በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 79

በቅርቡ ጥፋት የሚመጣው ለምንድን ነው?

በቅርቡ ጥፋት የሚመጣው ለምንድን ነው?

ሉቃስ 13:1-21

  • ኢየሱስ በሁለት አሳዛኝ ክስተቶች ላይ ተመሥርቶ ትምህርት ሰጠ

  • የአካል ጉዳተኛ የሆነችን ሴት በሰንበት ፈወሰ

ኢየሱስ፣ ሕዝቡ በአምላክ ፊት ስላላቸው አቋም እንዲያስቡ ለማበረታታት ብዙ ዘዴዎችን ሲጠቀም ቆይቷል። በአንድ ፈሪሳዊ ቤት ደጅ ላይ ተሰብስቦ ከነበረው ሕዝብ ጋር ከተነጋገረ በኋላ፣ ሰዎቹን ለማስተማር የሚያስችለው ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ።

በዚያ ካሉት ሰዎች አንዳንዶቹ፣ ስለ አንድ አሳዛኝ ክንውን ተናገሩ። ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ “ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ለኢየሱስ አወሩለት።” (ሉቃስ 13:1) ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?

እነዚህ የገሊላ ሰዎች የተገደሉት ጲላጦስ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ውኃ የሚያስገባ ቦይ ለማሠራት ሲል ከቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ገንዘብ መውሰዱን በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በተቃወሙ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ጲላጦስ ገንዘቡን የወሰደው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ተባብረውት ይሆናል። ይህን ሁኔታ ለኢየሱስ ያወሩለት ግለሰቦች፣ የገሊላ ሰዎች እንዲህ ያለ አሳዛኝ ነገር የደረሰባቸው ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን በዚህ አልተስማማም።

“እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ይበልጥ ኃጢአተኞች እንደሆኑ አድርጋችሁ ታስባላችሁ?” በማለት ከጠየቃቸው በኋላ “በፍጹም” በማለት መለሰ። ከዚያም “ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ” በማለት የተፈጠረውን ክስተት አይሁዳውያኑን ለማስጠንቀቅ ተጠቀመበት። (ሉቃስ 13:2, 3) ኢየሱስ በመቀጠል ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ጠቀሰ፤ ይህም ከውኃው ቦይ ግንባታ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የተፈጸመ ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስ “የሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት 18 ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ በደለኞች የነበሩ ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው። (ሉቃስ 13:4) ሕዝቡ እነዚያ ሰዎች የሞቱት መጥፎ ድርጊት ስለፈጸሙ እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። አሁንም ኢየሱስ በዚህ አልተስማማም። “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙ እንደሚችሉና ይህ አደጋ የተከሰተውም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያውቃል። (መክብብ 9:11) ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ከዚህ ክስተት ትምህርት ማግኘት አለባቸው። ኢየሱስ “ንስሐ ካልገባችሁ ሁላችሁም ልክ እንደ እነሱ ትጠፋላችሁ” አላቸው። (ሉቃስ 13:5) ይሁንና ኢየሱስ ይህንን ነጥብ በዚህ ወቅት ያጎላው ለምንድን ነው?

አገልግሎቱን እያጠናቀቀ በመሆኑ ነው፤ ነጥቡን በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው በወይን እርሻው ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ እሱም ከዛፏ ፍሬ ሊለቅም መጣ፤ ሆኖም ምንም አላገኘባትም። በዚህ ጊዜ የወይን አትክልት ሠራተኛውን ‘ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ሆኖም ምንም አላገኘሁባትም። ስለዚህ ቁረጣት! ለምን በከንቱ ቦታ ትይዛለች?’ አለው። እሱም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታዬ፣ ዙሪያዋን ቆፍሬ ፍግ ላድርግባትና እስቲ ለአንድ ዓመት ደግሞ እንያት። ወደፊት ፍሬ ካፈራች ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ትቆርጣታለህ።’”—ሉቃስ 13:6-9

ኢየሱስ፣ አይሁዳውያን እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ከሦስት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ደክሟል። ሆኖም የድካሙ ፍሬ ተደርገው ሊቆጠሩ የሚችሉት፣ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። አሁን በአገልግሎቱ አራተኛውን ዓመት የያዘ ሲሆን ጥረቱን እያፋፋመ ነው። የበለሱን ዛፍ ዙሪያ ቆፍሮ ፍግ እያደረገበት በሌላ አባባል በይሁዳና በፔሪያ ለሚገኙ አይሁዳውያን እየሰበከና እያስተማረ ነው። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ኢየሱስን የተቀበሉት ጥቂት አይሁዳውያን ብቻ ናቸው። በጥቅሉ ሲታይ ብሔሩ ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ በማለቱ ወደ ጥፋት እየተጓዘ ነው።

 ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ብዙም ሳይቆይ የተፈጸመው ነገር አብዛኞቹ አይሁዳውያን እሱን መቀበል እንዳልፈለጉ የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። ዕለቱ ሰንበት ሲሆን ኢየሱስ በምኩራብ ውስጥ እያስተማረ ነው። በዚያም ባደረባት ክፉ መንፈስ የተነሳ ለ18 ዓመት ጎብጣ የኖረች ሴት ተመለከተ። ኢየሱስ በጣም ስላዘነላት “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” አላት። (ሉቃስ 13:12) እጁንም ሲጭንባት ወዲያው ቀጥ አለች፤ አምላክንም ማመስገን ጀመረች።

የምኩራቡ አለቃ ይህን ሲያይ ተቆጥቶ ሕዝቡን “ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላቸው። (ሉቃስ 13:14) የምኩራቡ አለቃ ኢየሱስ የመፈወስ ኃይል እንዳለው አልካደም፤ እሱ ያወገዘው ሕዝቡ ለመፈወስ በሰንበት ቀን መምጣታቸውን ነው! ኢየሱስ የሚከተለውን ምክንያታዊ ነጥብ በማንሳት ምላሽ ሰጠ፦ “እናንተ ግብዞች፣ እያንዳንዳችሁ በሰንበት ቀን በሬያችሁን ወይም አህያችሁን ከጋጣው ፈታችሁ ውኃ ለማጠጣት ትወስዱ የለም? ታዲያ የአብርሃም ልጅ የሆነችውና 18 ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ የኖረችው ይህች ሴት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራቷ መፈታት አይገባትም?”—ሉቃስ 13:15, 16

ተቃዋሚዎቹ በኀፍረት ተሸማቀቁ፤ ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ሲፈጽም ባዩት አስደናቂ ነገር ተደሰቱ። ከዚያም ኢየሱስ፣ በገሊላ ባሕር ጀልባ ላይ ሆኖ የተናገራቸውን ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹ ሁለት ትንቢታዊ ምሳሌዎች በይሁዳ ደገመ።—ማቴዎስ 13:31-33፤ ሉቃስ 13:18-21