በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 14

ደቀ መዛሙርት ማፍራት ጀመረ

ደቀ መዛሙርት ማፍራት ጀመረ

ዮሐንስ 1:29-51

  • ኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ

ኢየሱስ ለ40 ቀናት በምድረ በዳ ቆይቶ ወደ ገሊላ ከመመለሱ በፊት፣ ቀደም ሲል ወዳጠመቀው ወደ ዮሐንስ እንደገና ሄደ። ኢየሱስ እየቀረበ ሲመጣ ዮሐንስ በእጁ ወደ እሱ እያመለከተ አብረውት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ አለ፦ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ! ‘ከኋላዬ አንድ ሰው ይመጣል፤ ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ያልኳችሁ እሱ ነው።” (ዮሐንስ 1:29, 30) ዮሐንስ ከኢየሱስ በዕድሜ ትንሽ የሚበልጥ ቢሆንም እንኳ ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ሆኖ በሰማይ ይኖር እንደነበር ያውቃል።

ኢየሱስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ ሲመጣ፣ መሲሕ የሚሆነው እሱ መሆኑን ዮሐንስ እርግጠኛ የነበረ አይመስልም። ዮሐንስ “እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ እኔ በውኃ እያጠመቅኩ የመጣሁበት ምክንያት ግን እሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 1:31

ከዚያም ዮሐንስ፣ ኢየሱስን ሲያጠምቀው የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “መንፈስ ከሰማይ ወጥቶ እንደ ርግብ ሲወርድ አይቻለሁ፤ በእሱም ላይ አረፈ። እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ ሆኖም በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ ራሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት የምታየው ያ ሰው ነው’ አለኝ። እኔም አይቻለሁ፤ እሱም የአምላክ ልጅ መሆኑን መሥክሬአለሁ።”—ዮሐንስ 1:32-34

በነጋታው ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እያለ ኢየሱስን እንደገና ተመለከተው። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ “የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” አለ። (ዮሐንስ 1:36) የመጥምቁ ዮሐንስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ይህን ሲሰሙ ኢየሱስን ተከተሉት። አንደኛው እንድርያስ ይባላል። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ዘገባ ያሰፈረው ሰው ይኸውም ዮሐንስ ሳይሆን አይቀርም። ይሄኛው ዮሐንስ፣ የሰሎሜ ልጅ በመሆኑ የኢየሱስ አክስት ልጅ ሊሆን ይችላል። የዘብዴዎስ ሚስት የሆነችው ሰሎሜ የማርያም እህት ሳትሆን አትቀርም።

ኢየሱስ ወደኋላ ዞር ሲል እንድርያስና ዮሐንስ ሲከተሉት ስለተመለከተ “ምን ፈልጋችሁ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

እነሱም “ረቢ፣ የት ነው የምትኖረው?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስም “ኑና እዩ” አላቸው።—ዮሐንስ 1:37-39

ጊዜው ከቀትር በኋላ አሥር ሰዓት ገደማ ነው፤ እንድርያስና ዮሐንስ በዚያ ዕለት ከኢየሱስ ጋር አብረው ቆዩ። እንድርያስ በጣም ተደስቷል፤ በመሆኑም ጴጥሮስ ተብሎም የሚጠራውን ወንድሙን ስምዖንን ሲያየው “መሲሑን አገኘነው” አለው። (ዮሐንስ 1:41) እንድርያስ ጴጥሮስን ወደ ኢየሱስ ወሰደው። ከጊዜ በኋላ የተከናወኑት ነገሮች እንደሚጠቁሙት ዮሐንስም ወንድሙን ያዕቆብን አግኝቶ ወደ ኢየሱስ ያመጣው ይመስላል፤ ይሁንና ዮሐንስ ከራሱ ጋር የተያያዘውን ይህን ታሪክ በዘገባው ውስጥ አላሰፈረውም።

በሚቀጥለው ቀን ኢየሱስ፣ ፊልጶስ የተባለውን የቤተሳይዳ ሰው አገኘ። ቤተሳይዳ የምትገኘው በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ዳርቻ አቅራቢያ ሲሆን እንድርያስና ጴጥሮስ ያደጉት በዚህች ከተማ ነው። ኢየሱስ ለፊልጶስ “ተከታዬ ሁን” የሚል ግብዣ አቀረበለት።—ዮሐንስ 1:43

 ከዚያም ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ ተብሎም የሚጠራውን ናትናኤልን አገኘውና “ሙሴ በሕጉ፣ ነቢያት ደግሞ በመጻሕፍት የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” አለው። ናትናኤል ግን ስለተጠራጠረ ፊልጶስን “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ሲል ጠየቀው።

ፊልጶስም “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስ፣ ናትናኤል ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” በማለት ስለ እሱ ተናገረ።

ናትናኤል “እንዴት ልታውቀኝ ቻልክ?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስም “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ” አለው።

ናትናኤል በመገረም “ረቢ፣ አንተ የአምላክ ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው።

“ያመንከው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልኩህ ነው?” ሲል ኢየሱስ ጠየቀው። አክሎም “ከዚህ የሚበልጥ ነገር ገና ታያለህ” አለ። ከዚያም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ የአምላክ መላእክት ወደዚያ ሲወጡና የሰው ልጅ ወዳለበት ሲወርዱ ታያላችሁ” ሲል ቃል ገባ።—ዮሐንስ 1:45-51

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ከአዲሶቹ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በመሆን ከዮርዳኖስ ሸለቆ ተነስቶ ወደ ገሊላ ተጓዘ።