በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 17

ኒቆዲሞስን በምሽት አስተማረ

ኒቆዲሞስን በምሽት አስተማረ

ዮሐንስ 2:23–3:21

  • ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ተወያየ

  • ‘ዳግመኛ መወለድ’ ያለው ትርጉም

ኢየሱስ በ30 ዓ.ም. በተከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት ኢየሩሳሌም መጥቶ እያለ አስደናቂ ምልክቶች ወይም ተአምራት ፈጸመ። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች በእሱ አመኑ። ሳንሄድሪን የተባለው የአይሁድ ከፍተኛ ሸንጎ አባል የሆነው ፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ በዚህ በጣም ተደነቀ። ይበልጥ ለማወቅ ስለፈለገም ከመሸ በኋላ ወደ ኢየሱስ ሄደ፤ ምናልባትም እንዲህ ያደረገው ሰዎች ካዩት በሌሎቹ የአይሁድ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳያጣ ፈርቶ ሊሆን ይችላል።

ኒቆዲሞስ “ረቢ፣ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም” አለ። ኢየሱስም በምላሹ አንድ ሰው ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንዲችል ‘ዳግመኛ መወለድ’ እንዳለበት ነገረው።—ዮሐንስ 3:2, 3

ይሁንና አንድ ሰው እንዴት ዳግመኛ ሊወለድ ይችላል? ኒቆዲሞስ፣ “ሰው . . . ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ ይችላል?” ሲል ጠየቀ።—ዮሐንስ 3:4

ዳግመኛ መወለድ ሲባል እንዲህ ማለት አይደለም። ኢየሱስ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም” በማለት ነገሩን አብራራለት። (ዮሐንስ 3:5) ኢየሱስ ሲጠመቅና መንፈስ ቅዱስ ሲወርድበት “ከውኃና ከመንፈስ” ተወልዷል። በዚያ ጊዜ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰምቶ ነበር። (ማቴዎስ 3:16, 17) አምላክ ይህን ሲል በዚህ ወቅት ኢየሱስ፣ ወደ ሰማያዊው መንግሥት የመግባት ተስፋ ያለው መንፈሳዊ ልጁ መሆኑን መግለጹ ነበር። ሌሎች የተጠመቁ ሰዎችም ከጊዜ በኋላ ማለትም በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ ዳግመኛ ይወለዳሉ፤ በሌላ አባባል በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች ይሆናሉ።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-4

ኒቆዲሞስ፣ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሚያስተምረውን ነገር መረዳት ከበደው። በመሆኑም ኢየሱስ፣ የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ በመሆን የሚጫወተውን ወሳኝ የሆነ ሚና አብራራለት። ኢየሱስ “ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:14, 15

ከረጅም ዘመናት በፊት፣ በመርዘኛ እባቦች ተነድፈው የነበሩት እስራኤላውያን መዳን እንዲችሉ ከመዳብ የተሠራውን እባብ መመልከት ነበረባቸው። (ዘኁልቁ 21:9) በተመሳሳይም የሰው ልጆች በሙሉ ከሞት ነፃ ለመውጣትና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በአምላክ ልጅ ማመን አለባቸው። ኢየሱስ፣ በዚህ ረገድ ይሖዋ ፍቅሩን ያሳየበትን መንገድ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ለኒቆዲሞስ እንዲህ አለው፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) በመሆኑም ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች መዳን የሚያገኙበት መንገድ እሱ መሆኑን አገልግሎቱን በጀመረ በስድስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ውስጥ በግልጽ ተናግሯል።

ኢየሱስ “አምላክ ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ላይ እንዲፈርድ” አለመሆኑን ለኒቆዲሞስ ነገረው። ኢየሱስ ይህን ሲል፣ የተላከው በሰው ዘር ሁሉ ላይ የጥፋት ፍርድ እንዲፈርድ አለመሆኑን እየገለጸ ነው። ከዚህ ይልቅ የተላከው “ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን” መሆኑን ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:17

ኒቆዲሞስ ስለፈራ ወደ ኢየሱስ የመጣው ጨለማን ተገን አድርጎ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ውይይቱን በሚከተሉት ቃላት መደምደሙ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን [ኢየሱስ በአኗኗሩና በትምህርቱ የሚፈነጥቀው ብርሃን] ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። መጥፎ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ እንዲሁም ሥራው እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን  አይመጣም። ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ግን ያደረገው ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የተከናወነ መሆኑ እንዲታይ ወደ ብርሃን ይመጣል።”—ዮሐንስ 3:19-21

ፈሪሳዊና የእስራኤል አስተማሪ የሆነው ኒቆዲሞስ፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና በተማረው ነገር ላይ ከዚህ በኋላ ሊያሰላስልበት ይገባል።