በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 103

ቤተ መቅደሱ እንደገና ጸዳ

ቤተ መቅደሱ እንደገና ጸዳ

ማቴዎስ 21:12, 13, 18, 19 ማርቆስ 11:12-18 ሉቃስ 19:45-48 ዮሐንስ 12:20-27

  • ኢየሱስ አንዲት የበለስ ዛፍ ረገመ፤ ቤተ መቅደሱንም አጸዳ

  • ብዙዎች ሕይወት እንዲያገኙ ኢየሱስ መሞት አለበት

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ከመጡ ወዲህ በቢታንያ ሦስት ቀን አድረዋል። ሰኞ፣ ኒሳን 10 ገና በጠዋቱ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀመሩ። ኢየሱስ ርቦታል። ስለዚህ አንዲት የበለስ ዛፍ ሲመለከት ወደ እሷ ሄደ። ዛፏ ፍሬ ይኖራት ይሆን?

መጋቢት እየተገባደደ ነው፤ በለስ ደግሞ ከሰኔ በፊት አይደርስም። ያም ቢሆን ዛፏ ከወቅቱ ቀደም ብላ ቅጠል አውጥታለች። በመሆኑም ኢየሱስ አስቀድማ አፍርታ ሊሆን እንደሚችል አስቧል። ሆኖም ዛፏ ላይ አንድም ፍሬ አላገኘም። ዛፏ ቅጠል በማውጣቷ ታሳስታለች። ኢየሱስ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። (ማርቆስ 11:14) የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ መድረቅ ጀመረች፤ ይህ ምን ትርጉም እንዳለው ነገ ጠዋት ግልጽ ይሆናል።

ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ኢየሱስ ትናንት ከሰዓት በኋላ ቤተ መቅደሱን ቃኝቶ ነበር፤ ዛሬም ወደዚያው ሄደ። አሁን ግን በመመልከት ብቻ ሳይወሰን፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በ30 ዓ.ም. በተከበረው የፋሲካ በዓል ላይ የወሰደውን እርምጃ ደገመው። (ዮሐንስ 2:14-16) በዚህ ወቅት ኢየሱስ “በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን” ሰዎች አስወጣ። “የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ።” (ማርቆስ 11:15) ዕቃ የተሸከመ ማንኛውም ሰው አቋራጭ ለማግኘት ሲል በቤተ መቅደሱ ግቢ አልፎ እንዳይሄድ ከለከለ።

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ገንዘብ በሚመነዝሩትና እንስሳት በሚሸጡት ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? እንዲህ አለ፦ “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም? እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት።” (ማርቆስ 11:17) ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች፣ ዘራፊዎች ብሎ የጠራቸው ለመሥዋዕት የሚሆኑ እንስሳትን ከእነሱ ከመግዛት ሌላ አማራጭ የሌላቸውን ሰዎች በጣም ውድ ዋጋ ስለሚያስከፍሏቸው ነው። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ንግድ እንደ ዘረፋ ወይም ሌብነት ተመልክቶታል።

የካህናት አለቆችና ጸሐፍት እንዲሁም የሕዝቡ መሪዎች ኢየሱስ ያደረገውን መስማታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም እሱን ለማስገደል እንደገና መንገድ መፈለግ ጀመሩ። ይሁንና አንድ ችግር አጋጠማቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ሕዝቡ ሁሉ እሱን ለመስማት እየጎረፈ በመሆኑ እንዴት ሊያስገድሉት እንደሚችሉ ግራ ገባቸው።

ከአይሁዳውያን በተጨማሪ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችም በፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት መጥተዋል። ከእነዚህም መካከል ለበዓሉ የመጡ ግሪካውያን ይገኙበታል። እነሱም ወደ ፊልጶስ ቀረቡና ኢየሱስን ሊያዩ እንደሚፈልጉ ነገሩት፤ ሰዎቹ ወደ ፊልጶስ የመጡት የግሪክኛ ስም ስላለው ይሆናል። ፊልጶስ፣ ሰዎቹን ከኢየሱስ ጋር ማገናኘቱ ተገቢ መሆኑን ለማረጋገጥ ሳይሆን አይቀርም ጉዳዩን ለእንድርያስ ነገረው። ከዚያም ሁለቱ ሐዋርያት ይህን በተመለከተ ኢየሱስን አነጋገሩት፤ በዚህ ወቅትም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያለ ይመስላል።

ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚሞት ያውቃል፤ በመሆኑም እሱን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተናገድ ወይም ማንነቱን ለማሳወቅ አሁን ጊዜው አይደለም። የሚከተለውን ምሳሌ በመናገር ለሁለቱ ሐዋርያት መልስ ሰጣቸው፦ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አንዲት የስንዴ ዘር መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች አንድ ዘር ብቻ ሆና ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።”—ዮሐንስ 12:23, 24

አንዲት የስንዴ ዘር ያን ያህል ዋጋ ያላት አትመስል ይሆናል። መሬት ላይ ተዘርታ ‘ከሞተች’ ግን ትበቅላለች፤ ውሎ አድሮም ብዙ የስንዴ ዘሮችን የያዘ ዛላ ታፈራለች። በተመሳሳይም ኢየሱስ ፍጹም የሆነ አንድ ሰው ነው። ይሁንና ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከሞተ፣ ልክ እንደ እሱ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያሳዩ በርካታ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ይከፍታል። በመሆኑም ኢየሱስ “ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” በማለት ተናገረ።—ዮሐንስ 12:25

ኢየሱስ ስለ ራሱ ብቻ እየተናገረ አይደለም፤ ምክንያቱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “እኔን ሊያገለግል የሚፈልግ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል።  የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል።” (ዮሐንስ 12:26) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ወሮታ ነው! አብ የሚያከብራቸው ሰዎች በአምላክ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር አብረው ይገዛሉ።

ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከፍተኛ ሥቃይና አሠቃቂ ሞት በማሰብ እንዲህ አለ፦ “አሁን ተጨንቄአለሁ፤ እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።” ኢየሱስ ይህን ሲል የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንደማይፈልግ መግለጹ አይደለም። “የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 12:27) ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ መሞትን ጨምሮ የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም ተስማምቷል።