በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 19

አንዲት ሳምራዊት አስተማረ

አንዲት ሳምራዊት አስተማረ

ዮሐንስ 4:3-43

  • ኢየሱስ አንዲት ሳምራዊትንና ሌሎችን አስተማረ

  • አምላክ የሚቀበለው አምልኮ

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከይሁዳ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ወደ ገሊላ ሲመለሱ በሰማርያ አውራጃ በኩል አለፉ። ጉዞው ስላደከማቸው እኩለ ቀን ገደማ ሲካር በምትባል ከተማ አቅራቢያ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፉ። ይህ ጉድጓድ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ያዕቆብ የቆፈረው አሊያም ገንዘብ ከፍሎ ያስቆፈረው ሊሆን ይችላል። በዘመናችን ናብለስ ተብላ በምትጠራው ከተማ አቅራቢያ አሁንም የውኃ ጉድጓድ አለ።

ኢየሱስ በጉድጓዱ አጠገብ አረፍ ሲል ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት በአቅራቢያው ወደምትገኝ ከተማ ሄዱ። እነሱ ሄደው እያለ አንዲት ሳምራዊት ውኃ ለመቅዳት መጣች። ኢየሱስ “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” ብሎ ጠየቃት።—ዮሐንስ 4:7

አይሁዳውያንና ሳምራውያን በመካከላቸው ባለው ሥር የሰደደ ጥላቻ ምክንያት በአብዛኛው ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። በመሆኑም ሴትየዋ በመገረም “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “የአምላክን ነፃ ስጦታ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም የሕይወት ውኃ ይሰጥሽ ነበር።” እሷም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ውኃ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጉድጓዱ ደግሞ ጥልቅ ነው። ታዲያ ይህን የሕይወት ውኃ ከየት ታገኛለህ? አንተ ይህን የውኃ ጉድጓድ ከሰጠን እንዲሁም ከልጆቹና ከከብቶቹ ጋር ከዚህ ጉድጓድ ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህ?”—ዮሐንስ 4:9-12

ኢየሱስም “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል” አላት። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” (ዮሐንስ 4:13, 14) ኢየሱስ ቢደክመውም እንኳ ሕይወት የሚያስገኘውን የእውነት ቃል ለሳምራዊቷ ከመናገር ወደኋላ አላለም።

ሴትየዋም መልሳ “ጌታዬ፣ እንዳልጠማም ሆነ ውኃ ለመቅዳት ወደዚህ ቦታ እንዳልመላለስ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመልሰሽ ነይ” አላት። እሷም “ባል የለኝም” ብላ መለሰችለት። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ሲመልስላት ሴትየዋ ስለ እሷ በሚያውቀው ነገር በጣም ተገርማ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፦ “‘ባል የለኝም’ ማለትሽ ትክክል ነው። ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብሮሽ ያለው ሰው ደግሞ ባልሽ አይደለም። ስለዚህ የተናገርሽው እውነት ነው።”—ዮሐንስ 4:15-18

ሴትየዋ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ስለ እሱ ምን እንደሚጠቁም ስለገባት በመገረም “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አሁን ተረዳሁ” አለችው። ከዚያም ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዳላት የሚያሳይ ነገር ተናገረች። እንዴት? “አባቶቻችን [ሳምራውያን] በዚህ ተራራ [በአቅራቢያው ባለው የገሪዛን ተራራ] ላይ አምልኳቸውን ያካሂዱ ነበር፤ እናንተ አይሁዳውያን ግን ሰዎች ማምለክ ያለባቸው በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለች።—ዮሐንስ 4:19, 20

ኢየሱስ ግን ትልቅ ቦታ ያለው ነገር የአምልኮ ስፍራው እንዳልሆነ ገለጸላት። “በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት ይመጣል” አለ። አክሎም እንዲህ አላት፦ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው።”—ዮሐንስ 4:21, 23, 24

አብ ትኩረት የሚያደርገው እውነተኛ አምላኪዎቹ እሱን በሚያመልኩበት ቦታ ላይ ሳይሆን በሚያመልኩበት መንገድ  ላይ ነው። ሴትየዋ ይህን ስትሰማ ተደነቀች። “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ። እሱ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ አድርጎ ይነግረናል” አለችው።—ዮሐንስ 4:25

