በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 111

ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት

ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት

ማቴዎስ 24:3-51 ማርቆስ 13:3-37 ሉቃስ 21:7-38

  •   አራት ደቀ መዛሙርት ምልክት ጠየቁ

  • ምልክቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመንና ከዚያ በኋላ የሚኖረው ፍጻሜ

  • ምንጊዜም ንቁ መሆን አለብን

ዕለቱ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ሲሆን ኒሳን 11 እየተገባደደ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በሥራ ተወጥሮ ያሳለፈው ጊዜም ሊያበቃ ተቃርቧል። ኢየሱስ ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እየዋለ ማታ ደግሞ ከከተማዋ ውጭ ያድራል። ሕዝቡ ልዩ ትኩረት የሰጡት ሲሆን “በቤተ መቅደስ እሱን ለመስማት በማለዳ ወደ እሱ” ሲመጡ ሰንብተዋል። (ሉቃስ 21:37, 38) ይህ ሁሉ አልፎ አሁን ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከጴጥሮስ፣ ከእንድርያስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ተቀምጧል።

እነዚህ አራት ሐዋርያት ወደ እሱ የመጡት ብቻውን ሊያናግሩት ነው። ኢየሱስ የቤተ መቅደሱ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ እንደማይቀር ስለተናገረ ጉዳዩ አሳስቧቸዋል። ይሁንና ያሳሰባቸው ሌላም ነገር አለ። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 12:40) በተጨማሪም ‘የሰው ልጅ ስለሚገለጥበት ቀን’ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:30) እነዚህ ሐሳቦች አሁን ቤተ መቅደሱን አስመልክቶ ከተናገረው ነገር ጋር የተያያዙ ናቸው? ሐዋርያቱ ይህን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮባቸዋል። በመሆኑም “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።—ማቴዎስ 24:3

ይህን ያሉት በቅርብ ርቀት የሚታያቸው ቤተ መቅደስ የሚጠፋበትን ጊዜ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የሰው ልጅ ስለሚገኝበት ጊዜ ጠይቀውታል። ደቀ መዛሙርቱ “ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ” ስለተጓዘ “አንድ መስፍን” ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ያስታውሱ ይሆናል። (ሉቃስ 19:11, 12) ከዚህም ሌላ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለማወቅ ፈልገዋል።

ኢየሱስ የሰጠው ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ መልስ፣ በወቅቱ ያለው የአይሁድ ሥርዓትና ቤተ መቅደሱ የሚጠፋበትን ጊዜ የሚጠቁም ምልክት ያካተተ ነው። ምልክቱ ግን በዚህ ብቻ አይወሰንም። ይህ ምልክት፣ ወደፊት ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ ላይ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የእሱን ‘መገኘት’ እንዲገነዘቡና በምድር ላይ ያለው ሥርዓት የሚደመደምበትን ጊዜ መቅረብ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሐዋርያቱ የኢየሱስ ትንቢት ሲፈጸም ይመለከታሉ። በእርግጥም ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገራቸው በርካታ ነገሮች እነሱ በሕይወት እያሉ መፈጸም ጀመሩ። በመሆኑም ከ37 ዓመታት በኋላ ማለትም በ70 ዓ.ም. የሚኖሩ ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ የአይሁድ ሥርዓትና ቤተ መቅደሱ የሚጠፉበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ሁኔታው እንግዳ አልሆነባቸውም። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል እስከ 70 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ሁሉም አይደሉም። ታዲያ ወደፊት፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚጠቁም ምን ነገር ይፈጸማል? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የተናገረው ነገር መልሱን ይሰጠናል።

ኢየሱስ “ጦርነትና የጦርነት ወሬ” እንደሚሰማ እንዲሁም “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ” እንደሚነሳ ተነበየ። (ማቴዎስ 24:6, 7) በተጨማሪም “ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል” አለ። (ሉቃስ 21:11) ኢየሱስ “ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቃቸው። (ሉቃስ 21:12) ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። ክፋት እየበዛ ይሄዳል፤ እንዲሁም የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 24:14

 ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ኢየሩሳሌም በሮማውያን ከመጥፋቷ በፊትና በምትጠፋበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ የተፈጸመ ቢሆንም ምልክቱ ከዚያ በኋላ ታላቅ ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? ኢየሱስ የተናገረው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትንቢት በዘመናችን ዋነኛ ፍጻሜውን እያገኘ እንደሆነ የሚጠቁመውን ማስረጃስ እየተመለከትክ ነው?

ኢየሱስ፣ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሰጠው ምልክት አንዱ ገጽታ “ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’” መታየቱ ነው። (ማቴዎስ 24:15) በ66 ዓ.ም. የጣዖት አርማ ወይም ምልክት የያዘው የሮም “ጦር ሠራዊት” ሲመጣ ይህ “ርኩስ ነገር” ታይቷል። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከበው የግንቡን የተወሰነ ክፍል ማፍረስ ጀመሩ። (ሉቃስ 21:20) በመሆኑም ይህ “ርኩስ ነገር” መቆም በሌለበት ቦታ ማለትም አይሁዳውያን ‘እንደተቀደሰ’ በሚቆጥሩት ስፍራ ቆመ።

