በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 44

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘው

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘው

ማቴዎስ 8:18, 23-27 ማርቆስ 4:35-41 ሉቃስ 8:22-25

  • ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ላይ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘው

ኢየሱስ ቀኑን ያሳለፈው በሥራ ተወጥሮ ነው። አመሻሹ ላይ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ይህን ሲል ከቅፍርናሆም ማዶ ያለውን አካባቢ ማለቱ ነው።—ማርቆስ 4:35

በገሊላ ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ ጌርጌሴኖን የሚባለው ክልል ይገኛል። ይህ አካባቢ ዲካፖሊስ ተብሎም ይጠራል። የዲካፖሊስ ከተሞች የግሪክ ባሕል ማዕከል ናቸው፤ በእርግጥ በዚያ ብዙ አይሁዳውያን ይኖራሉ።

ኢየሱስ ቅፍርናሆምን ለቆ መሄዱን አንዳንዶች አስተዋሉ። በመሆኑም ሌሎች ጀልባዎችም ባሕሩን ማቋረጥ ጀመሩ። (ማርቆስ 4:36) በእርግጥ ጉዞው ያን ያህል ረጅም አይደለም። የገሊላ ባሕር 21 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውና በዛ ቢባል 12 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ጨዋማ ያልሆነ ትልቅ ሐይቅ ነው፤ ጥልቀት የለውም ማለት ግን አይደለም።

ኢየሱስ ፍጹም ሰው ቢሆንም በአገልግሎት ብዙ ሲሠራ በመቆየቱ እንደደከመው ግልጽ ነው። በመሆኑም በባሕሩ ላይ መጓዝ ከጀመሩ ብዙም ሳይቆይ በጀልባዋ የኋለኛ ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኛ።

ከሐዋርያቱ መካከል አብዛኞቹ ጀልባ በመቅዘፍ ረገድ ልምድ ያላቸው ቢሆኑም ይህ ጉዞ ቀላል አልሆነላቸውም። አካባቢው በተራሮች የተከበበ ሲሆን የገሊላ ባሕር የላይኛው ክፍል አብዛኛውን ጊዜ ሞቃት ነው። አንዳንድ ጊዜ ከተራሮቹ የሚመጣው ቀዝቃዛ አየር፣ በባሕሩ የላይኛው ክፍል ካለው ሞቃት አየር ጋር ሲጋጭ ባሕሩ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ይፈጠራል። በዚህ ጊዜም የተከሰተው ይህ ነው። ብዙም ሳይቆይ ማዕበሉ ጀልባዋን ይመታት ጀመር። ጀልባዋ “በውኃ መሞላት ስለጀመረች አደጋ ላይ ወደቁ።” (ሉቃስ 8:23) ኢየሱስ ግን አሁንም እንደተኛ ነው!

ባሕረተኞቹ እንዲህ ካሉ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም ጀልባቸውን እየቀዘፉ ማዕበሉን ለማለፍ ባለ በሌለ ኃይላቸው መታገል ጀመሩ። አሁን ያጋጠማቸው ሁኔታ ግን የተለየ ነው። ለሕይወታቸው ስለሰጉ ኢየሱስን ቀስቅሰው “ጌታ ሆይ፣ ማለቃችን እኮ ነው፤ አድነን!” አሉት። (ማቴዎስ 8:25) ደቀ መዛሙርቱ እንዳይሰምጡ ፈርተዋል።

ኢየሱስ ሲነቃ ሐዋርያቱን “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?” አላቸው። (ማቴዎስ 8:26) ከዚያም ነፋሱንና ባሕሩን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” ብሎ አዘዘው። (ማርቆስ 4:39) ባሕሩን ያናወጠው ነፋስ ቆመ፤ ባሕሩም ጸጥ አለ። (ማርቆስና ሉቃስ ይህን አስገራሚ ተአምር ሲዘግቡ መጀመሪያ የጠቀሱት ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ማዕበሉን ጸጥ ማሰኘቱን ነው፤ ስለ ደቀ መዛሙርቱ እምነት ማጣት የገለጹት ከዚያ በኋላ ነው።)

ይህ ክንውን በደቀ መዛሙርቱ ላይ ምን ስሜት እንደፈጠረ እስቲ አስበው! በማዕበል ይናወጥ የነበረው ባሕር በድንገት ረጭ ሲል ተመልክተዋል። በታላቅ ፍርሃት ተውጠው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ። ከዚያም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በሰላም ወደ ባሕሩ ማዶ ተሻገሩ። (ማርቆስ 4:41 እስከ 5:1) ሌሎቹ ጀልባዎችም ወደ ባሕሩ ምዕራባዊ ዳርቻ ሳይመለሱ አልቀሩም።

የአምላክ ልጅ የአየር ንብረቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል እንዳለው ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስ በመንግሥቱ አገዛዝ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ምድር ሲያደርግ፣ የሚያስፈራ የተፈጥሮ አደጋ ስለማይኖር ሁሉም ሰው ያለ ስጋት መኖር ይችላል!