ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-23

  • ሰላምታ (1, 2)

  • መንፈሳዊ በረከት (3-7)

  • ሁሉንም ነገር በክርስቶስ አንድ ላይ መጠቅለል (8-14)

    • በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ የሚቋቋም “አስተዳደር” (10)

    • በመንፈስ መታተም፣ “አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ” (13, 14)

  • ጳውሎስ በኤፌሶን ክርስቲያኖች እምነት የተነሳ አምላክን አመሰገነ (15-23)

1  በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ በኤፌሶን+ ላሉ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን፦  አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት* ሁሉ ስለባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤+  በእሱ ፊት ፍቅር እንድናሳይ እንዲሁም ቅዱሳንና እንከን የለሽ ሆነን እንድንገኝ+ ዓለም ከመመሥረቱ* በፊት ከክርስቶስ ጋር አንድ እንድንሆን መርጦናልና።  ደግሞም እሱ እንደወደደና እንደ በጎ ፈቃዱ+ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የገዛ ራሱ ልጆች አድርጎ ሊወስደን+ አስቀድሞ ወስኗል፤+  ይኸውም በተወደደው ልጁ+ አማካኝነት በደግነት ለእኛ በሰጠው ክቡር በሆነው ጸጋው+ የተነሳ እንዲወደስ ነው።  በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት በልጁ ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤+ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል።+  ጸጋውንም ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ ጋር አትረፍርፎ ሰጥቶናል፤  ይህን ያደረገው የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ በማሳወቅ ነው።+ ይህ ሚስጥር ደግሞ እሱ ራሱ ካሰበው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው፤ 10  ዓላማውም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ አንድ አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው።+ አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች ይሰበሰባሉ፤ 11  እኛም ከእሱ ጋር አንድነት ያለን ሲሆን ወራሾች እንድንሆንም ተመርጠናል፤+ ምክንያቱም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሁሉንም ነገር በወሰነው መንገድ የሚያከናውነው እሱ ከዓላማው ጋር በሚስማማ ሁኔታ አስቀድሞ መርጦናል፤ 12  ይህም የሆነው በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ አምላክን ከፍ ከፍ እንድናደርግና እንድናወድስ ነው። 13  ይሁንና እናንተም የእውነትን ቃል ማለትም ስለ መዳናችሁ የሚገልጸውን ምሥራች ከሰማችሁ በኋላ በእሱ ተስፋ አድርጋችኋል። ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤+ 14  ይህም ለአምላክ ታላቅ ምስጋና ያስገኝ ዘንድ የራሱ ንብረት+ የሆኑትን በቤዛ+ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ* ነው።+ 15  ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነት እንዲሁም ለቅዱሳን ሁሉ ስለምታሳዩት ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ 16  ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረቤን አላቋረጥኩም። ወደፊትም ስለ እናንተ መጸለዬን እቀጥላለሁ፤ 17  የክብር አባት የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለ እሱ ትክክለኛ እውቀት ስትቀስሙ የጥበብ መንፈስ እንዲሰጣችሁና እሱ የሚገልጣቸውን ነገሮች መረዳት እንድትችሉ እጸልያለሁ።+ 18  የልባችሁ ዓይኖች እንዲበሩ አድርጓል፤ ይህን ያደረገው ለምን ዓይነት ተስፋ እንደጠራችሁ እንድታውቁ፣ ለቅዱሳን ውርሻ አድርጎ የሚሰጠው ታላቅ ብልጽግና ምን እንደሆነ እንድትረዱ+ 19  እንዲሁም ታላቅ ኃይሉ ለእኛ ለምናምነው ምን ያህል የላቀ እንደሆነ እንድታውቁ ነው።+ የዚህ ኃይል ታላቅነት፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነው ብርታቱ በሚያከናውነው ሥራ ታይቷል፤ 20  ክርስቶስን ከሞት ባስነሳውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ባስቀመጠው+ ጊዜ ይህን ኃይሉን ተጠቅሟል፤ 21  በዚህ ሥርዓት* ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ጭምር ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት እንዲሁም ከተሰየመው ከየትኛውም ስም በላይ እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።+ 22  በተጨማሪም ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛለት፤+ ከጉባኤው ጋር በተያያዘም በሁሉ ነገር ላይ ራስ አደረገው፤+ 23  ጉባኤው የእሱ አካል+ ከመሆኑም በላይ በእሱ የተሞላ ነው፤ እሱ ደግሞ ሁሉንም ነገር በሁሉ የሚሞላ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አምላክ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት በሰጠን በረከት።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “ቀብድ፤ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ዋስትና (መያዣ)።”
ወይም “በዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።