በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 87

አርቆ በማሰብ ዕቅድ ማውጣት

አርቆ በማሰብ ዕቅድ ማውጣት

ሉቃስ 16:1-13

  • የዓመፀኛው መጋቢ ምሳሌ

  • በሀብታችሁ “ወዳጆች አፍሩ”

ኢየሱስ ስለ ጠፋው ልጅ የተናገረው ምሳሌ፣ በቦታው ያሉት ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ጸሐፍትና ፈሪሳውያን አምላክ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን እንዲገነዘቡ ሊያደርጋቸው ይገባል። (ሉቃስ 15:1-7, 11) ኢየሱስ አሁን ደግሞ ትኩረቱን ወደ ደቀ መዛሙርቱ አደረገ። አንድ ሀብታም ሰው፣ የቤት አስተዳዳሪው ወይም መጋቢው ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ አለመሆኑን እንደሰማ የሚገልጽ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው።

መጋቢው የጌታውን ንብረት እያባከነ እንዳለ የሚገልጽ ክስ ለጌታው እንደደረሰው ኢየሱስ ተናገረ። በመሆኑም ጌታው መጋቢውን ጠርቶ ሊያባርረው መሆኑን ነገረው። በዚህ ጊዜ መጋቢው በልቡ እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ የመጋቢነት ኃላፊነቴን ሊወስድብኝ ነው፤ ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል? እንዳልቆፍር አቅም የለኝም፤ እንዳልለምን ያሳፍረኛል።” ወደፊት የሚያጋጥመውን ነገር መወጣት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ካሰበ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ቆይ፣ ምን እንደማደርግ አውቃለሁ! ከመጋቢነት ኃላፊነቴ ስነሳ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ አንድ ነገር አደርጋለሁ።” ከዚያም ከጌታው የተበደሩትን ሰዎች ወዲያውኑ በመጥራት እያንዳንዳቸውን “ከጌታዬ የተበደርከው ምን ያህል ነው?” በማለት ጠየቃቸው።—ሉቃስ 16:3-5

የመጀመሪያው “አንድ መቶ የባዶስ መስፈሪያ የወይራ ዘይት” ሲል መለሰለት። ይህም 2,200 ሊትር ዘይት ማለት ነው። ተበዳሪው ሰፊ የወይራ ዛፍ እርሻ ሊኖረው አሊያም የዘይት ነጋዴ ሊሆን ይችላል። መጋቢው “የውል ሰነድህ ይኸውልህ፤ ቁጭ በልና ቶሎ ብለህ 50 [1,100 ሊትር] ብለህ ጻፍ” አለው።—ሉቃስ 16:6

መጋቢው ሌላውን ተበዳሪ ደግሞ “አንተስ፣ የተበደርከው ምን ያህል ነው?” ብሎ ጠየቀው። እሱም “አንድ መቶ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ” አለው። ይህም 17,000 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። መጋቢው፣ ተበዳሪውን “የውል ሰነድህ ይኸውልህ፤ 80 ብለህ ጻፍ” አለው። በዚህ መንገድ ዕዳውን በ20 በመቶ ቀነሰለት።—ሉቃስ 16:7

መጋቢው አሁንም ቢሆን በጌታው ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ኃላፊ በመሆኑ ከጌታው የተበደሩትን ሰዎች ዕዳ መቀነስ ችሏል። ይህ መጋቢ የተበዳሪዎቹን ዕዳ በመቀነስ፣ ከሥራው በሚባረርበት ጊዜ ውለታ ሊመልሱለት ከሚችሉት ሰዎች ጋር እየተወዳጀ ነው።

ውሎ አድሮ ጌታው፣ መጋቢው ያደረገውን ነገር ሰማ። የመጋቢው ድርጊት በጌታው ላይ ኪሳራ እንደሚያስከትልበት የታወቀ ነው፤ ሆኖም “መጋቢው ዓመፀኛ ቢሆንም እንኳ አርቆ በማሰብ ባደረገው ነገር” ጌታው አደነቀው። ኢየሱስ አክሎም “የዚህ ሥርዓት ልጆች በእነሱ ትውልድ ካሉት ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ከብርሃን ልጆች ይበልጥ ብልሆች ናቸው” አለ።—ሉቃስ 16:8

ኢየሱስ መጋቢው የተጠቀመበትን ዘዴ እየደገፈ ወይም ማጭበርበርን እያበረታታ አይደለም። ታዲያ ማስተማር የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱን “በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤ እነሱም የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል” በማለት አሳሰባቸው። (ሉቃስ 16:9) በእርግጥም አርቆ አሳቢና ብልህ መሆንን በተመለከተ ከዚህ ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ‘የብርሃን ልጆች’ የተባሉት የአምላክ አገልጋዮች ቁሳዊ ንብረታቸውን በጥበብ መጠቀማቸው ወደፊት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።

 አንድ ሰው በሰማይ ያለውን መንግሥትም ሆነ በዚህ መንግሥት አስተዳደር ሥር በምድር ላይ የሚኖረውን ገነት እንዲወርስ ማድረግ የሚችሉት ይሖዋ አምላክ እና ልጁ ብቻ ናቸው። በመሆኑም ያለንን ቁሳዊ ንብረት ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ በመጠቀም ከይሖዋና ከልጁ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ካደረግን ወርቅ፣ ብርና ሌሎች ቁሳዊ ነገሮች በሚያልቁበት ወይም በሚጠፉበት ጊዜ የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተረጋገጠ ይሆናል።

በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ካላቸው ሀብትም ሆነ ቁሳዊ ነገር ጋር በተያያዘ ታማኝ የሆኑ ሰዎች የላቀ ዋጋ ባላቸው ነገሮችም የታመኑ እንደሚሆኑ ገልጿል። ኢየሱስ “ስለዚህ በዓመፅ ሀብት ታማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ እውነተኛውን ሀብት [ለምሳሌ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን] ማን በአደራ ይሰጣችኋል?” ብሏል።—ሉቃስ 16:11

ደቀ መዛሙርቱም “በዘላለማዊ መኖሪያ” የሚቀበላቸው ለማግኘት ከፈለጉ ተመሳሳይ ነገር እንደሚጠበቅባቸው ኢየሱስ መግለጹ ነው። አንድ ሰው፣ በአንድ በኩል የአምላክ እውነተኛ አገልጋይ በሌላ በኩል ደግሞ የዓመፃ ሀብት ባሪያ መሆን አይችልም። ኢየሱስ ሐሳቡን ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ መሆን የሚችል አገልጋይ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድ ጊዜ ባሪያ መሆን አትችሉም።”—ሉቃስ 16:9, 13