በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 134

ባዶ መቃብር—ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

ባዶ መቃብር—ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

ማቴዎስ 28:3-15 ማርቆስ 16:5-8 ሉቃስ 24:4-12 ዮሐንስ 20:2-18

  • ኢየሱስ ከሞት ተነሳ

  • የኢየሱስ መቃብር ጋ ያጋጠሙ ነገሮች

  • ኢየሱስ ለተለያዩ ሴቶች ተገለጠ

ሴቶቹ መቃብሩን ባዶ ሆኖ ሲያገኙት ምንኛ ደንግጠው ይሆን! መግደላዊቷ ማርያም “ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር” ይኸውም ወደ ሐዋርያው ዮሐንስ እየሮጠች ሄደች። (ዮሐንስ 20:2) መቃብሩ ቦታ የቀሩት ሌሎቹ ሴቶች ግን አንድ መልአክ አዩ። በመቃብሩ ውስጥ ደግሞ “ነጭ ልብስ የለበሰ” ሌላ መልአክ አለ።—ማርቆስ 16:5

ከመላእክቱ አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ። አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም። ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ። ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። . . .’ በሏቸው።” (ማቴዎስ 28:5-7) ስለዚህ ሴቶቹ “በአድናቆት ተውጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ” ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።—ማርቆስ 16:8

በዚህ ጊዜ ማርያም፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አግኝታቸዋለች። ትንፋሿ እየተቆራረጠ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። (ዮሐንስ 20:2) ጴጥሮስና ዮሐንስም ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ መሮጥ ጀመሩ። ዮሐንስ ፈጣን በመሆኑ መቃብሩ ጋ ቀድሞ ደረሰ። ዮሐንስ ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት የበፍታ ጨርቆቹን አየ፤ ወደ ውስጥ ግን አልገባም።

ጴጥሮስ ግን መቃብሩ ጋ ሲደርስ ሰተት ብሎ ወደ ውስጥ ገባ። በዚያም የበፍታ ጨርቆቹንና የኢየሱስ ራስ የተሸፈነበትን ጨርቅ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም ወደ ውስጥ ገባ፤ ማርያም የነገረችውንም አመነ። ኢየሱስ አስቀድሞ የነገራቸው ቢሆንም አንዳቸውም ከሞት እንደተነሳ አልገባቸውም። (ማቴዎስ 16:21) በነገሩ ግራ ተጋብተው ወደ ቤት ተመለሱ። ወደ መቃብሩ ቦታ ተመልሳ የመጣችው ማርያም ግን እዚያው ቆየች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎቹ ሴቶች ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ። መንገድ ላይ እያሉ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!”  አላቸው። እነሱም እግሩ ላይ ወድቀው “ሰገዱለት።” ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው።—ማቴዎስ 28:9, 10

ቀደም ሲል የምድር መናወጥ ሲከሰትና መላእክቱ ሲገለጡ መቃብሩ ጋ የነበሩት ወታደሮች ‘ተንቀጥቅጠው፣ እንደ በድን ሆነው’ ነበር። ድንጋጤያቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው “ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው።” የካህናት አለቆቹም ከአይሁድ ሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩ። ከዚያም ወታደሮቹ ጉዳዩን በሚስጥር እንዲይዙትና “ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት” ብለው እንዲናገሩ ለማድረግ ጉቦ ሊሰጧቸው ወሰኑ።—ማቴዎስ 28:4, 11, 13

ሮማውያን ወታደሮች በጥበቃ ሥራ ላይ እያሉ ካንቀላፉ በሞት ሊቀጡ ይችላሉ፤ በመሆኑም ካህናቱ “አትጨነቁ፤ ወሬው [ስለ መተኛታቸው የሚናገሩት ውሸት] ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን” ብለው ቃል ገቡላቸው። (ማቴዎስ 28:14) ወታደሮቹ ጉቦውን ተቀብለው ካህናቱ እንዳሏቸው አደረጉ። በዚህም ምክንያት የኢየሱስ አስከሬን እንደተሰረቀ የሚገልጸው የሐሰት ወሬ በአይሁዳውያን መካከል በስፋት ተሰራጨ።

በዚህ ወቅት መግደላዊቷ ማርያም መቃብሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች ነው። ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ ስትል ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አየች! የኢየሱስ አስከሬን አርፎበት በነበረው ቦታ አንዱ በራስጌው ሌላው በግርጌው ተቀምጠዋል። እነሱም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። ማርያምም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” በማለት መለሰች። ከዚያም ዞር ስትል አንድ ሰው አየች። እሱም መላእክቱ ያቀረቡላትን ጥያቄ ከጠየቃት በኋላ አክሎ “የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። እሷም አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው።—ዮሐንስ 20:13-15

ማርያም እያነጋገረች ያለችው ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ነው፤ በዚያ ወቅት ግን ይህን አልተገነዘበችም። ይሁንና ኢየሱስ “ማርያም!” ሲላት አወቀችው፤ ማንነቱን ያወቀችው ሌላ ጊዜ በሚያናግራት መንገድ ስለጠራት ነው። በዚህ ጊዜ በደስታ “ራቦኒ!” አለችው (ትርጉሙም “መምህር!” ማለት ነው)። ማርያም ወደ ሰማይ ሊያርግ እንደሆነ ስለተሰማት ያዘችው። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።”—ዮሐንስ 20:16, 17

በዚህ ጊዜ ማርያም፣ ሐዋርያት ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ወደተሰበሰቡበት ቦታ እየሮጠች ሄደች። ከዚያም “ጌታን አየሁት!” አለቻቸው፤ እሷ የተናገረችው ነገር ቀደም ሲል ከሌሎቹ ሴቶች የሰሙትን የሚያጠናክር ነው። (ዮሐንስ 20:18) ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ፣ ሴቶቹ ‘እንዲሁ የሚቀባጥሩ መሰላቸው።’—ሉቃስ 24:11