በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 137

ከጴንጤቆስጤ በፊት በርካቶች አዩት

ከጴንጤቆስጤ በፊት በርካቶች አዩት

ማቴዎስ 28:16-20 ሉቃስ 24:50-52 የሐዋርያት ሥራ 1:1-12፤ 2:1-4

  • ኢየሱስ ለብዙዎች ተገለጠ

  • ወደ ሰማይ አረገ

  • ኢየሱስ በ120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ አፈሰሰ

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከ11 ሐዋርያቱ ጋር ገሊላ ውስጥ ባለ አንድ ተራራ ላይ እንዲገናኙ ዝግጅት አደረገ። ቁጥራቸው 500 የሚሆን ሌሎች ደቀ መዛሙርትም በቦታው ተገኝተዋል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ነበራቸው። (ማቴዎስ 28:17፤ 1 ቆሮንቶስ 15:6) ሆኖም ኢየሱስ አሁን የተናገረው ነገር በእርግጥ ሕያው መሆኑን ሁሉም እንዲያምኑ ረድቷቸዋል።

ኢየሱስ፣ በሰማይና በምድር ሁሉ አምላክ ሥልጣን እንደሰጠው ተናገረ። “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” አላቸው። (ማቴዎስ 28:18-20) በእርግጥም ኢየሱስ ሕያው ነው፤ ከዚህም ሌላ ምሥራቹ እንዲሰበክ አሁንም ይፈልጋል።

ወንድ፣ ሴት ወይም ልጅ ሳይል ሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። ተቃዋሚዎች የስብከትና የማስተማር ሥራቸውን ለማስቆም ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” በማለት አጽናንቷቸዋል። ይህ ለተከታዮቹ ምን ትርጉም አለው? “እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” አላቸው። ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የሚካፈሉ ሁሉ ተአምራት የመፈጸም ችሎታ እንደሚሰጣቸው አልገለጸም። ያም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ አይለያቸውም።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ፣ በጠቅላላ “ለ40 ቀናት” ተገልጧል። የተለያየ አካል እየለበሰ የታየ ሲሆን “ሕያው መሆኑን በብዙ አሳማኝ ማስረጃዎች አሳያቸው።” እንዲሁም “ስለ አምላክ መንግሥት” አስተማራቸው።—የሐዋርያት ሥራ 1:3፤ 1 ቆሮንቶስ 15:7

ሐዋርያቱ በገሊላ እያሉ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አዘዛቸው። ከዚያም በከተማዋ ውስጥ ባገኛቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ከዚህ ይልቅ አብ ቃል የገባውንና እኔም ስለዚሁ ጉዳይ ስናገር የሰማችሁትን ቃል ፍጻሜ ተጠባበቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:4, 5

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር እንደገና ተገናኘ። ከዚያም በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ አቀበት ላይ እስከምትገኘው “እስከ ቢታንያ ይዟቸው ሄደ።” (ሉቃስ 24:50) ኢየሱስ ተለይቷቸው እንደሚሄድ ብዙ ጊዜ የነገራቸው ቢሆንም እንኳ መንግሥቱ በሆነ መንገድ ምድር ላይ እንደሚቋቋም እየጠበቁ ነው።—ሉቃስ 22:16, 18, 30፤ ዮሐንስ 14:2, 3

ሐዋርያት “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። እሱም “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው አብ ብቻ ስለሆነ እናንተ ይህን ማወቅ አያስፈልጋችሁም” በማለት በአጭሩ መለሰላቸው። ከዚያም ሊሠሩት የሚገባውን ሥራ በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ እንዲህ አላቸው፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:6-8

ሐዋርያቱ ከሞት ከተነሳው ከኢየሱስ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እያሉ እሱ ወደ ሰማይ መውጣት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ደመና ከዓይናቸው ሰወረው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሥጋዊ አካል ለብሶ ታይቷል። አሁን ግን በዚህ ወቅት የለበሰውን ሥጋዊ አካል በመተው መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ወደ ሰማይ አረገ። (1 ቆሮንቶስ 15:44, 50፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ታማኝ ሐዋርያቱ ትኩር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ “ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ።” ሥጋዊ አካል የለበሱት እነዚህ መላእክት ሐዋርያቱን እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የተወሰደው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመጣል።”—የሐዋርያት ሥራ 1:10, 11

ኢየሱስ ምድርን ለቆ የሄደው በሕዝብ ሆታ አይደለም፤ ሲሄድ ያዩት ታማኝ ተከታዮቹ ብቻ ናቸው። የሚመለሰውም “በዚሁ ሁኔታ” ነው፤ በሌላ አባባል ከፍተኛ ሕዝባዊ  አቀባበል አይደረግለትም፤ ከዚህ ይልቅ በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ መገኘቱን የሚያስተውሉት ታማኝ ተከታዮቹ ብቻ ናቸው።

ከዚህ በኋላ ሐዋርያቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በቀጣዮቹ ቀናት “ከኢየሱስ እናት ከማርያም እንዲሁም ከወንድሞቹ” እና ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ተሰባሰቡ። (የሐዋርያት ሥራ 1:14) እነዚህ ሰዎች ተግተው እየጸለዩ ነው። በጸሎት ታግዘው ካሰቡባቸው ጉዳዮች አንዱ የሐዋርያቱ ቁጥር እንደገና 12 እንዲሆን የአስቆሮቱ ይሁዳን የሚተካውን ደቀ መዝሙር መምረጥ ነው። (ማቴዎስ 19:28) ይህ ሰው የኢየሱስን ሥራዎች እና ትንሣኤውን የተመለከተ መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ የአምላክን ፈቃድ ለማወቅ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣ ስለ መጣል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ላይ ነው። (መዝሙር 109:8፤ ምሳሌ 16:33) ማትያስ ተመረጠና “ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ”፤ ማትያስ፣ ኢየሱስ ከላካቸው 70 ደቀ መዛሙርት አንዱ ሳይሆን አይቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 1:26

በ33 ዓ.ም. የተከበረው ጴንጤቆስጤ የተባለው የአይሁድ በዓል የዋለው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ ነው። በኢየሩሳሌም በሚገኝ ሰገነት ላይ 120 ገደማ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበዋል። በድንገት ኃይለኛ ነፋስ የመሰለ ድምፅ ቤቱን ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ አረፉ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። ኢየሱስ ቃል በገባላቸው መሠረት በዚህ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው!—ዮሐንስ 14:26