የሉቃስ ወንጌል 10:1-42

  • ኢየሱስ 70 ሰዎች ላከ (1-12)

  • ንስሐ ላልገቡ ከተሞች የተነገረ ወዮታ (13-16)

  • የተላኩት 70 ሰዎች ተመለሱ (17-20)

  • ‘ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለልጆች ገለጥክላቸው’ (21-24)

  • የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ (25-37)

  • ኢየሱስ ወደ ማርታና ማርያም ቤት ሄደ (38-42)

10  ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች 70* ሰዎችን ሾመ፤ እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱም ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።+  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።+  እንግዲህ ሂዱ! እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ።+  የገንዘብ ኮሮጆ ወይም የምግብ ከረጢት ወይም ትርፍ ጫማ አትያዙ፤+ በመንገድም ላይ ቆማችሁ ከማንም ጋር ሰላምታ አትለዋወጡ።*  ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ በቅድሚያ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ።+  በዚያም ሰላም ወዳድ ሰው ካለ ሰላማችሁ ያርፍበታል። ሰላም ወዳድ ሰው ከሌለ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል።  ለሠራተኛ ደሞዙ ስለሚገባው+ ያቀረቡላችሁን ነገር እየበላችሁና እየጠጣችሁ+ በዚያው ቤት ቆዩ።+ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ።  “በተጨማሪም ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤  እንዲሁም በዚያ ያሉትን በሽተኞች ፈውሱ፤ ደግሞም ‘የአምላክ መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቧል’ በሏቸው።+ 10  ሆኖም ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ካልተቀበሏችሁ ወደ አውራ ጎዳናዎች ወጥታችሁ እንዲህ በሉ፦ 11  ‘በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን አቧራ እንኳ ሳይቀር አራግፈንላችሁ እንሄዳለን።+ ይሁንና የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ።’ 12  እላችኋለሁ፦ በዚያ ቀን* ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል።+ 13  “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና* ተደርገው ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ማቅ ለብሰውና አመድ ላይ ተቀምጠው ንስሐ በገቡ ነበር።+ 14  ስለዚህ በፍርድ ወቅት ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 15  አንቺም ቅፍርናሆም ወደ ሰማይ ከፍ የምትዪ ይመስልሻል? በፍጹም! ወደ መቃብር* ትወርጃለሽ! 16  “እናንተን የሚሰማ ሁሉ እኔንም ይሰማል።+ እናንተን የማይቀበል ሁሉ ደግሞ እኔንም አይቀበልም። ከዚህም በላይ እኔን የማይቀበል ሁሉ የላከኝንም አይቀበልም።”+ 17  ከዚያም 70ዎቹ ደስ እያላቸው ተመልሰው “ጌታ ሆይ፣ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት።+ 18  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ።+ 19  እነሆ፣ እባቦችንና ጊንጦችን እንድትረግጡ እንዲሁም የጠላትን ኃይል ሁሉ እንድትቋቋሙ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤+ የሚጎዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። 20  ይሁን እንጂ መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”+ 21  በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች+ ሰውረህ ለትናንሽ ልጆች ስለገለጥክላቸው በይፋ አወድስሃለሁ። አዎ፣ አባት ሆይ፣ ይህ የአንተ ፈቃድ ነውና።+ 22  ሁሉንም ነገር አባቴ ሰጥቶኛል፤ ከአብ በስተቀር ወልድ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤+ እንዲሁም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም።”+ 23  ከዚያም ብቻቸውን በነበሩበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር የሚያዩ ዓይኖች ደስተኞች ናቸው።+ 24  እላችኋለሁ፣ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ አሁን የምታዩትን ነገር ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ግን አላዩም፤+ አሁን የምትሰሙትን ነገር ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሰሙም።” 25  እነሆም አንድ ሕግ አዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነስቶ “መምህር፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ?” አለው።+ 26  ኢየሱስም “በሕጉ ላይ የተጻፈው ምንድን ነው? አንተስ ምን ትረዳለህ?” አለው። 27  እሱም መልሶ “‘አምላክህን ይሖዋን* በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣* በሙሉ ኃይልህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ’፤+ እንዲሁም ‘ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ’”+ አለው። 28  ኢየሱስም “በትክክል መልሰሃል፤ ዘወትር ይህን አድርግ፤ ሕይወትም ታገኛለህ” አለው።+ 29  ሰውየው ግን ጻድቅ መሆኑን ለማሳየት ፈልጎ+ ኢየሱስን “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው። 30  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በዘራፊዎች እጅ ወደቀ፤ እነሱም ከገፈፉትና ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ሄዱ። 31  እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲወርድ ሰውየውን አየውና ራቅ ብሎ አልፎት ሄደ። 32  በተመሳሳይም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና ገለል ብሎ አልፎት ሄደ። 33  ሆኖም አንድ ሳምራዊ+ በዚያ መንገድ ሲጓዝ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ በጣም አዘነለት። 34  ስለሆነም ወደ ሰውየው ቀርቦ በቁስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ በጨርቅ አሰረለት። ከዚያም በራሱ አህያ ላይ ካስቀመጠው በኋላ ወደ አንድ የእንግዶች ማረፊያ በመውሰድ ተንከባከበው። 35  በማግስቱ ሁለት ዲናር* አውጥቶ ለእንግዶች ማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠውና ‘ይህን ሰው አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውን ተጨማሪ ወጪ ሁሉ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው። 36  ታዲያ ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ+ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” 37  እሱም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” አለ።+ ከዚያም ኢየሱስ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።+ 38  እየተጓዙም ሳሉ ወደ አንድ መንደር ገባ። በዚያም ማርታ+ የምትባል አንዲት ሴት በቤቷ በእንግድነት ተቀበለችው። 39  እሷም ማርያም የምትባል እህት ነበረቻት፤ ማርያምም በጌታ እግር ሥር ተቀምጣ የሚናገረውን* ታዳምጥ ነበር። 40  ማርታ ግን በብዙ ሥራ ተጠምዳ ትባክን ነበር። በመሆኑም ወደ እሱ መጥታ “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? መጥታ እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው። 41  ጌታም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ደግሞም ትጠበቢያለሽ። 42  ይሁንና የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው። ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ* መርጣለች፤+ ይህም ከእሷ አይወሰድም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

በእጅ የተጻፉ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎች “ሰባ ሁለት” ይላሉ።
ወይም “ማንንም እያቀፋችሁ ሰላም አትበሉ።”
የፍርድን ቀን ያመለክታል።
እነዚህ የአይሁዳውያን ከተሞች አልነበሩም።
ወይም “ሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቃሉን።”
ወይም “የተሻለውን ድርሻ።”