በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 136

በገሊላ ባሕር ዳርቻ

በገሊላ ባሕር ዳርቻ

ዮሐንስ 21:1-25

  • ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ተገለጠ

  • ጴጥሮስና ሌሎች፣ በጎችን ይመግባሉ

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት “ከተነሳሁ በኋላ . . . ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:32፤ 28:7, 10) አሁን ከተከታዮቹ ብዙዎቹ ወደ ገሊላ ሄዱ፤ ሆኖም እዚያ ምን ማድረግ ይኖርባቸው ይሆን?

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ፣ ከሐዋርያቱ መካከል ስድስቱን “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው። ሁሉም “እኛም አብረንህ እንሄዳለን” አሉት። (ዮሐንስ 21:3) ሆኖም ሌሊቱን ሙሉ አንድም ዓሣ አላጠመዱም። ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ተገለጠ፤ እነሱ ግን ማን እንደሆነ አላወቁም። ከዚያም ኢየሱስ “ልጆቼ፣ የሚበላ ነገር አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “የለንም!” ብለው መለሱለት። ኢየሱስ “መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። (ዮሐንስ 21:5, 6) እንደተባሉት ሲያደርጉ በጣም ብዙ ዓሣ ከመያዛቸው የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው።

በዚህ ጊዜ፣ ዮሐንስ ለጴጥሮስ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። (ዮሐንስ 21:7) ጴጥሮስ ዓሣ ሲያጠምድ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ በፍጥነት ለበሰ። ከዚያም ባሕሩ ውስጥ ዘሎ ገባና 100 ሜትር ገደማ የሚሆነውን ርቀት እየዋኘ ወደ ዳርቻው ሄደ። ሌሎቹም በዓሣ የተሞላውን መረብ እየጎተቱ በጀልባው ተከተሉት።

ወደ ባሕሩ ዳርቻ በደረሱ ጊዜ “በከሰል ፍም ላይ የተቀመጠ ዓሣ እንዲሁም ዳቦ አዩ።” ኢየሱስ “አሁን ከያዛችሁት ዓሣ የተወሰነ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጴጥሮስ በ153 ትላልቅ ዓሣዎች የተሞላውን መረብ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎተተው። ከዚያም ኢየሱስ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” አላቸው። ሐዋርያቱ ይህ ሰው ኢየሱስ መሆኑን ስለተገነዘቡ አንዳቸውም “አንተ ማን ነህ?” ብለው ለመጠየቅ አልደፈሩም። (ዮሐንስ 21:9-12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ተሰባስበው እያለ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ነው።

ኢየሱስ ለእያንዳንዳቸው ጥቂት ዳቦና ዓሣ በመስጠት ቁርሳቸውን አበላቸው። ምናልባትም ወደተጠመደው ዓሣ እየተመለከተ ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” አለው። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የሰጠውን ሥራ ዓሣ ከማጥመድ ይበልጥ ይወደዋል? “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል ጴጥሮስ መለሰ። በመሆኑም ኢየሱስ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።—ዮሐንስ 21:15

ደግሞም ለሁለተኛ ጊዜ ኢየሱስ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” ብሎ ጠየቀው። ጴጥሮስ ግራ ተጋብቶ ሳይሆን አይቀርም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” በማለት ከልቡ መለሰ። ኢየሱስ “ግልገሎቼን ጠብቅ” በማለት ከቀድሞው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትእዛዝ ሰጠው።—ዮሐንስ 21:16

ከዚያም ለሦስተኛ ጊዜ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ በጣም ትወደኛለህ?” አለው። ይህን ሲለው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ታማኝነቱን እንደተጠራጠረ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” በማለት ጠበቅ አድርጎ መለሰ። በዚህ ጊዜም ኢየሱስ “ግልገሎቼን መግብ” በማለት ጴጥሮስ ሊያከናውነው የሚገባውን ሥራ ጎላ አድርጎ ገለጸለት። (ዮሐንስ 21:17) በእርግጥም ኃላፊነት ያላቸው ሁሉ፣ ወደ አምላክ በረት የሚመጡትን ማገልገል አለባቸው።

ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ሥራ በመሥራቱ ታስሯል፤ እንዲሁም ተገድሏል። ጴጥሮስም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገጥመው ኢየሱስ ገለጸ፦ “ወጣት ሳለህ ራስህ ለብሰህ ወደፈለግክበት ቦታ ትሄድ ነበር። ስታረጅ ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያለብስሃል፤ ወደማትፈልግበትም ቦታ ይወስድሃል።” ያም ቢሆን ኢየሱስ “እኔን መከተልህን ቀጥል” በማለት አሳሰበው።—ዮሐንስ 21:18, 19

ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ዮሐንስን ተመለከተና “ጌታ ሆይ፣ ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” ብሎ ጠየቀ። ለመሆኑ ኢየሱስ ይበልጥ የሚወደው ሐዋርያ ወደፊት ምን ይገጥመዋል? ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲቆይ ብፈቅድ አንተ ምን ቸገረህ?” አለው። (ዮሐንስ 21:21-23) ጴጥሮስ ሌሎች ስለሚያደርጉት ነገር ሳይጨነቅ ኢየሱስን መከተል ይኖርበታል። ያም ቢሆን ዮሐንስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ረጅም ዕድሜ እንደሚኖረውና ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን በሚመጣበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ ራእይ እንደሚመለከት ኢየሱስ ጠቁሟል።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ ቢጻፉ ብዙ ጥቅልሎች እንኳ አይበቋቸውም።