ዘፀአት 21:1-36

  • ለእስራኤላውያን የተሰጡ ድንጋጌዎች (1-36)

    • ከዕብራውያን ባሮች ጋር በተያያዘ (2-11)

    • በባልንጀራ ላይ ከሚወሰድ የኃይል እርምጃ ጋር በተያያዘ (12-27)

    • ከእንስሳት ጋር በተያያዘ (28-36)

21  “ለእነሱ የምትነግራቸው ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው፦+  “ዕብራዊ ባሪያ ከገዛህ+ ለስድስት ዓመት ባሪያ ሆኖ ያገለግልሃል፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ያለምንም ክፍያ ነፃ ይወጣል።+  የመጣው ብቻውን ከሆነ ብቻውን ነፃ ይወጣል። ሚስት ካለችው ግን ሚስቱም አብራው ነፃ ትውጣ።  ጌታው ሚስት ቢያጋባውና ሚስቱ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆችን ብትወልድለት ሚስቱና ልጆቿ የጌታዋ ይሆናሉ፤ እሱም ብቻውን ነፃ ይወጣል።+  ሆኖም ባሪያው ‘ጌታዬን፣ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ፤ ነፃ መውጣት አልፈልግም’+ በማለት በአቋሙ ከጸና  ጌታው በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርበው። ከዚያም ጌታው ወደ በሩ ወይም ወደ መቃኑ አምጥቶ ጆሮውን በወስፌ ይበሳዋል፤ እሱም ዕድሜውን ሙሉ ባሪያው ይሆናል።  “አንድ ሰው ሴት ልጁን ባሪያ አድርጎ ቢሸጣት ነፃ የምትወጣው ወንድ ባሪያ ነፃ በሚወጣበት መንገድ አይደለም።  ጌታዋ ደስ ባይሰኝባትና ቁባቱ እንድትሆን ባይፈልግ ከዚህ ይልቅ ሌላ ሰው እንዲገዛት* ቢያደርግ እሷን ለባዕድ አገር ሰው የመሸጥ መብት አይኖረውም፤ ምክንያቱም ክህደት ፈጽሞባታል።  ለወንድ ልጁ እንድትሆን ከመረጣት ደግሞ አንዲት ልጅ ማግኘት የሚገባትን መብት እንድታገኝ ያድርግ። 10  ሌላ ሚስት ካገባም የመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧ፣ ልብሷና የጋብቻ መብቷ ሊጓደልባት አይገባም።+ 11  እነዚህን ሦስት ነገሮች የማያሟላላት ከሆነ ግን ምንም ገንዘብ ሳትከፍል እንዲሁ ነፃ ትውጣ። 12  “አንድ ሰው ሌላውን ሰው መትቶ ቢገድል ገዳዩ ይገደል።+ 13  ሆኖም የገደለው ሆን ብሎ ባይሆንና እውነተኛው አምላክ ይህ ነገር እንዲሆን ቢፈቅድ ገዳዩ የሚሸሽበት ቦታ እኔ አዘጋጅልሃለሁ።+ 14  አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ እጅግ ቢቆጣና ሆን ብሎ ቢገድለው+ ይህን ሰው ከመሠዊያዬ አጠገብም እንኳ ቢሆን ወስደህ ግደለው።+ 15  አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ይገደል።+ 16  “ማንኛውም ግለሰብ አንድን ሰው አፍኖ ቢወስድና+ ቢሸጠው ወይም ይህን ሰው ይዞት ቢገኝ+ ይገደል።+ 17  “አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ይገደል።+ 18  “ሰዎች ተጣልተው አንደኛው ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ* ቢመታውና ተመቺው ባይሞት ከዚህ ይልቅ አልጋ ላይ ቢውል መደረግ ያለበት ነገር ይህ ነው፦ 19  ሰውየው ከአልጋው በመነሳት ከቤት ወጥቶ በምርኩዝ መንቀሳቀስ ከቻለ የመታው ሰው ከቅጣት ነፃ ይሆናል። ተጎጂው ሙሉ በሙሉ እስኪድን ድረስ ከሥራ በመስተጓጎሉ ለባከነበት ጊዜ ብቻ ካሳ ይከፍላል። 20  “አንድ ሰው ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታና እጁ ላይ ቢሞትበት ወይም ብትሞትበት ይህ ሰው የበቀል ቅጣት መቀጣት አለበት።