ዘዳግም 8:1-20

  • የይሖዋ በረከት (1-9)

    • ‘ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም’ (3)

  • አምላክህን ይሖዋን አትርሳ (10-20)

8  “በሕይወት እንድትኖሩና+ እንድትበዙ እንዲሁም ይሖዋ ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ ዛሬ የማዛችሁን እያንዳንዱን ትእዛዝ በጥንቃቄ ጠብቁ።+  አምላክህ ይሖዋ በልብህ ምን እንዳለ+ ይኸውም ትእዛዛቱን ትጠብቅ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ይፈትንህና ትሑት ያደርግህ ዘንድ+ በእነዚህ 40 ዓመታት በምድረ በዳ እንድትጓዝበት ያደረገህን ረጅሙን መንገድ አስታውስ።+  ትሑት እንድትሆን አደረገህ፤ ካስራበህም+ በኋላ አንተ የማታውቀውን፣ አባቶችህም የማያውቁትን መና መገበህ፤+ ይህን ያደረገው፣ ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር እንደማይችል ሊያሳውቅህ ነው።+  በእነዚህ 40 ዓመታት፣ የለበስከው ልብስ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም።+  አንድ ሰው ለልጁ እርማት እንደሚሰጥ ሁሉ አምላክህ ይሖዋም እርማት ይሰጥህ+ እንደነበር ልብህ በሚገባ ያውቃል።  “እንግዲህ አንተ በመንገዶቹ በመሄድና እሱን በመፍራት የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ጠብቅ።  ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ መልካም ወደሆነች ምድር ሊያስገባህ ነው፤+ ይህች ምድር ጅረቶች* ያሏት፣ በሸለቋማ ሜዳዋና በተራራማ አካባቢዋ ምንጮች የሚፈልቁባትና ውኃዎች የሚንዶለዶሉባት፣  ስንዴ፣ ገብስ፣ ወይን፣ በለስና ሮማን+ የሚበቅልባት፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት፣+  የምግብ እጥረት የሌለባት፣ ምንም ነገር የማታጣባት፣ ብረት ያለባቸው ድንጋዮች የሚገኙባት እንዲሁም ከተራሮቿ መዳብ ቆፍረህ የምታወጣባት ምድር ናት። 10  “በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ ስለሰጠህ ስለ መልካሚቱ ምድር አምላክህን ይሖዋን አመስግነው።+ 11  እኔ ዛሬ የማዝህን የእሱን ትእዛዛት፣ ድንጋጌዎችና ደንቦች ችላ በማለት አምላክህን ይሖዋን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ። 12  በልተህ ስትጠግብ፣ ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ በዚያ መኖር ስትጀምር፣+ 13  ከብትህና መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበራከት እንዲሁም የአንተ የሆነው ሁሉ እየበዛ ሲሄድ 14  ልብህ እንዳይታበይና+ ከግብፅ ምድር ይኸውም ከባርነት ቤት ያወጣህን አምላክህን ይሖዋን እንዳያስረሳህ ተጠንቀቅ፤+ 15  መርዛማ እባቦችና ጊንጦች በሞሉበት እንዲሁም ውኃ የተጠማ ደረቅ ምድር ባለበት በዚያ ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ ምድረ በዳ+ አቋርጠህ እንድታልፍ ያደረገህን አምላክህን እንዳያስረሳህ ተጠንቀቅ። እሱ ከጠንካራ ዓለት* ውኃ አፍልቆልሃል፤+ 16  እንዲሁም ወደፊት መልካም እንዲሆንልህ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን ሲል+ አባቶችህ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መግቦሃል።+ 17  በልብህም ‘ይህን ሀብት ያፈራሁት በራሴ ኃይልና በእጄ ብርታት ነው’+ ብለህ ብታስብ 18  ሀብት እንድታፈራ ኃይል የሰጠህ አምላክህ ይሖዋ መሆኑን አስታውስ፤+ ይህን ያደረገው ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ለአባቶችህ በመሐላ የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ነው።+ 19  “አምላክህን ይሖዋን ብትረሳና ሌሎች አማልክትን ብትከተል እንዲሁም እነሱን ብታገለግልና ለእነሱ ብትሰግድ፣ በእርግጥ እንደምትጠፉ እኔ ዛሬ እመሠክርባችኋለሁ።+ 20  የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ስላልሰማችሁ ይሖዋ ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው ብሔራት እናንተም እንዲሁ ትጠፋላችሁ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
ቃል በቃል “ከባልጩት ድንጋይ።”