በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 116

በመጨረሻው ፋሲካ ላይ ትሕትናን ማስተማር

በመጨረሻው ፋሲካ ላይ ትሕትናን ማስተማር

ማቴዎስ 26:20 ማርቆስ 14:17 ሉቃስ 22:14-18 ዮሐንስ 13:1-17

  • ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን ፋሲካ በላ

  • የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትምህርት ሰጠ

ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለፋሲካ ዝግጅት ለማድረግ ቀደም ብለው ኢየሩሳሌም ገብተዋል። ትንሽ ቆየት ብሎ ኢየሱስና ሌሎቹ አሥር ሐዋርያት ወደዚያ ሄዱ። ጊዜው ከቀትር በኋላ ሲሆን ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች ከደብረ ዘይት ተራራ ሲወርዱ ፀሐይዋ በምዕራብ አቅጣጫ እየጠለቀች ነው። ኢየሱስ ሞቶ ከመነሳቱ በፊት ከዚህ ተራራ ላይ ሆኖ በቀን አካባቢውን የሚመለከተው ለመጨረሻ ጊዜ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሐዋርያት ወደ ከተማዋ ደረሱና ፋሲካን ወደሚበሉበት ቤት አመሩ። ከዚያም ደረጃዎቹን ወጥተው ወደ ሰፊው ሰገነት ገቡ። ብቻቸውን ሆነው ለሚያከብሩት የፋሲካ በዓል የሚያስፈልጉት ዝግጅቶች ሁሉ ተደርገዋል። ኢየሱስ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር” ስላለ ይህን በዓል በጉጉት ሲጠባበቀው ቆይቷል።—ሉቃስ 22:15

በፋሲካ በዓል ላይ የወይን ጠጅ የያዙ ጥቂት ጽዋዎችን የመቀባበል ልማድ ከበርካታ ዓመታት በፊት ተጀምሮ ነበር። በበዓሉ ላይ ኢየሱስ አንደኛውን ጽዋ ተቀብሎ አምላክን ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንኩ፣ ይህን ጽዋ እየተቀባበላችሁ ጠጡ፤ እላችኋለሁና፣ ከአሁን ጀምሮ የአምላክ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ዳግመኛ አልጠጣም።” (ሉቃስ 22:17, 18) ኢየሱስ ይህን ማለቱ የሚሞትበት ጊዜ መቅረቡን በግልጽ ያሳያል።

ፋሲካን እየበሉ ሳለ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከናወነ። ኢየሱስ ተነስቶ መደረቢያውን ካስቀመጠ በኋላ ፎጣ ወስዶ ወገቡ ላይ አሸረጠ። ከዚያም በአቅራቢያው በሚገኝ የመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨመረ። በአብዛኛው የእንግዶች እግር እንዲታጠብ ዝግጅት የሚያደርገው ጋባዡ ነው፤ ምናልባትም አንድ አገልጋዩ እግራቸውን እንዲያጥብ ያደርግ ይሆናል። (ሉቃስ 7:44) ይሁንና በቦታው ጋባዥ ስለሌለ ኢየሱስ ይህን አገልግሎት ራሱ አከናወነ። ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸው እንዲህ ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ሆኖም ማናቸውም ይህን አላደረጉም። ይህ የሆነው በመካከላቸው ያለው ፉክክር ስላልጠፋ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ እግራቸውን ማጠብ ሲጀምር አፈሩ።

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ “በፍጹም እግሬን አታጥብም” ሲል ተቃወመ። ኢየሱስም “ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ምንም ድርሻ አይኖርህም” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በስሜታዊነት “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ” አለው። ኢየሱስ በሰጠው መልስ ምንኛ ተገርሞ ይሆን! ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “ገላውን የታጠበ ሁለመናው ንጹሕ በመሆኑ ከእግሩ በስተቀር መታጠብ አያስፈልገውም። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ ሁላችሁም ግን አይደላችሁም።”—ዮሐንስ 13:8-10

ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ጨምሮ የ12ቱንም እግር አጠበ። መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ  አስተዋላችሁ? እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ የተላከም ከላከው አይበልጥም። እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ።”—ዮሐንስ 13:12-17

ትሕትና በተግባር የታየበት እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! የኢየሱስ ተከታዮች ከፍ ተደርገው ሊታዩና ሊገለገሉ እንደሚገባ በማሰብ ቀዳሚውን ቦታ ለማግኘት መጣር የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይገባቸዋል፤ ይህን የሚያደርጉት እግር የማጠብን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ሳይሆን በትሕትና እንዲሁም ያለአድልዎ ለማገልገል ፈቃደኛ በመሆን ነው።