+ 21  ሆኖም ባሪያው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን በሕይወት ከቆየ የበቀል ቅጣት መቀጣት የለበትም፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በጌታው ገንዘብ የተገዛ ነው። 22  “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና ያለጊዜዋ ብትወልድ*+ ሆኖም ለሞት* የተዳረገ ባይኖር ጉዳት ያደረሰው ሰው የሴትየዋ ባል የጠየቀውን ካሳ መክፈል አለበት፤ ፈራጆቹ የወሰኑበትን ካሳ መክፈል ይኖርበታል።+ 23  ሆኖም ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት፣*+ 24  ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ፣ እግር ስለ እግር፣+ 25  መቃጠል ስለ መቃጠል፣ ቁስል ስለ ቁስል እንዲሁም ምት ስለ ምት እንዲመለስ ማድረግ አለብህ። 26  “አንድ ሰው የወንድ ባሪያውን ወይም የሴት ባሪያውን ዓይን ቢመታና ዓይኑን ቢያጠፋው ለዓይኑ ካሳ እንዲሆን ባሪያውን ነፃ ሊያወጣው ይገባል።+ 27  የወንድ ባሪያውን ወይም የሴት ባሪያውን ጥርስ ቢያወልቅ ለጥርሱ ካሳ እንዲሆን ከባርነቱ ነፃ አድርጎ ሊያሰናብተው ይገባል። 28  “አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢወጋና የተወጋው ሰው ቢሞት በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይገደል፤+ ሥጋውም መበላት የለበትም። የበሬው ባለቤት ግን ከቅጣት ነፃ ነው። 29  በሬው የመዋጋት አመል እንዳለው የሚታወቅ ከሆነና ለባለቤቱም ስለ በሬው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከነበረ በሬውን ሳይጠብቀው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም ይገደል። 30  ቤዛ* እንዲከፍል ከተጠየቀ ለሕይወቱ* መዋጃ የሚሆነውን ዋጋ ይክፈል፤ የተጠየቀውንም ሁሉ ይስጥ። 31  በሬው ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢወጋ የበሬው ባለቤት በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ሊፈረድበት ይገባል። 32  በሬው የወጋው አንድን ወንድ ባሪያ ወይም አንዲትን ሴት ባሪያ ከሆነ የበሬው ባለቤት ለባሪያው ጌታ 30 ሰቅል* ይሰጠዋል፤ በሬውም በድንጋይ ተወግሮ ይገደላል። 33  “አንድ ሰው ጉድጓድ ከፍቶ ወይም ቆፍሮ ጉድጓዱን ሳይከድነው ቢተወውና አንድ በሬ ወይም አንድ አህያ ጉድጓዱ ውስጥ ቢወድቅ 34  የጉድጓዱ ባለቤት ካሳ መክፈል አለበት።+ ዋጋውን ለእንስሳው ባለቤት መስጠት ይኖርበታል፤ የሞተውም እንስሳ የእሱ ይሆናል። 35  የአንድ ሰው በሬ በሌላው ሰው በሬ ላይ ጉዳት ቢያደርስና በሬው ቢሞት ሰዎቹ በሕይወት ያለውን በሬ ሸጠው ገንዘቡን ይካፈሉ፤ የሞተውንም በሬ ይካፈሉ። 36  ወይም በሬው የመዋጋት አመል እንዳለበት እየታወቀ ባለቤቱ ሳይጠብቀው ቀርቶ ከሆነ ባለቤቱ በበሬ ፋንታ በሬ ካሳ መክፈል አለበት፤ የሞተውም በሬ የእሱ ይሆናል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እንዲዋጃት።”
“በሥራ መሣሪያ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ልጆቿ ቢወጡ።”
ወይም “ለከባድ ጉዳት።”
ወይም “ነፍስ ስለ ነፍስ።”
ወይም “ካሳ።”
ወይም “ለነፍሱ።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።