ሁለተኛ ነገሥት 1:1-18

  • ኤልያስ፣ አካዝያስ እንደሚሞት ትንቢት ተናገረ (1-18)

1  አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ+ በእስራኤል ላይ ዓመፀ።  በዚህ ወቅት አካዝያስ በሰማርያ በሚገኘው ቤቱ ሰገነት ላይ ካለው ክፍል በርብራቡ ሾልኮ በመውደቁ ጉዳት ደርሶበት ነበር። በመሆኑም “ከደረሰብኝ ጉዳት እድን እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ እንድችል ሄዳችሁ የኤቅሮንን+ አምላክ ባአልዜቡብን ጠይቁልኝ” በማለት መልእክተኞች ላከ።+  የይሖዋ መልአክ ግን ቲሽባዊውን ኤልያስን*+ እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለማግኘት ውጣ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው?+  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።”’” ከዚያም ኤልያስ ሄደ።  መልእክተኞቹ ወደ እሱ ተመልሰው ሲመጡ አካዝያስ “ለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” አላቸው።  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛን ለማግኘት የመጣ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም እንዲህ አለን፦ ‘ሂዱ፣ ወደላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኛ የምትልከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’”’”+  በዚህ ጊዜ አካዝያስ “እናንተን ለማግኘት የመጣውና ይህን የነገራችሁ ሰው ምን ይመስላል?” ብሎ ጠየቃቸው።  እነሱም “ሰውየው ፀጉራም ልብስ የለበሰ+ ሲሆን ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ታጥቋል”+ አሉት። እሱም ወዲያውኑ “ይሄማ ቲሽባዊው ኤልያስ ነው” አለ።  ከዚያም ንጉሡ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሃምሳ አለቃው ወደ እሱ ሲወጣ ኤልያስ ተራራው አናት ላይ ተቀምጦ ነበር። ሃምሳ አለቃውም “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣+ ንጉሡ ‘ና ውረድ’ ብሎሃል” አለው። 10  ኤልያስ ግን ሃምሳ አለቃውን “እኔ የአምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ+ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ። 11  በመሆኑም ንጉሡ እንደገና ሌላ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ወደ ኤልያስ ላከ። እሱም ሄዶ ኤልያስን “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ ንጉሡ ‘ና ፈጥነህ ውረድ’ ብሎሃል” አለው። 12  ኤልያስ ግን “እኔ የእውነተኛው አምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አላቸው። ከዚያም የአምላክ እሳት ከሰማይ ወርዶ እሱንና 50ዎቹን ሰዎች በላ። 13  ከዚያም ንጉሡ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ አንድ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር ላከ። ሆኖም ሦስተኛው ሃምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ ሰገደ፤ ሞገስ እንዲያሳየውም እየለመነ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ እባክህ የእኔም ሕይወት ሆነ የእነዚህ 50 አገልጋዮችህ ሕይወት በፊትህ የከበረ ይሁን።* 14  ከዚህ በፊት እሳት ከሰማይ ወርዶ ሁለቱን ሃምሳ አለቆችና አብረዋቸው የነበሩትን ሃምሳ ሃምሳ ሰዎች በልቷል፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን።” 15  በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ ኤልያስን “አብረኸው ውረድ። አትፍራው” አለው። በመሆኑም ኤልያስ ተነስቶ አብሮት ወደ ንጉሡ ወረደ። 16  ከዚያም ኤልያስ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የኤቅሮንን+ አምላክ ባአልዜቡብን ለመጠየቅ መልእክተኞች ልከሃል። ይህን ያደረግከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነው?+ ለምን የእስራኤልን አምላክ አልጠየቅክም? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም፤ በእርግጥ ትሞታለህ።’” 17  በመሆኑም ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ሞተ፤ አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው ኢዮራም*+ በምትኩ ነገሠ፤ ይህ የሆነው የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ኢዮራም በነገሠ+ በሁለተኛው ዓመት ነው። 18  የቀረው የአካዝያስ+ ታሪክ፣ ያደረገው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም?

የግርጌ ማስታወሻዎች

“አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የእኔም ነፍስ ሆነች የእነዚህ 50 አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።”
የአካዝያስን ወንድም ያመለክታል።