ዘፀአት 22:1-31

 • ለእስራኤላውያን የተሰጡ ድንጋጌዎች (1-31)

  • ከስርቆት ጋር በተያያዘ (1-4)

  • በእህል ላይ ከሚደርስ ጉዳት ጋር በተያያዘ (5, 6)

  • ካሳ ከመክፈልና ከንብረት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ (7-15)

  • ያልታጨችን ድንግል አባብሎ የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ (16, 17)

  • ከአምልኮና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ (18-31)

22  “አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅና ቢያርደው ወይም ቢሸጠው ለበሬው አምስት በሬዎችን ለበጉ ደግሞ አራት በጎችን ካሳ መክፈል አለበት።+  (“አንድ ሌባ+ ሰብሮ ሲገባ ቢያዝና ተመቶ ቢሞት ማንም ስለ እሱ በደም ዕዳ ተጠያቂ አይሆንም።  ይህ የሆነው ግን ፀሐይ ከወጣች በኋላ ከሆነ ገዳዩ በደም ዕዳ ተጠያቂ ይሆናል።) “ሌባው ካሳ መክፈል አለበት። ምንም የሚከፍለው ነገር ከሌለው ግን ለሰረቃቸው ነገሮች ካሳ እንዲከፍል እሱ ራሱ ይሸጥ።  የሰረቀው ነገር በሬም ሆነ አህያ ወይም በግ በሕይወት እንዳለ በእጁ ላይ ከተገኘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት።  “አንድ ሰው ከብቶቹን በእርሻ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ የሌላ ሰው እርሻ ውስጥ ገብተው ሲግጡ ዝም ቢላቸው ይህ ሰው ምርጥ ከሆነው ከራሱ እርሻ ወይም ምርጥ ከሆነው ከራሱ የወይን ቦታ ካሳ መክፈል አለበት።  “እሳት ተነስቶ ወደ ቁጥቋጦ ቢዛመትና ነዶዎችን ወይም ያልታጨደን እህል አሊያም አዝመራን ቢያወድም እሳቱን ያስነሳው ሰው ለተቃጠለው ነገር ካሳ መክፈል አለበት።  “አንድ ሰው ገንዘብ ወይም ንብረት እንዲያስቀምጥለት ለባልንጀራው ቢሰጠውና ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ከባልንጀራው ቤት ቢሰረቅ፣ ሌባው ከተያዘ እጥፍ አድርጎ ካሳ መክፈል አለበት።+  ሌባው ካልተያዘ ግን የቤቱ ባለቤት በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን አሳርፎ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በእውነተኛው አምላክ ፊት እንዲቀርብ መደረግ አለበት።+  አላግባብ በባለቤትነት የተያዘን ንብረት ይኸውም በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ጠፍቶ የነበረን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ‘ይህ ንብረት የእኔ ነው!’ በሚል ክርክር ቢነሳ፣ ሁለቱም ሰዎች ጉዳያቸውን በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርቡ።+ አምላክ ጥፋተኛ ነው ብሎ የሚፈርድበት ግለሰብ እጥፍ አድርጎ ለባልንጀራው ካሳ መክፈል አለበት።+ 10  “አንድ ሰው አህያ ወይም በሬ ወይም በግ አሊያም ሌላ ማንኛውንም የቤት እንስሳ ለባልንጀራው በአደራ ቢሰጥና እንስሳው ቢሞት ወይም ከባድ ጉዳት ቢደርስበት አሊያም ማንም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ 11  አደራ ተቀባዩ በባልንጀራው ንብረት ላይ እጁን እንዳላሳረፈ ለማረጋገጥ በይሖዋ ፊት ይማልለት፤ የንብረቱ ባለቤትም መሐላውን መቀበል አለበት። ያም ሰው ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም።+ 12  እንስሳው ተሰርቆበት ከሆነ ግን ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። 13  በአውሬ ተበልቶ ከሆነ ደግሞ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ ያቅርብ። አውሬ ለበላው ካሳ መክፈል አይጠበቅበትም። 14  “ሆኖም ማንኛውም ሰው ከባልንጀራው እንስሳ ቢዋስና እንስሳው ባለቤቱ በሌለበት ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ወይም ቢሞት የተዋሰው ሰው ካሳ መክፈል አለበት። 15  ጉዳቱ የደረሰው ባለቤቱ አብሮ እያለ ከሆነ ግን ካሳ መክፈል የለበትም። እንስሳው በኪራይ መልክ የተወሰደ ከሆነ የደረሰው ጉዳት በኪራዩ ዋጋ ይሸፈናል። 16  “አንድ ወንድ አንዲትን ያልታጨች ድንግል አባብሎ አብሯት ቢተኛ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስቱ ሊያደርጋት ይገባል።+ 17  የልጅቷ አባት ልጁን ለእሱ ለመስጠት ፈጽሞ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር ይህ ሰው ለደናግል የሚከፈለውን የማጫ ዋጋ መክፈል አለበት። 18  “መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ።+ 19  “ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽም ማንም ሰው ያለጥርጥር ይገደል።+ 20  “ለይሖዋ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ይገደል።+ 21  “የባዕድ አገር ሰውን አትበድል ወይም አትጨቁን፤+ ምክንያቱም እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ነበራችሁ።+ 22  “መበለቲቱን ወይም አባት የሌለውን* ልጅ አታጎሳቁሉ።+ 23  ብታጎሳቁለውና ወደ እኔ ቢጮኽ እኔ በእርግጥ ጩኸቱን እሰማለሁ፤+ 24  ቁጣዬም ይነድዳል። እናንተንም በሰይፍ እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የሌላቸው ልጆች ይሆናሉ። 25  “ከሕዝቤ መካከል አብሮህ ላለ ችግረኛ ገንዘብ ብታበድር እንደ አራጣ አበዳሪ አትሁንበት። ወለድም አትጠይቁት።+ 26  “የባልንጀራህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ልትመልስለት ይገባል።+ 27  ምክንያቱም የሚለብሰው ልብስ ይኸውም ሰውነቱ ላይ የሚጥለው ልብስ እሱ ብቻ ነው፤ አለዚያ ምን ለብሶ ይተኛል?+ እሱም ወደ እኔ በሚጮኽበት ጊዜ በእርግጥ እሰማዋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሩኅሩኅ* ነኝ።+ 28  “አምላክን አትራገም፤+ በሕዝብህ መካከል ያለውን አለቃም* አትራገም።+ 29  “ከተትረፈረፈው ምርትህና ሞልቶ ከሚፈሰው መጭመቂያህ* መባ ለማቅረብ አትሳሳ።+ የወንዶች ልጆችህን በኩር ለእኔ መስጠት አለብህ።+ 30  የበሬህንና የበግህን በኩር በተመለከተ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ይህ ነው፦+ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቆይ። በስምንተኛው ቀን ለእኔ መስጠት አለብህ።+ 31  “እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችሁ መገኘት አለባችሁ፤+ አውሬ ዘንጥሎት ሜዳ ላይ የተገኘን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ አትብሉ።+ ለውሾች ጣሉት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን።”
ወይም “ቸር።”
ወይም “ገዢም።”
የዘይትና የወይን መጭመቂያን ያመለክታል።