ዘፀአት 33:1-23

  • አምላክ ሕዝቡን ገሠጸ (1-6)

  • የመገናኛ ድንኳኑ ከሰፈሩ ውጭ ተተከለ (7-11)

  • ሙሴ የይሖዋን ክብር ለማየት ጠየቀ (12-23)

33  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ መርተህ ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ተነስተህ ሂድ። ‘ለዘርህ እሰጠዋለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማልኩላቸውም ምድር ተጓዝ።+  እኔም ከአንተ አስቀድሜ መልአክ በመላክ+ ከነአናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።+  ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ ሂዱ። ሆኖም እናንተ ግትር* ሕዝብ ስለሆናችሁ+ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ+ በመካከላችሁ ሆኜ አብሬያችሁ አልሄድም።”  ሕዝቡም ይህን ኃይለኛ ንግግር ሲሰሙ በሐዘን ተዋጡ፤ ከመካከላቸውም ማንም ጌጡን አላደረገም።  ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እናንተ ግትር* ሕዝብ ናችሁ።+ ለአንድ አፍታ በመካከላችሁ አልፌ ላጠፋችሁ እችል ነበር።+ በእናንተ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እስክወስን ድረስ ጌጣጌጣችሁን አውልቁ።’”  ስለዚህ እስራኤላውያን ከኮሬብ ተራራ አንስቶ ጌጣጌጣቸውን ማድረግ ተዉ።  ሙሴም የራሱን ድንኳን ወስዶ ከሰፈሩ ውጭ ማለትም ከሰፈሩ ትንሽ ራቅ አድርጎ ተከለው፤ ድንኳኑንም የመገናኛ ድንኳን ብሎ ጠራው። ይሖዋን የሚጠይቅ+ ማንኛውም ሰው ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው የመገናኛ ድንኳን ይሄድ ነበር።  ሙሴ ወደ ድንኳኑ ሲሄድ ሕዝቡ በሙሉ ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ በመቆም ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ትክ ብለው ይመለከቱት ነበር።  ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ አምላክ ከሙሴ ጋር በሚነጋገርበት+ ጊዜ የደመናው ዓምድ+ ወርዶ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ይቆማል። 10  ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሞ ሲመለከት እያንዳንዳቸው ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ ይሰግዱ ነበር። 11  አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር።+ ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበት ጊዜ አገልጋዩና ረዳቱ+ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ+ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። 12  ሙሴም ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ‘ይህን ሕዝብ ምራ’ እያልከኝ ነው፤ ሆኖም ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አላሳወቅከኝም። ከዚህም በላይ ‘በስም አውቄሃለሁ፤* ደግሞም በፊቴ ሞገስ አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። 13  እባክህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ።+ እንዲሁም ይህ ብሔር ሕዝብህ እንደሆነ አስብ።”+ 14  በመሆኑም እሱ “እኔ ራሴ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤*+ እረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው።+ 15  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ ከእኛ ጋር የማትሄድ* ከሆነ ይህን ቦታ ለቅቀን እንድንሄድ አታድርገን። 16  ታዲያ እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘን የሚታወቀው እንዴት ነው? እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በምድር ላይ ካሉ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየን እንድንሆን+ ስትል አብረኸን በመሄድህ አይደለም?”+ 17  ይሖዋም ሙሴን “በፊቴ ሞገስ ስላገኘህና በስም ስላወቅኩህ የጠየቅከውን ይህን ነገር እፈጽማለሁ” አለው። 18  እሱም በዚህ ጊዜ “እባክህ ክብርህን አሳየኝ” አለው። 19  ሆኖም እሱ እንዲህ አለው፦ “እኔ ራሴ ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሜን በፊትህ አውጃለሁ።+ ሞገስ ላሳየው የምፈልገውን ሞገስ አሳየዋለሁ፤ ልምረው የምፈልገውን ደግሞ እምረዋለሁ።”+ 20  ሆኖም “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” አለው። 21  በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “ይኸው አጠገቤ ቦታ አለ። አንተም በዓለቱ ላይ ቁም። 22  ክብሬ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ በዓለቱ ዋሻ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፤ እስከማልፍም ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ። 23  ከዚያም እጄን አነሳለሁ፤ አንተም ጀርባዬን ታያለህ። ፊቴ ግን አይታይም።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ቃል በቃል “አንገተ ደንዳና።”
ወይም “መርጬሃለሁ።”
ቃል በቃል “ፊቴ ከአንተ ጋር ይሄዳል።”
ቃል በቃል “ፊትህ ከእኛ ጋር የማይሄድ።”