ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-16

  • “ወደ እረፍቴ አይገቡም” (1-10)

  • ወደ አምላክ እረፍት እንዲገቡ የተሰጠ ማበረታቻ (11-13)

    • ‘የአምላክ ቃል ሕያው ነው’ (12)

  • ኢየሱስ፣ ታላቅ ሊቀ ካህናት (14-16)

4  ስለዚህ ወደ እረፍቱ የመግባት ተስፋ አሁንም ስላለ ከእናንተ መካከል ማንም ለዚያ የማይበቃ ሆኖ እንዳይገኝ እንጠንቀቅ።*+  ለአባቶቻችን ተሰብኮ እንደነበረው ሁሉ ምሥራቹ ለእኛም ተሰብኳልና፤+ እነሱ ግን ሰምተው የታዘዙት ሰዎች የነበራቸው ዓይነት እምነት ስላልነበራቸው የሰሙት ቃል አልጠቀማቸውም።  እኛ ግን እምነት በማሳየታችን ወደዚህ እረፍት እንገባለን። ምንም እንኳ የእሱ ሥራ ዓለም ከተመሠረተበት* ጊዜ ጀምሮ የተጠናቀቀ ቢሆንም+ “‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ” ብሏል።+  በአንድ ቦታ ላይ ሰባተኛውን ቀን አስመልክቶ “አምላክም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ” ብሏልና፤+  እንደገና እዚህ ላይ “ወደ እረፍቴ አይገቡም” ብሏል።+  ስለዚህ ገና ወደ እረፍቱ የሚገቡ ስላሉና መጀመሪያ ምሥራቹ የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሳይገቡ ስለቀሩ+  ከረጅም ጊዜ በኋላ በዳዊት መዝሙር ላይ “ዛሬ” በማለት እንደገና አንድን ቀን መደበ፤ ይህም ቀደም ሲል “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+  ኢያሱ+ ወደ እረፍት ቦታ እየመራ አስገብቷቸው ቢሆን ኖሮ አምላክ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።  ስለዚህ የአምላክ ሕዝብ የሰንበት እረፍት ገና ይቀረዋል።+ 10  ወደ አምላክ እረፍት የገባ ሰው አምላክ ከሥራው እንዳረፈ ሁሉ እሱም ከሥራው አርፏልና።+ 11  ስለዚህ ማንም የእነዚያን ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ እረፍት ለመግባት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።+ 12  የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤+ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤+ ነፍስንና* መንፈስን* እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል። 13  ደግሞም ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤+ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት+ በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው። 14  እንግዲህ ወደ ሰማያት የገባ ታላቅ ሊቀ ካህናት ይኸውም የአምላክ ልጅ+ ኢየሱስ እንዳለን ስለምናውቅ በእሱ ላይ እምነት እንዳለን ምንጊዜም በይፋ እንናገር።+ 15  ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለምና፤+ ከዚህ ይልቅ እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁንና እሱ ኃጢአት የለበትም።+ 16  እንግዲህ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለምንም ፍርሃት* ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እንፍራ።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “የመናገር ነፃነት ተሰምቶን።”