ኢዮብ 1:1-22
1 በዑጽ ምድር የሚኖር ኢዮብ*+ የሚባል ሰው ነበር። እሱም በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው*+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር።+
2 ኢዮብ ሰባት ወንዶች ልጆችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
3 የከብቶቹም ብዛት 7,000 በጎች፣ 3,000 ግመሎች፣ 1,000 ከብቶች፣* 500 አህዮች* ነበር፤ በተጨማሪም እጅግ ብዙ አገልጋዮች ስለነበሩት በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው ሆነ።
4 ወንዶች ልጆቹ ሁሉ በተመደበላቸው ተራ መሠረት በየቤታቸው* ግብዣ ያደርጉ ነበር። እነሱም ሦስቱ እህቶቻቸው አብረዋቸው እንዲበሉና እንዲጠጡ ይጋብዟቸው ነበር።
5 ሁሉም ተራው ደርሷቸው የግብዣዎቹ ቀናት ከተጠናቀቁ በኋላ ኢዮብ ልጆቹ ይቀደሱ ዘንድ መልእክት ይልክባቸው ነበር። ከዚያም “ልጆቼ ኃጢአት ሠርተውና አምላክን በልባቸው ረግመው ይሆናል” ብሎ በማሰብ በማለዳ ተነስቶ ለእያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+ ኢዮብ ሁልጊዜ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው።+
6 የእውነተኛው አምላክ ልጆች*+ በይሖዋ ፊት ለመቆም+ የሚገቡበት ቀን በደረሰ ጊዜ ሰይጣንም+ መጥቶ በመካከላቸው ቆመ።+
7 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “ከየት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም “በምድር ሁሉ ላይ ስዞርና በእሷ ላይ ስመላለስ ቆይቼ መጣሁ”+ ሲል ለይሖዋ መለሰ።
8 ይሖዋም ሰይጣንን እንዲህ አለው፦ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትከው?* በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም። በንጹሕ አቋም* የሚመላለስ ቅን ሰው+ እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነው።”
9 ሰይጣንም ለይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲያው በከንቱ ነው?+
10 እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም?+ የእጁን ሥራ ባርከህለታል፤+ ከብቱም በምድሪቱ ላይ በዝቷል።
11 ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”
12 ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንን “እነሆ፣ ያለው ነገር ሁሉ በእጅህ* ነው። እሱን ራሱን ግን እንዳትነካው!” አለው። ሰይጣንም ከይሖዋ ፊት ወጥቶ ሄደ።+
13 የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ በነበረበት ቀን፣+
14 አንድ መልእክተኛ ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ከብቶቹ እያረሱ፣ አህዮቹም በአጠገባቸው እየጋጡ ሳለ
15 ሳባውያን ጥቃት ሰንዝረው ወሰዷቸው፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”
16 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ከአምላክ ዘንድ ከሰማያት እሳት ወረደች፤* በበጎቹና በአገልጋዮቹ መካከልም ነድዳ በላቻቸው! እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”
17 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ከለዳውያን+ በሦስት ቡድን መጥተው በድንገት ጥቃት በመሰንዘር ግመሎቹን ወሰዱ፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”
18 እሱ ገና እየተናገረ ሳለ ሌላው ደግሞ መጥቶ እንዲህ አለ፦ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ነበር።
19 በድንገት ከምድረ በዳው ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ የቤቱን አራት ማዕዘናት መታ፤ ቤቱም በልጆችህ ላይ ወድቆ ገደላቸው። እኔም ብቻዬን አምልጬ ልነግርህ መጣሁ።”
20 በዚህ ጊዜ ኢዮብ ተነስቶ ልብሱን ቀደደ፤ ፀጉሩንም ተላጨ፤ ከዚያም መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤
21 እንዲህም አለ፦
“ከእናቴ ማህፀን ራቁቴን ወጣሁ፤ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ።+
ይሖዋ ሰጠ፤+ ይሖዋ ነሳ።
የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ።”
22 ኢዮብ ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኃጢአት አልሠራም ወይም አምላክን በደል ሠርቷል ብሎ አልወነጀለም።*
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “የጥላቻ ዒላማ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
^ ወይም “ነቀፋ የሌለበትና ቅን ሰው።”
^ ቃል በቃል “500 ጥማድ ከብቶች።”
^ ቃል በቃል “እንስት አህዮች።”
^ ወይም “ወንዶች ልጆቹ ሁሉ በእያንዳንዳቸው ቤት በተራቸው።”
^ የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።
^ ቃል በቃል “(በአገልጋዬ በኢዮብ) ላይ ልብህን አኑረሃል?”
^ ወይም “በቁጥጥርህ ሥር።”
^ “መብረቅ ወረደ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “በአምላክ ላይ አግባብ ያልሆነ ነገር አልተናገረም።”