ኢየሱስ ቀጥሎም “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል” አለ። በ70 ዓ.ም. ሮማውያን ኢየሩሳሌምን አጠፉ። በአይሁዳውያን ‘ቅድስት ከተማ’ እና በቤተ መቅደሱ ላይ የደረሰው ይህ ጥፋት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ታላቅ መከራ ሆኗል። (ማቴዎስ 4:5፤ 24:21) ይህ ጥፋት ኢየሩሳሌምም ሆነች የአይሁድ ሕዝብ ከዚያ ቀደም ካጋጠማቸው ሁሉ የባሰ ነው፤ አይሁዳውያን ለበርካታ ዘመናት ሲከተሉት የነበረው የተደራጀ የአምልኮ ሥርዓት እንዲያበቃ አድርጓል። ከዚህ አንጻር፣ የኢየሱስ ትንቢት ከጊዜ በኋላ የሚኖረው ታላቅ ፍጻሜ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ትንቢቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መረጋጋት

ኢየሱስ፣ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱንና የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ ስለሚጠቁመው ምልክት ከሐዋርያቱ ጋር ያደረገው ውይይት ገና አልተቋጨም። አሁን ደግሞ “ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት” እንዳያታልሏቸው ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች “ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ” ለማሳት እንደሚሞክሩ ተናገረ። (ማቴዎስ 24:24) ሆኖም እነዚህ የተመረጡ ሰዎች አይታለሉም። ሐሰተኛ ክርስቶሶች በዓይን ይታያሉ። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በሥልጣኑ የሚገኘው በማይታይ ሁኔታ ነው።

ኢየሱስ አሁን ባለንበት ሥርዓት መጨረሻ ላይ ስለሚኖረው ታላቅ መከራ ሲናገር “ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ” አለ። (ማቴዎስ 24:29) ይህን አስፈሪ ሐሳብ የሰሙት ሐዋርያት ምን እንደሚፈጸም በትክክል ባያውቁም ሁኔታው አስደንጋጭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

እነዚህ አስፈሪ ክስተቶች ሰዎች ምን እንዲሰማቸው ያደርጋሉ? ኢየሱስ “የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ” አለ። (ሉቃስ 21:26) በእርግጥም ኢየሱስ በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ጊዜ እንደሚመጣ እየገለጸ ነው።

ሆኖም ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ “በኃይልና በታላቅ ክብር” በሚመጣበት ጊዜ የሚያዝኑት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ ለሐዋርያቱ በግልጽ የነገራቸው መሆኑ የሚያበረታታ ነው። (ማቴዎስ 24:30) “ለተመረጡት ሲባል” አምላክ ጣልቃ እንደሚገባ ኢየሱስ ቀደም ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 24:22) ታዲያ እነዚያ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የገለጻቸው አስደንጋጭ ክንውኖች ሲፈጸሙ ምን ሊያደርጉ ይገባል? ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚል ማበረታቻ ሰጣቸው።—ሉቃስ 21:28

ይሁንና ኢየሱስ በተነበየው በዚያ ዘመን የሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው መቅረቡን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ በለስ ዛፍ የሚገልጽ ምሳሌ ሰጠ፦ “ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ። በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።”—ማቴዎስ 24:32-34

ከዚህ አንጻር፣ ደቀ መዛሙርቱ የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ሲመለከቱ መጨረሻው መቅረቡን ሊገነዘቡ ይገባል። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮች በሚከናወኑበት በዚያ ጊዜ ለሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ምክር ሰጠ፦

“ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም። በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።  ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:36-39) ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ ከሚገኝበት ጊዜ ጋር ያወዳደረው ክንውን ይኸውም በኖኅ ዘመን የመጣው የጥፋት ውኃ መላውን ዓለም ያዳረሰ ነው።

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆነው ኢየሱስን እያዳመጡ ያሉት ሐዋርያት ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት እንደሚገነዘቡ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል። ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋልና። እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ሉቃስ 21:34-36

ኢየሱስ፣ የተናገረው ትንቢት በተወሰነ ዘመን ወይም አካባቢ ላይ ብቻ የሚፈጸም እንዳልሆነ በድጋሚ እየጠቆመ ነው። እየተናገረ ያለው ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ ስለሚፈጸሙና ኢየሩሳሌምን ወይም የአይሁድን ብሔር ብቻ ስለሚነኩ ክንውኖች አይደለም። ከዚህ ይልቅ “በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ” ስለሚደርሱ ክንውኖች መግለጹ ነው።

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምንጊዜም ንቁና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ተናገረ። ይህን ማስጠንቀቂያ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽም ሌላ ምሳሌ ተጠቀመ፦ “ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ክፍለ ሌሊት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር። ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።”—ማቴዎስ 24:43, 44

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምክንያት እንዳለም ቀጥሎ ገለጸ። እሱ የተናገረው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ንቁ የሆነና በሥራ የተጠመደ “ባሪያ” እንደሚኖር አረጋገጠላቸው። ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ በቀላሉ በአእምሯቸው ሊስሉት የሚችሉ ሁኔታ ጠቀሰ፦ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው? ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” ይሁንና ያ “ባሪያ” ክፉ ቢሆንና ሌሎችን ቢበድል ጌታው “ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል።”—ማቴዎስ 24:45-51፤ ከሉቃስ 12:45, 46 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስ ይህን ሲል ግን የተወሰኑ ተከታዮቹ እንደ ክፉ ባሪያ ዓይነት ዝንባሌ እንደሚኖራቸው መግለጹ አይደለም። ታዲያ ለደቀ መዛሙርቱ ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? ምንጊዜም ንቁ እንዲሆኑና በሥራ እንዲጠመዱ ይጠብቅባቸዋል፤ ይህንንም ቀጥሎ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ግልጽ ያደርገዋል።