በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 94

ሁለት አስፈላጊ ነገሮች—ጸሎትና ትሕትና

ሁለት አስፈላጊ ነገሮች—ጸሎትና ትሕትና

ሉቃስ 18:1-14

  • ደጋግማ የጠየቀችው መበለት ምሳሌ

  • ፈሪሳዊውና ቀረጥ ሰብሳቢው

ኢየሱስ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት የሚያጎላ ምሳሌ ከዚህ ቀደም ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 11:5-13) አሁን የሚገኘው በሰማርያ አሊያም በገሊላ ሳይሆን አይቀርም፤ ሳይታክቱ የመጸለይን አስፈላጊነት በዚህ ወቅትም ጎላ አድርጎ ገለጸ። ይህን ያደረገው የሚከተለውን ምሳሌ በመጠቀም ነው፦

“በአንዲት ከተማ አምላክን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበር። በዚያች ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፤ በየጊዜው ወደ እሱ እየሄደች ‘ከባላጋራዬ ጋር ለምከራከርበት ጉዳይ ፍረድልኝ’ ትለው ነበር። ይሁንና ዳኛው ለተወሰነ ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፦ ‘ምንም እንኳ አምላክን የማልፈራ፣ ሰውንም የማላከብር ብሆን ይህች መበለት ሁልጊዜ እየመጣች ስለምታስቸግረኝ ፍትሕ እንድታገኝ አደርጋለሁ፤ አለዚያ በየጊዜው እየመጣች ትነዘንዘኛለች።’”—ሉቃስ 18:2-5

ኢየሱስ ምሳሌው ያዘለውን ቁም ነገር ሲያብራራ እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ዳኛው ዓመፀኛ ቢሆንም ምን እንዳለ ልብ በሉ! ታዲያ አምላክ በትዕግሥት የሚይዛቸውና ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?” (ሉቃስ 18:6, 7) ለመሆኑ ኢየሱስ ይህን የተናገረው ስለ አባቱ ምን ሊያስተምር አስቦ ነው?

ኢየሱስ ይህን ያለው፣ ይሖዋ አምላክ እንደ ዓመፀኛው ዳኛ መሆኑን ለመግለጽ ፈልጎ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ንጽጽር በመጠቀም የሚከተለውን ነጥብ አስገንዝቧል፦ ዓመፀኛ የሆነ ሰብዓዊ ዳኛ እንኳ በተደጋጋሚ ለሚቀርብለት ልመና ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ አምላክም እንዲህ እንደሚያደርግ ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ጻድቅና ጥሩ አምላክ በመሆኑ ሕዝቦቹ ተስፋ ሳይቆርጡ ከጸለዩ ምላሽ ይሰጣቸዋል። ኢየሱስ አክሎ “እላችኋለሁ፣ [አምላክ] በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል” ማለቱ ይህን ያሳያል።—ሉቃስ 18:8

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችና ድሆች ብዙውን ጊዜ ፍትሕ አያገኙም፤ በሌላ በኩል ግን ኃያልና ሀብታም ለሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አድልዎ ይደረጋል። አምላክ ግን እንዲህ አያደርግም። አምላክ ጊዜው ሲደርስ ክፉዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉና አገልጋዮቹ የዘላለም ሕይወት እንዲወርሱ በማድረግ ፍትሕ እንዲፈጸም ያደርጋል።

ታዲያ የመበለቷ ዓይነት እምነት ያላቸው እነማን ናቸው? አምላክ “በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ” እንደሚያደርግ ከልባቸው የሚያምኑስ ምን ያህል ናቸው? ኢየሱስ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ተናግሮ መጨረሱ ነው። አሁን ደግሞ ጸሎት ባለው ኃይል ላይ እምነት ማሳደርን አስመልክቶ “የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እምነት ያገኝ ይሆን?” ሲል ጠየቀ። (ሉቃስ 18:8) የጥያቄው አንድምታ፣ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ብዙዎች እንዲህ ዓይነት እምነት ላይኖራቸው እንደሚችል የሚያመለክት ነው።

ኢየሱስን ከሚያዳምጡት ሰዎች አንዳንዶቹ እምነት እንዳላቸው እርግጠኞች ናቸው። ጻድቅ እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑ ሲሆን ሌሎችን ግን ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። ኢየሱስ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች የሚከተለውን ምሳሌ ተናገረ፦

“ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንደኛው ፈሪሳዊ፣ ሌላኛው ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ እንዲህ ሲል ይጸልይ ጀመር፦ ‘አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌላው ሰው ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ። በሳምንት ሁለቴ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ነገር ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ።’”—ሉቃስ 18:10-12

ፈሪሳውያን፣ ጻድቅ መስለው ለመታየት በሚያደርጉት  ነገር ይታወቃሉ። ይህን የሚያደርጉት ሌሎችን ለማስደመም ብለው ነው። ራሳቸው ባወጡት ሥርዓት መሠረት ሰኞና ሐሙስ ይጾማሉ፤ በእነዚህ ቀናት በትላልቆቹ የገበያ ቦታዎች ብዙ ሕዝብ ስለሚኖር በርካታ ሰዎች ሊያዩዋቸው ይችላሉ። ከዚህም ሌላ ለትናንሽ ተክሎች እንኳ ምንም ሳያጓድሉ አሥራት ይከፍላሉ። (ሉቃስ 11:42) ከጥቂት ወራት በፊት እነዚህ ሰዎች “ሕጉን [ፈሪሳውያን ለሕጉ የሚሰጡትን ትርጓሜ] የማያውቀው ይህ ሕዝብ . . . የተረገመ ነው” በማለት ለተራው ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ገልጸዋል።—ዮሐንስ 7:49

ኢየሱስ ምሳሌውን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ቀረጥ ሰብሳቢው ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየትም እንኳ አልደፈረም፤ እንዲያውም ‘አምላክ ሆይ፣ ኃጢአተኛ ለሆንኩት ለእኔ ቸርነት አድርግልኝ’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ቀረጥ ሰብሳቢው የፈጸማቸውን ስህተቶች በትሕትና አምኖ ተቀብሏል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “እላችኋለሁ፣ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይሄኛው ሰው ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ምክንያቱም ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ግን ከፍ ይደረጋል።”—ሉቃስ 18:13, 14

በዚህ መንገድ ኢየሱስ ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ራሳቸውን የሚያመጻድቁት ፈሪሳውያን በሥልጣንና በማዕረግ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፤ እንዲህ ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ ላደጉት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህ ጠቃሚ ምክር ነው። በእርግጥም ምክሩ ለሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል።