በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 39

መልእክቱን ለማይቀበል ትውልድ ወዮለት

መልእክቱን ለማይቀበል ትውልድ ወዮለት

ማቴዎስ 11:16-30 ሉቃስ 7:31-35

  • ኢየሱስ አንዳንድ ከተሞችን ወቀሰ

  • ለሰዎች እረፍት እንደሚሰጥ ተናገረ

ኢየሱስ ለመጥምቁ ዮሐንስ ከፍ ያለ ግምት አለው፤ ይሁንና ብዙዎች ዮሐንስን የሚመለከቱት እንዴት ነው? ኢየሱስ በዘመኑ ስላለው ትውልድ ሲናገር እንደሚከተለው ብሏል፦ “በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’”—ማቴዎስ 11:16, 17

ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው? ሐሳቡን እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ።” (ማቴዎስ 11:18, 19) ዮሐንስ የናዝራውያን ዓይነት ቀላል ሕይወት መርቷል፤ ሌላው ቀርቶ የወይን ጠጅ እንኳ አልጠጣም፤ ያም ቢሆን ሰዎቹ ጋኔን እንዳለበት ተናግረዋል። (ዘኁልቁ 6:2, 3፤ ሉቃስ 1:15) ኢየሱስ ደግሞ የኖረው እንደ ማንኛውም ሰው ነው። የሚበላውና የሚጠጣው ልከኝነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ቢሆንም ሰዎች መጠኑን እንዳለፈ ተናግረዋል። በእርግጥም ሕዝቡን ማስደሰት አስቸጋሪ ነው!

ኢየሱስ በዘመኑ ያለውን ትውልድ፣ በገበያ ስፍራ ካሉ ልጆች ጋር አመሳስሎታል። እነዚህ ልጆች፣ ጓደኞቻቸው ዋሽንት ቢነፉላቸውም አልጨፈሩም፤ ሙሾ ቢያወርዱላቸውም አላዘኑም። ኢየሱስ “የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:16, 19) አዎን፣ ‘ሥራቸው’ ማለትም ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ያከናወኑት ነገር በእነሱ ላይ የቀረቡት ክሶች ሐሰት መሆናቸውን ያረጋግጣል።

ኢየሱስ በዘመኑ ያለው ትውልድ መልእክቱን የማይቀበል እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ተአምራት የፈጸመባቸውን ሦስት ከተሞች ማለትም ኮራዚንን፣ ቤተሳይዳንና ቅፍርናሆምን ለይቶ በመጥቀስ ነቀፋቸው። ተአምራቱን የፊንቄ ከተሞች በሆኑት በጢሮስና በሲዶና ፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ሕዝቡ ንስሐ ይገቡ እንደነበር ተናገረ። በአገልግሎቱ ወቅት ማረፊያውና የእንቅስቃሴው ማዕከል አድርጎ ይጠቀምባት የነበረችውን ቅፍርናሆምንም ጠቅሷል። በዚህች ከተማም እንኳ ብዙዎች መልእክቱን አልተቀበሉትም። ኢየሱስ ይህችን ከተማ “በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ምድር ይቀልላታል” ብሏታል።—ማቴዎስ 11:24

ቀጥሎም ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን አወደሰ፤ ይህን ያደረገው ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን “ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች” ሰውሮ እንደ ትናንሽ ልጆች ለሆኑ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ስለገለጠላቸው ነው። (ማቴዎስ 11:25) እንዲህ ላሉት ሰዎች የሚከተለውን ማራኪ ግብዣ አቅርቦላቸዋል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30

ኢየሱስ እረፍት የሚሰጠው እንዴት ነው? የሃይማኖት መሪዎቹ በሕዝቡ ላይ የተለያዩ ወጎችን በመጫን እንደ ባሪያ ይጨቁኗቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል ከሰንበት ጋር የተያያዙትን የማያፈናፍኑ ደንቦች እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ኢየሱስ ግን ከእነዚህ ልማዶች ነፃ የሆነውን የአምላክን እውነት ለሕዝቡ በማስተማር እረፍት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም በፖለቲካ ባለሥልጣናት የጭቆና አገዛዝ መንፈሳቸው ለተሰበረና ኃጢአታቸው እንደ ሸክም ሆኖ ለደቆሳቸው ሰዎች እፎይታ የሚያገኙበትን መንገድ ያሳያቸዋል። ኢየሱስ፣ እንዲህ ላሉት ሰዎች ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸውና ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጽላቸዋል።

የኢየሱስን ልዝብ ቀንበር የሚሸከሙ ሁሉ ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰን፣ ሩኅሩኅና መሐሪ የሆነውን ሰማያዊ አባታችንን ማገልገል ይችላሉ። እንዲህ ማድረግ ደግሞ ከባድ ሸክም አይሆንባቸውም፤ ምክንያቱም የአምላክ መመሪያዎች በፍጹም ከባድ አይደሉም።—1 ዮሐንስ 5:3