ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 6:1-18
6 ወንድሞች፣ አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት* መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።+ ይሁንና አንተም ፈተና ላይ እንዳትወድቅ+ ለራስህ ተጠንቀቅ።+
2 አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤+ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።+
3 አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ+ ራሱን እያታለለ ነው።
4 ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤+ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር+ ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።
5 እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማልና።+
6 ከዚህም በተጨማሪ ቃሉን በመማር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ይህን ትምህርት* ከሚያስተምረው ሰው ጋር መልካም ነገሮችን ሁሉ ይካፈል።+
7 አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤+
8 ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል፤ ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል።+
9 ካልታከትን* ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።+
10 እንግዲያው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ* እስካገኘን ድረስ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ።
11 በራሴ እጅ እንዴት ባሉ ትላልቅ ፊደላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ።
12 በሥጋ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ* እንድትገረዙ ሊያስገድዷችሁ ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በክርስቶስ የመከራ እንጨት* ሳቢያ ስደት እንዳይደርስባቸው ነው።
13 እነሱ እንድትገረዙ የሚፈልጉት በእናንተ ሥጋ ለመኩራራት ብለው ነው እንጂ የተገረዙት ራሳቸውም እንኳ ሕጉን አይጠብቁም።+
14 ይሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ እንጨት* ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ፈጽሞ መኩራራት አልፈልግም፤+ በእሱ የተነሳ፣ በእኔ አመለካከት ዓለም ሞቷል፤* በዓለም አመለካከት ደግሞ እኔ ሞቻለሁ።*
15 መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤+ ከዚህ ይልቅ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።+
16 ይህን የሥነ ምግባር ደንብ በመከተል በሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ይኸውም በአምላክ እስራኤል+ ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።
17 የኢየሱስ ባሪያ መሆኔን የሚያሳይ መለያ ምልክት በሰውነቴ ላይ ስላለ+ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።
18 ወንድሞች፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን። አሜን።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ይህን የቃል ትምህርት።”
^ ወይም “ተስፋ ካልቆረጥን።”
^ ቃል በቃል “የተቀጠረ ጊዜ።”
^ ወይም “ከውጭ ሲያዩአቸው ጥሩ መስለው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅሏል።”
^ ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅያለሁ።”