ዘዳግም 29:1-29

  • በሞዓብ ምድር የተገባው ቃል ኪዳን (1-13)

  • አለመታዘዝን አስመልክቶ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (14-29)

    • የተሰወሩና የተገለጡ ነገሮች (29)

29  ይሖዋ በኮሬብ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ ሙሴ በሞዓብ ምድር ከእነሱ ጋር እንዲገባ ያዘዘው ቃል ኪዳን ቃላት እነዚህ ናቸው።+  ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን በሙሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ሁሉ እንዲሁም በመላ ምድሩ ላይ ያደረገውን ነገር ሁሉ በገዛ ዓይናችሁ ተመልክታችኋል፤+  ደግሞም እነዚያን ታላላቅ የፍርድ እርምጃዎች፣* ድንቅ ምልክቶችና ተአምራት+ በዓይናችሁ አይታችኋል።  ሆኖም ይሖዋ እስከ ዛሬ ድረስ የሚያስተውል ልብ፣ የሚያይ ዓይንና የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።+  ‘በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት+ በመራኋችሁ ጊዜ ልብሳችሁ ላያችሁ ላይ አላለቀም፤ ጫማችሁም እግራችሁ ላይ አላለቀም።+  እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን ታውቁ ዘንድ ዳቦ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም።’  በኋላም ወደዚህ ስፍራ መጣችሁ፤ የሃሽቦን ንጉሥ ሲሖን+ እና የባሳን ንጉሥ ኦግ+ ሊወጉን ወጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።+  ከዚያም ምድራቸውን ወስደን ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው።+  በመሆኑም የምታደርጉት ነገር ሁሉ መልካም እንዲሆንላችሁ የዚህን ቃል ኪዳን ቃላት ጠብቁ፤ ደግሞም ታዘዙ።+ 10  “እናንተ ሁላችሁ ይኸውም የየነገዶቻችሁ መሪዎች፣ ሽማግሌዎቻችሁ፣ አለቆቻችሁና በእስራኤል ያለ ወንድ ሁሉ በዛሬው ዕለት በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት ቆማችኋል፤ 11  እንዲሁም ልጆቻችሁ፣ ሚስቶቻችሁና+ ከእንጨት ለቃሚዎቻችሁ አንስቶ እስከ ውኃ ቀጂዎቻችሁ ድረስ፣ በሰፈራችሁ የሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎች+ ሁሉ በፊቱ ቆመዋል። 12  አሁን እዚህ የተገኘኸው አምላክህ ይሖዋ በዛሬው ዕለት ከአንተ ጋር ወደሚገባው ይኸውም በመሐላ ወደሚያጸናው ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቃል ኪዳን እንድትገባ ነው፤+ 13  ይህም ለአንተ ቃል በገባውና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣+ ለይስሐቅና+ ለያዕቆብ+ በማለላቸው መሠረት በዛሬው ዕለት አንተን ሕዝቡ አድርጎ+ ያጸናህ እንዲሁም አምላክህ ይሆን ዘንድ+ ነው። 14  “እኔ አሁን ይህን ቃል ኪዳን የምገባውም ሆነ ይህን መሐላ የምምለው ለእናንተ ብቻ አይደለም፤ 15  ከዚህ ይልቅ በዛሬው ዕለት በይሖዋ ፊት አብረውን ለቆሙትና በዚህ ዕለት ከእኛ ጋር ለሌሉት ጭምር ነው። 16  (በግብፅ እንዴት እንኖር እንደነበረና በጉዟችንም ላይ የተለያዩ ብሔራትን እንዴት አቋርጠን እንዳለፍን በሚገባ ታውቃላችሁና።+ 17  በመካከላቸው የነበሩትን የሚያስጠሉ ነገሮች እንዲሁም ከእንጨት፣ ከድንጋይ፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸውንም*+ አይታችኋል።) 18  የእነዚያን ብሔራት አማልክት ለማገልገል ከአምላካችን ከይሖዋ ልቡ የሚሸፍት+ ወንድ ወይም ሴት ወይም ቤተሰብ አሊያም ነገድ በዛሬው ዕለት በመካከላችሁ እንዳይገኝ እንዲሁም መርዛማና መራራ ፍሬ የሚያፈራ ሥር በመካከላችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ።+ 19  “አንድ ሰው ይህን የመሐላ ቃል ቢሰማና በመንገዱ ላይ ያገኘውን ሁሉ* ጠራርጎ ለማጥፋት በማሰብ ‘እንዳሻኝ ብሆን እንኳ በሰላም እኖራለሁ’ እያለ በልቡ ቢኩራራ 20  ይሖዋ ይቅር ሊለው ፈቃደኛ አይሆንም።+ ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ታላቅ ቁጣ በዚያ ሰው ላይ ይነድዳል፤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉት እርግማኖች በሙሉ ይወርዱበታል፤+ ይሖዋም የዚህን ሰው ስም ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21  ከዚያም በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው በቃል ኪዳኑ እርግማን ሁሉ መሠረት ይሖዋ ከሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ እሱን ለጥፋት ይለየዋል። 22  “መጪው የልጆቻችሁ ትውልድና ከሩቅ ምድር የሚመጡት የባዕድ አገር ሰዎች በምድሪቱ ላይ የወረዱትን መቅሰፍቶች ይኸውም ይሖዋ በላይዋ ላይ ያመጣውን በሽታ 23  እንዲሁም ይሖዋ በቁጣውና በመዓቱ ሰዶምንና ገሞራን፣+ አድማህንና ጸቦይምን+ እንደገለባበጠ ሁሉ መላዋ ምድር እንዳይዘራባት፣ እንዳታቆጠቁጥ ወይም ምንም ዓይነት ተክል እንዳታበቅል የላከውን ድኝ፣ ጨውና እሳት ሲመለከቱ 24  እነሱም ሆኑ ሁሉም ብሔራት ‘ይሖዋ በዚህች ምድር ላይ እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው?+ ይህን ታላቅ ቁጣስ ምን አመጣው?’ ይላሉ። 25  ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ከግብፅ ምድር ባወጣቸው+ ጊዜ ከእነሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረሳቸው ነው።+ 26  ሄደውም ሌሎችን አማልክት ይኸውም የማያውቋቸውንና እሱ እንዲያመልኳቸው ያልፈቀደላቸውን* አማልክት አገለገሉ፤ ደግሞም ሰገዱላቸው።+ 27  ይሖዋም በዚህ መጽሐፍ ላይ የተጻፉትን እርግማኖች በሙሉ እስኪያመጣባት ድረስ ቁጣው በምድሪቱ ላይ ነደደ።+ 28  በመሆኑም ይሖዋ በታላቅ ቁጣውና በኃይለኛው ንዴቱ ከምድራቸው ላይ ነቅሎ+ አሁን ወዳሉበት ሌላ ምድር አፈለሳቸው።’+ 29  “የተሰወሩት ነገሮች የአምላካችን የይሖዋ ናቸው፤+ የተገለጡት ነገሮች ግን በዚህ ሕግ ውስጥ ያሉትን ቃላት በሙሉ እንፈጽም ዘንድ ለዘላለም የእኛና የዘሮቻችን ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ፈተናዎች።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃል በቃል “ውኃ የጠገበውን ውኃ ከተጠማው ጋር።”
ቃል በቃል “እሱ ያልመደበላቸውን።”