መክብብ 9:1-18

  • “ፍጻሜያቸው ተመሳሳይ ነው” (1-3)

  • ከመሞትህ በፊት በሕይወትህ ተደሰት (4-12)

    • ‘ሙታን ምንም አያውቁም’ (5)

    • በመቃብር ምንም ሥራ የለም (10)

    • “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” (11)

  • ጥበብ የሚናቅበት ጊዜ አለ (13-18)

9  ስለዚህ ይህን ሁሉ በጥሞና ተመልክቼ ጻድቃንም ሆኑ ጥበበኞች እንዲሁም የሚያከናውኗቸው ሥራዎች በእውነተኛው አምላክ እጅ ናቸው ብዬ ደመደምኩ።+ ሰዎች ከእነሱ በፊት በነበረው ዘመን የታየውን ፍቅርና ጥላቻ አያውቁም።  ጻድቁና ክፉው ሰው፣+ ጥሩው ሰውም ሆነ ንጹሕ የሆነውና ንጹሕ ያልሆነው ሰው፣ መሥዋዕት የሚያቀርቡትም ሆኑ የማያቀርቡት ፍጻሜያቸው* ተመሳሳይ ነው።+ ጥሩው ሰው ከኃጢአተኛው ጋር አንድ ነው፤ የሚምለውም ሰው፣ ላለመማል ከሚጠነቀቀው ሰው ጋር አንድ ነው።  ከፀሐይ በታች የሚፈጸመው አስጨናቂ ነገር ይህ ነው፦ የሁሉም ፍጻሜ* አንድ ስለሆነ+ የሰዎችም ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወታቸው ዘመን በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ ከዚያም ይሞታሉ!*   በሕያዋን መካከል ያለ ማንኛውም ሰው ተስፋ አለው፤ ምክንያቱም በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል።+  ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤+ ሙታን ግን ምንም አያውቁም፤+ ከእንግዲህም የሚያገኙት ብድራት* የለም፤ ምክንያቱም የሚታወሱበት ነገር ሁሉ ተረስቷል።+  በተጨማሪም ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ጠፍቷል፤ ከዚህም በኋላ ከፀሐይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ ፈጽሞ ድርሻ አይኖራቸውም።+  ሂድ፣ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ልብህም ደስ ብሎት የወይን ጠጅህን ጠጣ፤+ እውነተኛው አምላክ በሥራህ ደስ ተሰኝቷልና።+  ልብስህ ምንጊዜም ነጭ* ይሁን፤ ራስህንም ዘይት መቀባት አትዘንጋ።+  አምላክ ከፀሐይ በታች በሰጠህ ከንቱ በሆነው የሕይወት ዘመንህ ሁሉ፣ ከንቱ በሆነውም ዕድሜህ ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ተደስተህ ኑር፤+ በሕይወትህ እንዲሁም ከፀሐይ በታች በምትደክምበትና በትጋት በምታከናውነው ሥራ ዕጣ ፋንታህ* ይህ ነውና።+ 10  እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን፤ አንተ በምትሄድበት በመቃብር* ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።+ 11  እኔም ከፀሐይ በታች ሌላ ነገር ተመለከትኩ፤ ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም፤+ ጥበበኞች ሁልጊዜ ምግብ አያገኙም፤ አስተዋዮች ሁልጊዜ ሀብት አያገኙም፤+ እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤+ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች* ያጋጥሟቸዋል። 12  ሰው የራሱን ጊዜ አያውቅምና።+ ዓሣዎች በአደገኛ መረብ እንደሚጠመዱና ወፎች በወጥመድ እንደሚያዙ፣ የሰው ልጆችም ድንገት በሚያጋጥማቸው ክፉ ጊዜ* ይጠመዳሉ። 13  ደግሞም ከፀሐይ በታች ስላለች ጥበብ ይህን አስተዋልኩ፤ በእሷም እጅግ ተገረምኩ፦ 14  ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኃያል ንጉሥም መጥቶ ከበባት፤ በዙሪያዋም ትልቅ ቅጥር ገነባ። 15  በከተማዋ ውስጥ ጥበበኛ የሆነ አንድ ድሃ ሰው ነበር፤ እሱም በጥበቡ ከተማዋን አዳናት። ሆኖም ይህን ድሃ ማንም ሰው አላስታወሰውም።+ 16  እኔም ለራሴ እንዲህ አልኩ፦ ‘ጥበብ ከኃይል ትበልጣለች፤+ ይሁንና የድሃው ጥበብ ተናቀ፤ የተናገረውም ነገር ሰሚ አላገኘም።’+ 17  ሞኞችን የሚገዛ ሰው ከሚያሰማው ጩኸት ይልቅ ጥበበኞች በዝግታ የሚናገሩትን ቃል መስማት ይሻላል። 18  ከጦር መሣሪያ ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካም ነገርን ሊያጠፋ ይችላል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዕጣ ፋንታቸው።”
ወይም “ዕጣ ፋንታ።”
ቃል በቃል “ከዚያም በኋላ፣ ወደ ሙታን!”
ወይም “ደሞዝ።”
ነጭ ልብስ መልበስ የደስተኝነትን መንፈስ ያንጸባርቃል፤ የሐዘን ልብስ አይደለም።
ወይም “ድርሻህ።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ያልታሰቡ ገጠመኞች።”
ወይም “የአደጋ ጊዜ።”