በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 125

ኢየሱስ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ

ኢየሱስ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ

ማቴዎስ 26:57-68 ማርቆስ 14:53-65 ሉቃስ 22:54, 63-65 ዮሐንስ 18:13, 14, 19-24

  • ኢየሱስ ወደ ቀድሞው ሊቀ ካህናት ወደ ሐና ተወሰደ

  • የሳንሄድሪን ሸንጎ የመራው ሕጋዊ ያልሆነ የፍርድ ሂደት

ኢየሱስ እንደ ተራ ወንጀለኛ ከታሰረ በኋላ ወደ ሐና ተወሰደ፤ ሐና፣ ኢየሱስ ልጅ እያለ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መምህራኑን ባስደመመበት ወቅት ሊቀ ካህናት ነበር። (ሉቃስ 2:42, 47) ከሐና ወንዶች ልጆች አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ ሊቀ ካህናት ሆነው አገልግለዋል፤ አሁን ደግሞ ይህን ቦታ የያዘው የሐና አማች የሆነው ቀያፋ ነው።

ኢየሱስ፣ ሐና ቤት እያለ ቀያፋ የሳንሄድሪንን ሸንጎ ለማሰባሰብ ጊዜ አገኘ። ይህ ሸንጎ ሊቀ ካህናቱንና ቀደም ሲል ይህን ቦታ ይዘው የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 71 አባላት አሉት።

ሐና “ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ። አይሁዳውያን ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በቤተ መቅደሱ ሁልጊዜ አስተምር ነበር፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም። እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? እኔ የነገርኳቸውን ነገር የሰሙትን ሰዎች ጠይቃቸው።”—ዮሐንስ 18:19-21

በዚህ ጊዜ አጠገቡ ከቆሙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አንዱ ኢየሱስን በጥፊ መታውና “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነው?” ሲል አረመው። ኢየሱስ ግን ምንም ጥፋት እንዳልሠራ ስለሚያውቅ “የተሳሳተ ነገር ተናግሬ ከሆነ ስህተቴ ምን እንደሆነ ንገረኝ፤ የተናገርኩት ነገር ትክክል ከሆነ ግን ለምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። (ዮሐንስ 18:22, 23) ከዚያም ሐና ኢየሱስን ወደ አማቹ ወደ ቀያፋ ላከው።

 በዚህ ወቅት መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ይኸውም ሊቀ ካህናቱና የሕዝቡ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጸሐፍት ተሰብስበዋል። የተሰበሰቡት በቀያፋ ቤት ነው። በፋሲካ ሌሊት እንዲህ ዓይነት ችሎት ማካሄድ ሕጉን የሚጥስ ቢሆንም ይህ የክፋት ዓላማቸውን ከማከናወን አላገዳቸውም።

እነዚህ ሰዎች ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍርድ እንደማይሰጡ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ጊዜ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ኢየሱስን ለመግደል ወስነዋል። (ዮሐንስ 11:47-53) ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለመያዝና ለመግደል ሴራ ጠንስሰዋል። (ማቴዎስ 26:3, 4) በእርግጥም ኢየሱስ ሞት የተፈረደበት ገና ችሎት ፊት ሳይቀርብ ነው!

የካህናት አለቆቹና ሌሎቹ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ሕጋዊ ያልሆነ ስብሰባ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ኢየሱስን ለመወንጀል የሚያበቃ ክስ ለማግኘት ሲሉ የሐሰት መረጃ የሚያቀርቡ ምሥክሮችን ለማግኘት እየሞከሩ ነው። ብዙ ሰዎች ያገኙ ቢሆንም ምሥክርነታቸው ሊስማማ አልቻለም። በመጨረሻ ሁለት ሰዎች ቀረቡና “‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል” አሉ። (ማርቆስ 14:58) ይሁንና የእነዚህ ሰዎች ቃል እንኳ ሙሉ በሙሉ ሊስማማ አልቻለም።

ከዚያም ቀያፋ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው። (ማርቆስ 14:60) ኢየሱስ ግን እርስ በርሱ የማይስማማ ሐሳብ የሰጡት ምሥክሮች ላቀረቡት የሐሰት ክስ ምንም መልስ አልሰጠም። ስለዚህ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሌላ ዘዴ ተጠቀመ።

ቀያፋ፣ ማንኛውም ሰው የአምላክ ልጅ እንደሆነ ቢናገር አይሁዳውያን በጣም እንደሚቆጡ ያውቃል። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ አምላክ አባቱ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ አይሁዶች ‘ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል እንዳደረገ’ በመግለጽ ሊገድሉት ፈልገው ነበር። (ዮሐንስ 5:17, 18፤ 10:31-39) ቀያፋ ይህን ስሜታቸውን ስለሚያውቅ “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” በማለት ተንኮል ያዘለ ጥያቄ አቀረበለት። (ማቴዎስ 26:63) ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተናግሮ ያውቃል። (ዮሐንስ 3:18፤ 5:25፤ 11:4) አሁን ይህን ባይናገር የአምላክ ልጅ እንዲሁም ክርስቶስ መሆኑን እንደ መካድ ሊቆጠር ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለ።—ማርቆስ 14:62

በዚህ ጊዜ ቀያፋ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር በጣም የሚያስቆጣ እንደሆነ ለማስመሰል ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፦ “አምላክን ተሳድቧል! ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል? ስድቡን እንደሆነ እናንተም ሰምታችኋል። እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” የሸንጎው አባላትም “ሞት ይገባዋል” በማለት ፍትሕ የጎደለው ብያኔ ሰጡ።—ማቴዎስ 26:65, 66

ከዚያም በኢየሱስ ላይ ያሾፉበትና በቡጢ ይመቱት ጀመር። ሌሎች ደግሞ በጥፊ መቱት፤ ምራቃቸውንም ተፉበት። ፊቱን ሸፍነው እየመቱት “እስቲ ትንቢት ተናገር! የመታህ ማን ነው?” እያሉ አፌዙበት። (ሉቃስ 22:64) በሌሊት በተካሄደው ሕገ ወጥ ችሎት ላይ የአምላክ ልጅ ግፍ እየደረሰበት ነው!