸው አይቀርም። ከእነሱ የተነሳ መሰማሪያቸውን ባድማ ያደርጋል።+ 46  ባቢሎን ስትያዝ ከሚሰማው ድምፅ የተነሳ ምድር ትናወጣለች፤ከብሔራትም መካከል ጩኸት ይሰማል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “አውራ በጎችና አውራ ፍየሎች።”
ቃል በቃል “የምትረግጡ።”
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “ነፍሱ እስክትጠግብ ድረስ ትመገባለች።”
ወይም “ለጥፋት ለያቸው።”
ቃል በቃል “የሚረግጡትንም።”
ቃል በቃል “ጸጥ ይላሉ።”
ወይም “በሐሰተኛ ነቢያት።”
ወይም “የመከረውን ምክርና።”