ዘዳግም 26:1-19

  • የፍሬ በኩራትን መባ አድርጎ ማቅረብ (1-11)

  • ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጥ አሥራት (12-15)

  • እስራኤል የይሖዋ ልዩ ንብረት ነው (16-19)

26  “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርጎ የሚሰጥህን ምድር ገብተህ ስትወርስና በዚያ መኖር ስትጀምር  አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ይኸውም ምድሪቱ ከምታፈራው ፍሬ ሁሉ በኩር የሆነውን ወስደህ በቅርጫት ውስጥ በማድረግ አምላክህ ይሖዋ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ ይዘህ ሂድ።+  በወቅቱ ወደሚያገለግለው ካህን ሄደህ ‘ይሖዋ ለእኛ ለመስጠት ለአባቶቻችን ወደማለላቸው ምድር መግባቴን ዛሬ ለአምላክህ ለይሖዋ አሳውቃለሁ’ በለው።+  “ከዚያም ካህኑ ቅርጫቱን ከእጅህ ላይ ወስዶ በአምላክህ በይሖዋ መሠዊያ ፊት ያስቀምጠዋል።  አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ‘አባቴ ዘላን* አራማዊ+ ነበር፤ እሱም ወደ ግብፅ ወርዶ+ በቁጥር አነስተኛ ከሆነው ቤተሰቡ+ ጋር የባዕድ አገር ሰው ሆኖ መኖር ጀመረ። ሆኖም በዚያ ሲኖር ኃያልና ቁጥሩ የበዛ ታላቅ ብሔር ሆነ።+  ግብፃውያንም ክፉኛ ያንገላቱንና ይጨቁኑን እንዲሁም በላያችን ላይ ከባድ የባርነት ቀንበር ይጭኑብን ነበር።+  እኛም ወደ አባቶቻችን አምላክ ወደ ይሖዋ ጮኽን፤ ይሖዋም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጉስቁልናችንን፣ መከራችንንና የደረሰብንን ጭቆናም ተመለከተ።+  በመጨረሻም ይሖዋ በኃያል እጅና በተዘረጋ ክንድ፣+ አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ እንዲሁም ድንቅ ምልክቶችን በማሳየትና ተአምራትን በመፈጸም ከግብፅ አወጣን።+  ከዚያም ወደዚህ ስፍራ አምጥቶ ይህችን ምድር ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ሰጠን።+ 10  ይኸው አሁን ይሖዋ የሰጠኝ ምድር ካፈራችው ፍሬ በኩር የሆነውን አምጥቻለሁ።’+ “ይህን በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስቀምጠው፤ አንተም በአምላክህ በይሖዋ ፊት ስገድ። 11  ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው የባዕድ አገር ሰው አምላክህ ይሖዋ ለአንተና ለቤተሰብህ በሰጠው መልካም ነገር ሁሉ ትደሰታላችሁ።+ 12  “የአሥራት ዓመት በሆነው በሦስተኛው ዓመት የምርትህን አንድ አሥረኛ አሥራት+ እንዲሆን ለይተህ ካስቀመጥክ በኋላ ለሌዋዊው፣ ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው* ልጅና ለመበለቲቱ ትሰጣለህ፤ እነሱም በከተሞችህ* ውስጥ እስኪጠግቡ ድረስ ይበሉታል።+ 13  ከዚያም በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንዲህ ትላለህ፦ ‘በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት ቅዱስ የሆነውን ነገር ከቤት አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለባዕድ አገሩ ሰው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለመበለቲቱ+ ሰጥቻለሁ። ትእዛዛትህን አልጣስኩም ወይም ችላ አላልኩም። 14  ሐዘን ላይ በተቀመጥኩበት ጊዜ ከእሱ አልበላሁም፤ ወይም ረክሼ ባለሁበት ጊዜ ከእሱ ላይ ምንም ነገር አላነሳሁም፤ አሊያም ለሞተ ሰው ከእሱ ላይ ምንም ነገር አልሰጠሁም። የአምላኬን የይሖዋን ቃል ታዝዣለሁ፤ ያዘዝከኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ። 15  እንግዲህ አሁን ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማያት ሆነህ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በማልክላቸው መሠረት+ የሰጠኸንን ምድር ይኸውም ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ባርክ።’+ 16  “አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች እንድትጠብቅ ዛሬ ያዝሃል። አንተም በሙሉ ልብህና+ በሙሉ ነፍስህ* ፈጽማቸው፤ ጠብቃቸውም። 17  ይሖዋ በመንገዶቹ ከሄድክ እንዲሁም ሥርዓቶቹን፣+ ትእዛዛቱንና+ ድንጋጌዎቹን+ ከጠበቅክና ቃሉን ከሰማህ አምላክህ እንደሚሆን ዛሬ ነግሮሃል። 18  አንተም ይሖዋ ቃል በገባልህ መሠረት ሕዝቡ ማለትም ልዩ ንብረቱ*+ እንደምትሆንና ትእዛዛቱን በሙሉ እንደምትጠብቅ የተናገርከውን ቃል በዛሬው ዕለት ሰምቷል፤ 19  አንተ ለአምላክህ ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ+ ሆነህ ስትገኝ እሱ ደግሞ በገባው ቃል መሠረት ውዳሴ፣ ዝናና ክብር በማጎናጸፍ፣ ከፈጠራቸው ሌሎች ብሔራት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ሊጠፋ የሚችል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በደጆችህ።”
ወይም “ወላጅ አልባ ለሆነው።”
ወይም “ውድ ሀብቱ።”