ኢዮብ 8:1-22

  • የበልዳዶስ የመጀመሪያ ዙር ንግግር (1-22)

    • የኢዮብ ልጆች ኃጢአት ሠርተው ሊሆን እንደሚችል ጠቆመ (4)

    • ‘ንጹሕ ብትሆን ኖሮ አምላክ ይጠብቅህ ነበር’ (6)

    • ኢዮብ አምላክ የለሽ እንደሆነ ጠቆመ (13)

8  ከዚያም ሹሃዊው+ በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦  2  “እንዲህ የምትናገረው እስከ መቼ ነው?+ ከአፍህ የሚወጣው ቃል ብርቱ ነፋስ ነው!  3  አምላክ ፍትሕን ያዛባል?ወይስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጽድቅን ያጣምማል?  4  ልጆችህ በእሱ ላይ ኃጢአት ሠርተው ከሆነ፣ለፈጸሙት ዓመፅ እንዲቀጡ አድርጓል፤*  5  አንተ ግን ወደ አምላክ ዞር ብትል፣+ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሞገስ እንዲያሳይህ ብትማጸን፣  6  በእርግጥ ንጹሕና ቅን ብትሆን፣+እሱ ትኩረት ይሰጥሃል፤*ወደ ትክክለኛ ቦታህም ይመልስሃል።  7  ጅማሬህ አነስተኛ ቢሆንም፣የወደፊት ሕይወትህ ታላቅ ይሆናል።+  8  እስቲ የቀድሞውን ትውልድ ጠይቅ፤አባቶቻቸው ለተገነዘቧቸው ነገሮችም ትኩረት ስጥ።+  9  እኛ የተወለድነው ገና ትናንት ስለሆነ የምናውቀው ነገር የለም፤ምክንያቱም በምድር ላይ ዘመናችን እንደ ጥላ ነው። 10  እነሱ አያስተምሩህም?ደግሞስ የሚያውቁትን ነገር* አይነግሩህም? 11  ደንገል ረግረጋማ ባልሆነ ስፍራ ያድጋል? ሸምበቆስ ውኃ በሌለበት ቦታ ያድጋል? 12  ገና ሳያብብና ሳይቆረጥ፣ከሌላው ተክል ሁሉ በፊት ይደርቃል። 13  አምላክን የሚረሱ ሰዎች ሁሉ መጨረሻቸው እንደዚህ ነው፤*አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው ተስፋ ይጨልማልና፤ 14  የሚመካበት ነገር ከንቱ ነው፤የሚታመንበትም ነገር ከሸረሪት ድር* የማይሻል ነው። 15  እሱ ቤቱን ይደገፈዋል፤ ሆኖም ቤቱ ጸንቶ አይቆምም፤አጥብቆ ሊይዘው ይሞክራል፤ ሆኖም አይጸናም። 16  እሱ በፀሐይ ብርሃን እንደሚያድግ እርጥበት ያለው ተክል ነው፤ቅርንጫፎቹም በአትክልት ስፍራው ውስጥ ይንሰራፋሉ።+ 17  ሥሩም በድንጋይ ክምር ውስጥ ይጠላለፋል፤በድንጋዮቹ መካከል ቤት ይፈልጋል።* 18  ሆኖም ከስፍራው በሚነቀልበት* ጊዜ፣ያ ስፍራ ‘ፈጽሞ አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል።+ 19  አዎ፣ በዚህ ሁኔታ ይጠፋል፤*+ከዚያም ሌሎች ከአፈሩ ውስጥ ይበቅላሉ። 20  በእርግጥም አምላክ ንጹሕ አቋማቸውን* የሚጠብቁትን አይጥልም፤ክፉ ሰዎችንም አይረዳም፤* 21  በመጨረሻም አፍህን በሳቅ፣ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላል። 22  የሚጠሉህ ኀፍረት ይከናነባሉ፤የክፉዎችም ድንኳን ይጠፋል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ቃል በቃል “ወደ ዓመፃቸው እጅ ልኳቸዋል።”
^ ወይም “እሱ ስለ አንተ ይነሳል።”
^ ቃል በቃል “ከልባቸውም ቃል አውጥተው።”
^ ቃል በቃል “መንገዶቻቸው እንደዚህ ናቸው።”
^ ወይም “የከሃዲ።”
^ ቃል በቃል “ቤት።”
^ ወይም “የድንጋይ ቤት ይመለከታል።”
^ ወይም “በሚዋጥበት።”
^ ወይም “መንገዱ በዚህ ሁኔታ ያከትማል።”
^ ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
^ ቃል በቃል “(የክፉ ሰዎችን) እጅ አይዝም።”