በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 93

የሰው ልጅ ይገለጣል

የሰው ልጅ ይገለጣል

ሉቃስ 17:20-37

  • መንግሥቱ በመካከላቸው ነው

  • ኢየሱስ ሲገለጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

ኢየሱስ አሁንም የሚገኘው በሰማርያ አሊያም በገሊላ ነው። ፈሪሳውያን ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት ጠየቁት፤ እነዚህ ሰዎች የአምላክ መንግሥት በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚመጣ ይጠብቃሉ። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “የአምላክ መንግሥት በግልጽ በሚታይ ሁኔታ አይመጣም፤ ሰዎችም ‘እነሆ እዚህ ነው!’ ወይም ‘እዚያ ነው!’ አይሉም። እነሆ፣ የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነውና።”—ሉቃስ 17:20, 21

አንዳንዶች፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በይሖዋ አገልጋዮች ልብ ውስጥ እየገዛ መሆኑን እንደተናገረ ያስቡ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ እያነጋገራቸው ባሉት ፈሪሳውያን ልብ ውስጥ ሊሆን አይችልም። ያም ቢሆን አምላክ የመረጠው የመንግሥቱ ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ አብሯቸው ስላለ ‘የአምላክ መንግሥት በመካከላቸው ነው’ ሊባል ይችላል።—ማቴዎስ 21:5

ፈሪሳውያኑ ከሄዱ በኋላ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ የመንግሥቱን መምጣት በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ ነገር ነገራቸው። በመጀመሪያ፣ በመንግሥቱ ሥልጣን የሚገኝበትን ሁኔታ አስመልክቶ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ግን አታዩትም።” (ሉቃስ 17:22) ኢየሱስ ይህን ሲል የሰው ልጅ በመንግሥቱ መግዛት የሚጀምረው ወደፊት መሆኑን ማመልከቱ ነው። ይህ ጊዜ ከመድረሱ በፊት አንዳንድ ደቀ መዛሙርት መንግሥቱን ለማየት ይጓጉ ይሆናል፤ ሆኖም የሰው ልጅ እንዲመጣ አምላክ የወሰነለት ጊዜ እስኪደርስ በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “ሰዎችም ‘እዚያ ነው!’ ወይም ‘እዚህ ነው!’ ይሏችኋል። ነገር ግን አትሂዱ ወይም አትከተሏቸው። ምክንያቱም መብረቅ ከአንዱ የሰማይ ክፍል እስከ ሌላኛው የሰማይ ክፍል እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል።” (ሉቃስ 17:23, 24) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሐሰት መሲሖችን ከመከተል እንዲቆጠቡ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ኢየሱስ የእውነተኛው መሲሕ መምጣት፣ ሰፊ በሆነ አካባቢ እንደሚታይ መብረቅ እንደሚሆን ተናግሯል። በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚያሳየው ማስረጃ አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል።

ከዚያም ኢየሱስ ወደፊት በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ ሰዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ እንደሚኖራቸው ለማሳየት በጥንት ዘመን የነበሩ ሁኔታዎችን ጠቀሰ፦ “በኖኅ ዘመን እንደተከሰተው ሁሉ በሰው ልጅ ዘመንም እንዲሁ ይሆናል፤ . . . በተመሳሳይም በሎጥ ዘመን እንደተከሰተው ሁሉ እንዲሁ ይሆናል፦ ሰዎች ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይገዙ፣ ይሸጡ፣ ይተክሉና ቤቶችን ይገነቡ ነበር። ሆኖም ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ከሰማይ እሳትና ድኝ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው። የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል።”—ሉቃስ 17:26-30

ኢየሱስ በኖኅና በሎጥ ዘመን የነበሩት ሰዎች የጠፉት እንደ መብላት፣ መጠጣት፣ መግዛት፣ መሸጥ፣ መትከልና ቤት መገንባት ያሉትን የተለመዱ እንቅስቃሴዎች በማከናወናቸው እንደሆነ መግለጹ አይደለም። ኖኅና ሎጥ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ከእነዚህ ነገሮች የተወሰኑትን እንዳደረጉ ግልጽ ነው። ሌሎቹ ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነቶቹን  ተግባሮች ሲያከናውኑ ለአምላክ ፈቃድ ምንም ትኩረት አልሰጡም፤ እንዲሁም የሚኖሩበትን ዘመን አላስተዋሉም። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ለአምላክ ፈቃድ ትኩረት እንዲሰጡና ምንጊዜም ፈቃዱን እንዲያደርጉ እየመከራቸው ነው። በዚህ መንገድ፣ አምላክ ወደፊት ጥፋት ሲያመጣ በሕይወት ለመትረፍ ተከታዮቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሳይቷል።

ደቀ መዛሙርቱ ‘ከኋላቸው ባሉት’ ይኸውም በዓለም ላይ ባሉ ነገሮች ትኩረታቸው እንዳይሰረቅ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በዚያን ቀን በጣሪያ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ እርሻም ላይ ያለ ሰው በኋላው ያለውን ነገር ለመውሰድ አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ።” (ሉቃስ 17:31, 32) የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ ሆናለች።

ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ ለደቀ መዛሙርቱ ማብራራቱን በመቀጠል “በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ላይ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላኛው ግን ይተዋል” አላቸው። (ሉቃስ 17:34) በመሆኑም አንዳንዶች መዳን ሲያገኙ ሌሎች ግን ይተዋሉ፤ ይህም ሕይወታቸውን ያጣሉ ማለት ነው።

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ የት?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም “በድን ባለበት ንስሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው። (ሉቃስ 17:37) በእርግጥም አንዳንዶች፣ ከርቀት መመልከት እንደሚችሉ ንስሮች ይሆናሉ። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ወደ እውነተኛው ክርስቶስ ይኸውም ወደ ሰው ልጅ ይሰበሰባሉ። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ፣ ሕይወት አድን የሆነውን እውነት ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸዋል።