በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 59

የሰው ልጅ ማን ነው?

የሰው ልጅ ማን ነው?

ማቴዎስ 16:13-27 ማርቆስ 8:22-38 ሉቃስ 9:18-26

  • ኢየሱስ አንድ ዓይነ ስውር ፈወሰ

  • የመንግሥቱ ቁልፎች ለጴጥሮስ ይሰጡታል

  • ኢየሱስ እንደሚሞትና እንደሚነሳ ተናገረ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቤተሳይዳ ደረሱ። በዚያም ሰዎች አንድ ዓይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው ዳስሶ እንዲፈውሰው ተማጸኑት።

ኢየሱስ የዓይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከመንደሩ ውጭ ወሰደው። ከዚያም በሰውየው ዓይኖች ላይ እንትፍ ካለ በኋላ “የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም “ሰዎች ይታዩኛል፤ ሆኖም የሚራመዱ ዛፎች ይመስላሉ” አለ። (ማርቆስ 8:23, 24) ኢየሱስ እጆቹን ሰውየው ዓይኖች ላይ በመጫን ዓይኑ እንዲበራ አደረገ። ከዚያም አጥርቶ ማየት የቻለውን ይህን ሰው ወደ መንደሩ እንዳይገባ በማዘዝ ወደ ቤቱ ሰደደው።

ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ወደ ቂሳርያ ፊልጵስዩስ ክልል ሄዱ። የተጓዙት 40 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሸፍን አቀበት መንገድ ነው። የሄዱበት መንደር የሚገኘው ከባሕር ጠለል በላይ 350 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፤ አናቱ በአመዳይ የተሸፈነው የሄርሞን ተራራ በስተ ሰሜን ምሥራቅ ይታያል። ጉዞው ጥቂት ቀናት ሳይወስድ አይቀርም።

በመንገድ ላይ ሳሉ ኢየሱስ ለመጸለይ ብቻውን ሄደ። ኢየሱስ ከዘጠኝ ወይም ከአሥር ወር ገደማ በኋላ ይገደላል፤ ስለዚህ የደቀ መዛሙርቱ ነገር አሳስቦታል። በቅርቡ ብዙዎች እሱን መከተል አቁመዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ግራ የተጋቡና የጠበቁት ነገር ባለመፈጸሙ ቅር የተሰኙ ይመስላል። ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ ቢያስቡም ፈቃደኛ ያልሆነው ወይም ማንነቱን ፈጽሞ በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጥ ምልክት ያላሳየው ለምን እንደሆነ ግር ብሏቸው ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ፤ እሱም “ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይሉታል?” ሲል ጠየቃቸው። “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው መለሱለት። በእርግጥም ሕዝቡ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ትንሣኤ እንዳገኘና ኢየሱስ ተብሎ እንደተጠራ ያስባሉ። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን አመለካከት ለማወቅ ሲል “እናንተስ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም ወዲያውኑ “አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት።—ማቴዎስ 16:13-16

አምላክ ይህን ስለገለጠለት ጴጥሮስ ሊደሰት እንደሚገባ ኢየሱስ ከተናገረ በኋላ እንዲህ አለው፦ “እልሃለሁ፦ አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህች ዓለት ላይ ጉባኤዬን እገነባለሁ፤ የመቃብር በሮችም አያሸንፏትም።” ኢየሱስ፣ እሱ ራሱ ጉባኤ እንደሚገነባና የዚህ ጉባኤ አባላት ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት እስካጠናቀቁ ድረስ መቃብርም እንኳ ይዞ ሊያስቀራቸው እንደማይችል መግለጹ ነው። ከዚያም ለጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፎች እሰጥሃለሁ” በማለት ቃል ገባለት።—ማቴዎስ 16:18, 19

ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከሐዋርያት መካከል ዋነኛ ቦታ አልሰጠውም፤ ወይም እሱን የጉባኤው መሠረት አላደረገውም። ጉባኤው የሚመሠረትበት ዓለት ኢየሱስ ራሱ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:11፤ ኤፌሶን 2:20) ሆኖም ጴጥሮስ ሦስት ቁልፎች ይሰጡታል። ይህም ሲባል የተለያዩ ቡድኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ የመክፈት መብት ያገኛል ማለት ነው።

 ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ቁልፍ የሚጠቀመው በ33 ዓ.ም. ይኸውም ንስሐ የገቡ አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲገልጽላቸው ነው። ሁለተኛውን የሚጠቀመው ደግሞ አማኝ የሆኑ ሳምራውያን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመክፈት ነው። ከዚያም በ36 ዓ.ም. ሦስተኛውን ቁልፍ፣ ላልተገረዙ አሕዛብ ማለትም ለቆርኔሌዎስና ለሌሎች ይህንኑ አጋጣሚ ለመክፈት ይጠቀምበታል።—የሐዋርያት ሥራ 2:37, 38፤ 8:14-17፤ 10:44-48

ኢየሱስ ንግግሩን በመቀጠል፣ በቅርቡ በኢየሩሳሌም መከራ እንደሚቀበልና እንደሚሞት ሲነግራቸው ሐዋርያቱ አዘኑ። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ባለመረዳቱ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ጀርባውን በመስጠት ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” አለው።—ማቴዎስ 16:22, 23

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ በተጨማሪ ሌሎችንም ወደ ራሱ ጠራና የእሱ ተከታይ መሆን ቀላል እንዳልሆነ ገለጸላቸው። እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ። ሕይወቱን ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታልና፤ ለእኔና ለምሥራቹ ሲል ሕይወቱን የሚያጣ ሁሉ ግን ያድናታል።”—ማርቆስ 8:34, 35

በእርግጥም፣ የኢየሱስ ተከታዮች የእሱን ሞገስ ለማግኘት ከፈለጉ ደፋሮችና የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ መሆን አለባቸው። ኢየሱስ “በዚህ አመንዝራና ኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ሲመጣ ያፍርበታል” ብሏል። (ማርቆስ 8:38) አዎን፣ ኢየሱስ በዚያ ጊዜ ሲመጣ “ለእያንዳንዱ እንደ ምግባሩ ይከፍለዋል።”—ማቴዎስ 16:27