በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 56

ሰውን የሚያረክሰው ምንድን ነው?

ሰውን የሚያረክሰው ምንድን ነው?

ማቴዎስ 15:1-20 ማርቆስ 7:1-23 ዮሐንስ 7:1

  • ኢየሱስ የሰዎችን ወግ አወገዘ

በ32 ዓ.ም. የሚከበረው የፋሲካ በዓል እየተቃረበ ነው፤ ኢየሱስ በገሊላ በስብከቱ ሥራ ተጠምዷል። የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት ፋሲካን ለማክበር ሳይሆን አይቀርም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ሊገድሉት እየፈለጉ ስለሆነ ወደዚያ የሄደው ተጠንቅቆ ነው። (ዮሐንስ 7:1) ከዚያ በኋላም ወደ ገሊላ ተመለሰ።

ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ከኢየሩሳሌም ተነስተው ወደ እሱ በመጡበት ወቅት ኢየሱስ ቅፍርናሆም ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ወደዚህ የመጡት ለምንድን ነው? ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ሕጎችን እንደጣሰ በመግለጽ እሱን የሚከሱበት ሰበብ እየፈለጉ ስለሆነ ነው። በመሆኑም እንዲህ ብለው ጠየቁት፦ “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚጥሱት ለምንድን ነው? ለምሳሌ፣ ሊበሉ ሲሉ እጃቸውን አይታጠቡም።” (ማቴዎስ 15:2) አምላክ፣ ‘እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ የመታጠብን’ ወግ እንዲከተሉ ሕዝቡን ፈጽሞ አላዘዘም። (ማርቆስ 7:3) ሆኖም ፈሪሳውያን ይህን አለማድረግ ከባድ ጥፋት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ኢየሱስ ለክሳቸው ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ የአምላክን ሕግ ሆን ብለው የሚጥሱት እንዴት እንደሆነ ጠቆመ። “እናንተ ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ለምሳሌ አምላክ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይገደል’ ብሏል። እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ ነው” ካለ አባቱን የማክበር ግዴታ የለበትም።’”—ማቴዎስ 15:3-6፤ ዘፀአት 20:12፤ 21:17

ፈሪሳውያን ለአምላክ በስጦታነት የተመደበ ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ሌላ ማንኛውም ነገር የቤተ መቅደሱ ስለሆነ ለሌላ ዓላማ መዋል እንደማይችል ያስተምራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለአምላክ በስጦታነት የተወሰነው ነገር በሰውየው እጅ እንዳለ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ልጅ ገንዘቡ አሊያም ንብረቱ “ቁርባን” ማለትም ለአምላክ ወይም ለቤተ መቅደሱ የተወሰነ ስጦታ እንደሆነ ሊገልጽ ይችላል፤ ይህን ሲል ከወላጆቹ ይልቅ በንብረቱ ላይ መብት ያለው ቤተ መቅደሱ እንደሆነ የተናገረ ያህል ነው። ልጁ፣ ገንዘቡን ወይም ንብረቱን እየተጠቀመበት ቢሆንም በዕድሜ የገፉና የተቸገሩ ወላጆቹን ለመርዳት ግን ሊጠቀምበት እንደማይችል ይናገራል። በዚህ መንገድ፣ ወላጆቹን የመርዳት ኃላፊነቱን ከመወጣት ወደኋላ ይላል።—ማርቆስ 7:11

ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ ሆን ብለው በማጣመማቸው መቆጣቱ በእርግጥም የተገባ ነው፤ እንዲህ አላቸው፦ “ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል። እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’” ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስ የሰነዘረውን ጠንከር ያለ ወቀሳ ሊያስተባብሉ አልቻሉም። በመሆኑም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ፤ ደግሞም ይህን ቃል አስተውሉ፦ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የሚገባው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው ነው።”—ማቴዎስ 15:6-11፤ ኢሳይያስ 29:13

በኋላ ላይ ቤት ውስጥ እያለ ደቀ መዛሙርቱ “ፈሪሳውያን በተናገርከው ነገር ቅር እንደተሰኙ አውቀሃል?” አሉት። እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።”—ማቴዎስ 15:12-14

ሰውን የሚያረክሰውን ነገር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጴጥሮስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወክሎ ሲጠይቀው ኢየሱስ የተገረመ ይመስላል። እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚዘልቅና ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ እንደሚገባ አታውቁም? ይሁን እንጂ ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው። ለምሳሌ ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ የፆታ ብልግና፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመሥከርና ስድብ ይወጣሉ። ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ግን ሰውን አያረክስም።”—ማቴዎስ 15:17-20

እዚህ ላይ ኢየሱስ ንጽሕናን መጠበቅ አስፈላጊ እንዳልሆነ  መግለጹ አይደለም፤ አንድ ሰው ምግብ ከመሥራቱ ወይም ከመብላቱ በፊት እጆቹን መታጠብ እንደሌለበት መናገሩም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ፣ የሰዎችን ወግ በመከተል የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ችላ የሚሉትን ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች ማውገዙ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሰውን የሚያረክሱት ከልብ የሚመነጩ ክፉ ሥራዎች ናቸው።