በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 66

ለዳስ በዓል ኢየሩሳሌም ተገኘ

ለዳስ በዓል ኢየሩሳሌም ተገኘ

ዮሐንስ 7:11-32

  • ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አስተማረ

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ታዋቂ ሆኗል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ተአምራቱን አይተዋል፤ ስላከናወናቸው ነገሮች የሚገልጽ ወሬም በመላ አገሪቱ ተሰራጭቷል። አሁን ሕዝቡ የዳስ በዓልን ለማክበር በኢየሩሳሌም በተሰበሰበበት ወቅት ብዙዎች እሱን መፈለግ ጀመሩ።

ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ነው። አንዳንዶች “እሱ ጥሩ ሰው ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም። እሱ ሕዝቡን ያሳስታል” ይላሉ። (ዮሐንስ 7:12) በበዓሉ መክፈቻ ቀናት በሕዝቡ መካከል ስለ ኢየሱስ እንዲህ ያለ ጉምጉምታ እየተሰማ ነው። ይሁንና ሕዝቡ በሙሉ የአይሁድ መሪዎችን ስለሚፈሩ እሱን ደግፎ በግልጽ የሚናገር ሰው የለም።

በበዓሉ አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ። ከሕዝቡ መካከል ብዙዎች አስደናቂ በሆነው የማስተማር ችሎታው ተገረሙ። ኢየሱስ በረቢዎች ትምህርት ቤት ገብቶ ስላልተማረ አይሁዳውያን በጣም ተገርመው “ይህ ሰው ትምህርት ቤት ገብቶ ሳይማር ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዴት እንዲህ ሊያውቅ ቻለ?” አሉ።—ዮሐንስ 7:15

ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው። ማንም የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ይህ ትምህርት ከአምላክ የመጣ ይሁን ከራሴ ለይቶ ያውቃል።” (ዮሐንስ 7:16, 17) የኢየሱስ ትምህርት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚስማማ በመሆኑ የራሱን ሳይሆን የአምላክን ክብር እንደሚፈልግ በግልጽ ማየት ይቻላል።

ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ሕጉን የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም? ሆኖም አንዳችሁም ሕጉን አትታዘዙም። እኔን ለመግደል የምትፈልጉት ለምንድን ነው?” በሕዝቡ መካከል ያሉ አንዳንዶች፣ ምናልባትም ለበዓሉ ከሌላ ቦታ የመጡት ኢየሱስን ለመግደል የተጠነሰሰውን ሴራ አያውቁም። እንዲህ ያለውን አስተማሪ ለመግደል የሚፈልግ ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ሆነባቸው። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ የተናገረው፣ የሆነ ችግር ቢኖርበት እንደሆነ አሰቡ። “አንተ ጋኔን አለብህ። ሊገድልህ የፈለገው ደግሞ ማን ነው?” አሉት።—ዮሐንስ 7:19, 20

ለነገሩ ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በሰንበት ቀን አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ የአይሁድ መሪዎች ሊገድሉት ሞክረው ነበር። አሁን ኢየሱስ አንድ የሚያመራምር ሐሳብ በማንሳት ምክንያታዊ አለመሆናቸውን ጠቆመ። በሕጉ መሠረት ወንዶች ልጆች ስምንት ቀን ሲሞላቸው በሰንበት ቀን እንኳ እንደሚገረዙ አስታወሳቸው። ከዚያም እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “የሙሴ ሕግ እንዳይጣስ ሲባል በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ እኔ በሰንበት አንድን ሰው መፈወሴ ይህን ያህል ሊያስቆጣችሁ ይገባል? የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።”—ዮሐንስ 7:23, 24

ይህን ጉዳይ የሚያውቁ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ አሉ፦ “[ገዢዎቹ] ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለም እንዴ? እሱ ግን ይኸው በአደባባይ እየተናገረ ነው፤ እነሱም ምንም አላሉትም። ገዢዎቹ ይህ ሰው በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ አስበው ይሆን?” ታዲያ ሕዝቡ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ መሆኑን ያላመኑት ለምንድን ነው? “እኛ ይህ ሰው ከየት እንደመጣ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከየት እንደመጣ ማንም አያውቅም” ብለው ተናገሩ።—ዮሐንስ 7:25-27

ኢየሱስ እዚያው ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያለ እንዲህ በማለት መለሰላቸው፦ “እኔ ማን እንደሆንኩም ሆነ ከየት እንደመጣሁ ታውቃላችሁ። የመጣሁትም በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤ ሆኖም የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ እናንተም አታውቁትም። እኔ ግን የእሱ ተወካይ ሆኜ የመጣሁ ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፤ የላከኝም እሱ ነው።” (ዮሐንስ 7:28, 29) እንዲህ ብሎ በግልጽ በመናገሩ አንዳንዶች ሊይዙት ይኸውም ሊያስሩት አሊያም ሊገድሉት ሞከሩ። ሆኖም ኢየሱስ የሚሞትበት ሰዓት ገና ስላልደረሰ አልተሳካላቸውም።

ያም ሆኖ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ፤ እንዲህ ማድረጋቸውም ተገቢ ነው። ኢየሱስ በውኃ ላይ ሄዷል፣ ነፋስን ጸጥ አሰኝቷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት ዳቦና ዓሣ በተአምር መግቧል፣ የታመሙትን ፈውሷል፣ ሽባዎች እንዲሄዱ አድርጓል፣ የዓይነ ስውሮችን ዓይን አብርቷል፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸውን ፈውሷል፣ አልፎ ተርፎም የሞቱ ሰዎችን እንኳ አስነስቷል። በእርግጥም ሕዝቡ “ክርስቶስስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው የበለጠ ብዙ ተአምራዊ ምልክት ያደርጋል እንዴ?” ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው።—ዮሐንስ 7:31

ፈሪሳውያን ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ የሚያወራውን ሲሰሙ ከካህናት አለቆቹ ጋር ተባብረው እሱን ለማስያዝ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኩ።