በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 91

አልዓዛር ከሞት ተነሳ

አልዓዛር ከሞት ተነሳ

ዮሐንስ 11:38-54

  • የአልዓዛር ትንሣኤ

  • የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል አቀደ

ኢየሱስ በቢታንያ አቅራቢያ ከማርታ ከዚያም ከማርያም ጋር ከተገናኘ በኋላ ወደ አልዓዛር መቃብር አብረው ሄዱ። መቃብሩ ዋሻ ሲሆን መግቢያው በድንጋይ ተዘግቷል። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። ማርታ፣ ኢየሱስ ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ስላልገባት “ጌታ ሆይ፣ አራት ቀን ስለሆነው አሁን ይሸታል” አለች። ኢየሱስ ግን “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት።—ዮሐንስ 11:39, 40

ስለዚህ ድንጋዩን አነሱት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ እየተመለከተ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ይህን ያልኩት ግን እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።” ኢየሱስ በሕዝቡ ፊት መጸለዩ፣ ቀጥሎ የሚያከናውነውን ነገር ከአምላክ ባገኘው ኃይል እንደሚፈጽመው በቦታው ያሉት ሰዎች እንዲያውቁ ያደርጋል። ከዚያም በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!”  አለ። አልዓዛር እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ ተጠምጥሞ ነበር። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ” አላቸው።—ዮሐንስ 11:41-44

ማርያምንና ማርታን ለማጽናናት የመጡ በርካታ አይሁዳውያን ይህን ተአምር ሲመለከቱ በኢየሱስ አመኑ። ሌሎቹ ግን ኢየሱስ የፈጸመውን ነገር ሄደው ለፈሪሳውያን ተናገሩ። በመሆኑም ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች፣ ሳንሄድሪን የተባለው የአይሁድ ከፍተኛ የፍርድ ሸንጎ እንዲሰበሰብ ጥሪ አደረጉ። ሊቀ ካህናቱ ቀያፋም የዚህ ሸንጎ አባል ነው። ከሸንጎው አባላት አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል” በማለት በምሬት ተናገሩ። (ዮሐንስ 11:47, 48) እነዚህ ሰዎች፣ ኢየሱስ “ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች” እንዳደረገ የተመለከቱ የዓይን ምሥክሮች የተናገሩትን ቢሰሙም አምላክ በእሱ አማካኝነት እያደረገ ባለው ነገር አልተደሰቱም። በዋነኝነት ያሳሰባቸው ቦታቸውና ሥልጣናቸው ነው።

ሰዱቃውያን ደግሞ በትንሣኤ ስለማያምኑ የአልዓዛር ከሞት መነሳት ለእነሱ ታላቅ ሽንፈት ነው። ሰዱቃዊ የሆነው ቀያፋ በዚህ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ደግሞም ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ፣ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት እንደሚሻል ማሰብ ተስኗችኋል።”—ዮሐንስ 11:49, 50፤ የሐዋርያት ሥራ 5:17፤ 23:8

ቀያፋ “ይህን የተናገረው ከራሱ አመንጭቶ” አይደለም፤ ቅዱስ ኃላፊነት ያለው በመሆኑ ይህን እንዲናገር ያነሳሳው አምላክ ነው። ቀያፋ ይህን ሲናገር፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ያላቸውን ሥልጣንና ተሰሚነት ኢየሱስ ይበልጥ እንዳያዳክምባቸው መገደል እንዳለበት መግለጹ ነው። ሆኖም ቀያፋ የተናገረው ትንቢት፣ የኢየሱስ ሞት ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ‘ተበታትነው ላሉት የአምላክ ልጆች’ በሙሉ ቤዛ እንደሚሆን ይጠቁማል።—ዮሐንስ 11:51, 52

ቀያፋ፣ የሳንሄድሪን ሸንጎ ኢየሱስን ለመግደል እንዲወስን ማግባባት ቻለ። የኢየሱስ ወዳጅና የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል የሆነው ኒቆዲሞስ ይህን ሴራ ለኢየሱስ ይነግረው ይሆን? ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ፣ አምላክ ከወሰነው ጊዜ በፊት እንዳይሞት ሲል የኢየሩሳሌምን አካባቢ ለቆ ሄደ።