በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 33

የኢሳይያስን ትንቢት መፈጸም

የኢሳይያስን ትንቢት መፈጸም

ማቴዎስ 12:15-21 ማርቆስ 3:7-12

  • ሕዝቡ ኢየሱስን አጨናነቀው

  • የኢሳይያስን ትንቢት ፈጸመ

ኢየሱስ፣ ፈሪሳውያንና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ሊገድሉት እንዳሴሩ ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። ከገሊላ፣ በባሕር ዳርቻ ላይ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና፣ ከዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ክፍል፣ ከኢየሩሳሌምና በስተ ደቡብ ርቆ ከሚገኘው ከኤዶምያስ እጅግ ብዙ ሰዎች እሱ ወዳለበት ጎረፉ። ኢየሱስም ብዙዎችን ፈወሰ። በዚህም የተነሳ ከባድ ሕመም ያለባቸው ወደ እሱ ለመቅረብ መጋፋት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እስኪዳስሳቸው ከመጠበቅ ይልቅ እሱን ለመንካት እየተንጠራሩ ነው።—ማርቆስ 3:9, 10

ሕዝቡ በጣም ብዙ ስለሆነ ኢየሱስ፣ ከባሕሩ ዳርቻ ፈቀቅ ለማለትና ከሚያጨናንቁት ሕዝብ ለመራቅ ሲል አንዲት ትንሽ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። በጀልባው ላይ ሆኖ ሕዝቡን ማስተማር ብሎም በባሕሩ ዳርቻ ወደሚገኙ አካባቢዎች በመሄድ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ይችላል።

ደቀ መዝሙሩ ማቴዎስ፣ ኢየሱስ ያከናወነው ሥራ ‘በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው’ ትንቢት እንዲፈጸም እንዳደረገ ገልጿል። (ማቴዎስ 12:17) ኢየሱስ በዚህ ቦታ የፈጸመው ትንቢት የትኛው ነው?

“እነሆ፣ የምወደውና ደስ የምሰኝበት የመረጥኩት አገልጋዬ! መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም። ፍትሕን በአስተማማኝ ሁኔታ እስኪያሰፍን ድረስ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም። በእርግጥም ብሔራት በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”—ማቴዎስ 12:18-21፤ ኢሳይያስ 42:1-4

አምላክ የሚወደውና ደስ የሚሰኝበት አገልጋይ ኢየሱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ፣ እውነተኛ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፤ ፍትሕ በሐሰት ሃይማኖታዊ ወጎች ተጋርዷል። ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመተርጎማቸው በሰንበት ቀን የታመመ ሰው እንኳ አይረዱም! ኢየሱስ፣ ሕዝቡን እንደ ሸክም ከተጫኗቸው ፍትሐዊ ያልሆኑ ወጎች በመገላገል የአምላክን ፍትሕ ያንጸባረቀ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ መንፈስ በእሱ ላይ እንደሆነ አሳይቷል። ይህንንም በማድረጉ የሃይማኖት መሪዎቹ ሊገድሉት ፈለጉ። ይህ እንዴት የሚያሳፍር ነው!

“አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ድምፁን የሚሰማ አይኖርም” የሚለው አገላለጽስ ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ የፈወሳቸውን ሰዎችም ሆነ ያስወጣቸውን አጋንንት “የእሱን ማንነት ለሌሎች እንዳይገልጹ” ከልክሏቸዋል። (ማርቆስ 3:12) ሰዎች የእሱን ማንነት እንዲያውቁ የፈለገው በየመንገዱ ስለ እሱ በሚለፈፍ አዋጅ ወይም በስሚ ስሚ በሚዛመት የተዛባ ወሬ አይደለም።

 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ በምሳሌያዊ ሁኔታ ላዘመሙና ለወደቁ ሰዎች የሚያጽናና መልእክት ይነግራቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሊጠፋ እንደተቃረበ የሚጨስ የጧፍ ክር ናቸው። ኢየሱስ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ ሊጠፋ የተቃረበን የሚጨስ ጧፍም አያጠፋም። ከዚህ ይልቅ የዋሆችን በአሳቢነትና በፍቅር እንዲሁም በዘዴ ቀና ያደርጋቸዋል። በእርግጥም ብሔራት ተስፋ ሊያደርጉ የሚገባው በኢየሱስ ነው!