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ፣ እሱ ነኝ” በማለት አንድ ትልቅ እውነት ገለጸላት። (ዮሐንስ 4:26) እስቲ አስበው! እኩለ ቀን ላይ ውኃ ለመቅዳት ለመጣችው ለዚህች ሴት ኢየሱስ ልዩ ነገር አድርጎላታል። ለሌላ ለማንም በግልጽ ያልተናገረውን ነገር ይኸውም መሲሕ መሆኑን ለእሷ በቀጥታ ነግሯታል።

ብዙ ሳምራውያን አመኑ

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምግብ ይዘው ከሲካር ሲመለሱ ኢየሱስን እነሱ ሲሄዱ ተቀምጦበት በነበረው በዚያው በያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አገኙት። በዚህ ወቅት ግን ከአንዲት ሳምራዊት ጋር እየተነጋገረ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ሲመጡ ሴትየዋ እንስራዋን እዚያው ትታ ወደ ከተማ ሄደች።

ሴትየዋ ሲካር ስትደርስ፣ ኢየሱስ የነገራትን ነገር ለከተማይቱ ሰዎች አወራችላቸው። “ያደረግኩትን ሁሉ የነገረኝን ሰው መጥታችሁ እዩ” በማለት በልበ ሙሉነት ተናገረች። ከዚያም “ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለቻቸው፤ እንዲህ ያለችው የማወቅ ጉጉታቸውን ለማነሳሳት ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ 4:29) ሴትየዋ ያነሳችው ጥያቄ ከሙሴ ዘመን አንስቶ የሰዎችን ትኩረት የሳበ ትልቅ ጉዳይ ነው። (ዘዳግም 18:18) ጥያቄው የከተማዋ ሰዎች፣ ኢየሱስን ራሳቸው መጥተው እንዲያዩ አነሳስቷቸዋል።

በዚህ መሃል፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያመጡትን ምግብ እንዲበላ ጎተጎቱት። እሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ተገርመው “ምግብ ያመጣለት ይኖር ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። ኢየሱስም “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” በማለት በደግነት መለሰላቸው፤ ይህ ሐሳብ ለሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች ልዩ ትርጉም ያዘለ ነው።—ዮሐንስ 4:32-34

ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው፣ ከአራት ወራት በኋላ የሚጀምረውን የመከር ሥራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ቀጥሎ እንደገለጸው ስለ መንፈሳዊው መከር መናገሩ ነው፦ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ። አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለና  ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል።”—ዮሐንስ 4:35, 36

ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ጋር መገናኘቱ ምን ውጤት እንደሚያስገኝ ከወዲሁ አስተውሎ ይሆናል። በርካታ የሲካር ነዋሪዎች፣ ሴትየዋ “ያደረግኩትን ሁሉ ነገረኝ” በማለት የሰጠችውን ምሥክርነት ሰምተው በእሱ አመኑ። (ዮሐንስ 4:39) በመሆኑም ከሲካር ወጥተው ኢየሱስ ወዳለበት የውኃ ጉድጓድ በመምጣት ከእነሱ ጋር እንዲቆይና ተጨማሪ ነገር እንዲነግራቸው ለመኑት። ኢየሱስም ግብዣውን ተቀብሎ በሰማርያ ሁለት ቀን ቆየ።

የሰማርያ ሰዎች የኢየሱስን ቃል ሲሰሙ ሌሎች ብዙዎች በእሱ አመኑ። ከዚያም ሴትየዋን እንዲህ አሏት፦ “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለነገርሽን ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ራሳችን ሰምተናል፤ እንዲሁም ይህ ሰው በእርግጥ የዓለም አዳኝ እንደሆነ አውቀናል።” (ዮሐንስ 4:42) ሳምራዊቷ ሴት፣ ሰዎች ተጨማሪ ነገር ለማወቅ እንዲነሳሱ ጉጉታቸውን በመቀስቀስ ስለ ክርስቶስ እንዴት መመሥከር እንደምንችል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ትታልናለች!

መከር (የገብስ አጨዳ ሳይሆን አይቀርም) ሊደርስ አራት ወራት እንደቀሩት አስታውስ፤ በዚህ አካባቢ ገብስ የሚታጨደው በጸደይ ወራት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ጋር የተወያየው ኅዳር ወይም ታኅሣሥ ላይ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ30 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል በኋላ በይሁዳ እያስተማሩና እያጠመቁ ስምንት ወር ገደማ አሳልፈዋል ማለት ነው። አሁን፣ መኖሪያቸው ወደሚገኝበት ወደ ገሊላ እየተመለሱ ነው። እዚያ ምን ያጋጥማቸው ይሆን?