ዳንኤል 10:1-21

  • ከአምላክ የተላከ መልእክተኛ ወደ ዳንኤል መጣ (1-21)

    • ሚካኤል መልአኩን ረዳው (13)

10  የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ተብሎ የተጠራው ዳንኤል+ አንድ ራእይ ተሰጠው፤ ይህም መልእክት እውነት ነው፤ መልእክቱም ስለ አንድ ታላቅ ውጊያ ይገልጻል። እሱም መልእክቱን ተረድቶት ነበር፤ ያየውንም ነገር ማስተዋል ችሎ ነበር።  በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ በሐዘን ላይ ነበርኩ።+  ሦስቱ ሳምንታት እስኪያበቁ ድረስ ምርጥ ምግብ አልበላሁም፤ ሥጋም ሆነ የወይን ጠጅ አልቀመስኩም እንዲሁም ሰውነቴን ቅባት አልተቀባሁም።  በመጀመሪያው ወር በ24ኛው ቀን በታላቁ ወንዝ ይኸውም በጤግሮስ*+ ዳርቻ ሳለሁ፣  ቀና ብዬ ስመለከት በፍታ የለበሰና+ ወገቡ ላይ በዑፋዝ ወርቅ የተሠራ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ።  ሰውነቱ እንደ ክርስቲሎቤ፣+ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዓይኖቹ እንደሚንቦገቦግ ችቦ፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደሚያብረቀርቅ መዳብ፣+ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር።  ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርኩ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም።+ ነገር ግን እጅግ ስለተሸበሩ ሸሽተው ተደበቁ።  እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ይህን ታላቅ ራእይ በተመለከትኩ ጊዜም በውስጤ ምንም ኃይል አልቀረም፤ ግርማ ሞገስ የተላበሰው ቁመናዬ ተለወጠ፤ ኃይሌም በሙሉ ተሟጠጠ።+  ከዚያም ሲናገር ድምፁን ሰማሁ፤ ሆኖም ሲናገር እየሰማሁት ሳለ በግንባሬ መሬት ላይ ተደፍቼ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ።+ 10  በዚህ ጊዜ አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤+ ከቀሰቀሰኝ በኋላ በእጄና በጉልበቴ ተደግፌ እንድነሳ አደረገኝ። 11  ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “እጅግ የተወደድክ*+ ዳንኤል ሆይ፣ የምነግርህን ቃል አስተውል። በነበርክበት ቦታ ላይ ቁም፤ ወደ አንተ ተልኬ መጥቼአለሁና።” ይህን ሲለኝ እየተንቀጠቀጥኩ ቆምኩ። 12  ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ አትፍራ።+ እነዚህን ነገሮች ለመረዳት ልባዊ ጥረት ማድረግና በአምላክህ ፊት ራስህን ዝቅ ማድረግ ከጀመርክበት ቀን አንስቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የመጣሁት ከቃልህ የተነሳ ነው።+ 13  ሆኖም የፋርስ ንጉሣዊ ግዛት አለቃ+ ለ21 ቀናት ተቋቋመኝ። በኋላ ግን ከዋነኞቹ አለቆች* አንዱ የሆነው ሚካኤል*+ ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያን ጊዜ ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ቆየሁ። 14  ራእዩ ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ስለሆነ+ በዘመኑ መጨረሻ በሕዝብህ ላይ የሚደርሰውን ነገር አስረዳህ ዘንድ መጥቻለሁ።”+ 15  ይህን ቃል በነገረኝ ጊዜ ወደ መሬት አቀረቀርኩ፤ መናገርም ተሳነኝ። 16  በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤+ እኔም አፌን ከፍቼ በፊቴ ቆሞ የነበረውን እንዲህ አልኩት፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ከራእዩ የተነሳ እየተንቀጠቀጥኩ ነው፤ ኃይሌም ተሟጥጧል።+ 17  ስለዚህ የጌታዬ አገልጋይ ከጌታዬ ጋር እንዴት መነጋገር ይችላል?+ አሁን ምንም ኃይል የለኝምና፤ በውስጤም የቀረ እስትንፋስ የለም።”+ 18  ሰው የሚመስለው እንደገና ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም።+ 19  ከዚያም “አንተ እጅግ የተወደድክ* ሰው+ ሆይ፣ አትፍራ።+ ሰላም ለአንተ ይሁን።+ በርታ፣ አይዞህ በርታ” አለኝ። እንዲህ ባለኝ ጊዜ ተበረታትቼ “ጌታዬ ሆይ፣ ብርታት ሰጥተኸኛልና ተናገር” አልኩት። 20  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አሁን ከፋርስ አለቃ ጋር ለመዋጋት ተመልሼ እሄዳለሁ።+ እኔ ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21  ሆኖም በእውነት መጽሐፍ ላይ የሠፈሩትን ነገሮች እነግርሃለሁ። ከእነዚህ ነገሮች ጋር በተያያዘ የሕዝብህ አለቃ+ ከሆነው ከሚካኤል+ በስተቀር በእጅጉ ሊረዳኝ የሚችል የለም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በሂዲኬል።”
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የመጀመሪያውን ደረጃ ከያዙት አለቆች።”
ወይም “ትልቅ ግምት የሚሰጥህ፤ እጅግ የተከበርክ።”