በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 90

“ትንሣኤና ሕይወት”

“ትንሣኤና ሕይወት”

ዮሐንስ 11:17-37

  • ኢየሱስ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ደረሰ

  • “ትንሣኤና ሕይወት”

ኢየሱስ ከፔሪያ ተነስቶ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ወደምትገኘው ቢታንያ የተባለች መንደር እየደረሰ ነው። የአልዓዛር እህቶች የሆኑት ማርያምና ማርታ ወንድማቸው በቅርቡ በመሞቱ ሐዘን ላይ ናቸው። እነሱን ለማጽናናት ብዙ ሰዎች ወደ ቤታቸው መጥተዋል።

አንድ ሰው ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ለማርታ ሲነግራት እሱን ለመቀበል በፍጥነት ወጣች። ማርታ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” በማለት እሷና እህቷ ላለፉት አራት ቀናት ሲያስቡት የቆዩትን ነገር ነገረችው። ማርታ ይህን ያለችው ተስፋ ስለሌላት አይደለም። “አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አምናለሁ” በማለት ቀጥላ ተናገረች። (ዮሐንስ 11:21, 22) ኢየሱስ አሁንም ቢሆን ለወንድሟ አንድ ነገር ሊያደርግለት እንደሚችል ተሰምቷታል።

ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። ኢየሱስ ይህን ሲል ማርታ ወደፊት ምድር ላይ ስለሚከናወነው ትንሣኤ እየተናገረ መሰላት፤ አብርሃምና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም እንዲህ ዓይነት ተስፋ ነበራቸው። ማርታ በዚህ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላት ስትገልጽ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለች።—ዮሐንስ 11:23, 24

ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚህ ወቅት ሐዘናቸውን የሚያስወግድላቸው ነገር ሊያደርግ ይችላል? አምላክ በሞት ላይ ሥልጣን እንደሰጠው ሲገልጽ ለማርታ እንዲህ አላት፦ “በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል፤ በሕይወት ያለና በእኔ የሚያምን ሁሉ ደግሞ ፈጽሞ አይሞትም።”—ዮሐንስ 11:25, 26

ኢየሱስ እንዲህ ሲል በወቅቱ በሕይወት ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ፈጽሞ እንደማይሞቱ መናገሩ አይደለም። ለሐዋርያቱ እንደነገራቸው እሱ ራሱ እንኳ መሞቱ አይቀርም። (ማቴዎስ 16:21፤ 17:22, 23) ኢየሱስ በእሱ ማመን ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ እንደሚችል ማጉላት ፈልጓል። ብዙዎች እንዲህ ያለውን ሕይወት የሚያገኙት ከሞት ሲነሱ ነው። ሆኖም ይህ ሥርዓት ሲያበቃ በሕይወት የሚኖሩ ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ፈጽሞ ሞትን ላያዩ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ፣ ሞቶ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን ይችላል።

ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” በማለት ተናገረ፤ ታዲያ ከሞተ ቀናት ያለፉትን አልዓዛርን ሊያስነሳው ይችላል? ኢየሱስ “ይህን ታምኛለሽ?” በማለት ማርታን ጠየቃት። እሷም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ኢየሱስ በዚያው ዕለት የሆነ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ስላመነች በፍጥነት ወደ ቤት በመሄድ እህቷን ለብቻዋ ጠርታ “መምህሩ መጥቷል፤ እየጠራሽ ነው” አለቻት። (ዮሐንስ 11:25-28) በዚህ ጊዜ ማርያም ከቤት ወጣች፤ እዚያ ያሉት ሰዎችም ወደ አልዓዛር መቃብር የምትሄድ ስለመሰላቸው ተከተሏት።

ማርያም ግን ወደ ኢየሱስ በመሄድ እግሩ ላይ ወድቃ እያለቀሰች “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” በማለት እህቷ የተናገረችውን ደገመችው። ኢየሱስ ማርያምና አብረዋት የመጡት ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ፤ ተረበሸም፤ እንዲያውም እንባውን አፈሰሰ። በቦታው ያሉት ሰዎች ይህን ሲያዩ ተገረሙ። ሆኖም አንዳንዶች ‘ኢየሱስ የዓይነ ስውርን ዓይን ማብራት ከቻለ ይሄኛውንም እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?’ አሉ።—ዮሐንስ 11:32, 37