በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 54

ኢየሱስ—“ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ”

ኢየሱስ—“ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ”

ዮሐንስ 6:25-48

  • ኢየሱስ ‘ከሰማይ የወረደው ምግብ’ ነው

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ በኋላ ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ እንዳሰቡ ሲያውቅ ትቷቸው ሄዷል። በዚያው ዕለት ሌሊት፣ በነፋስ በሚናወጥ ባሕር ላይ ተራመደ፤ ጴጥሮስም በውኃው ላይ መራመድ ከጀመረ በኋላ እምነቱ በመዳከሙ መስጠም ሲጀምር ኢየሱስ አድኖታል። እንዲሁም ነፋሱን ጸጥ አሰኝቷል፤ ምናልባትም ይህን ማድረጉ ደቀ መዛሙርቱ እንዳይሰጥሙ ረድቷቸዋል።

አሁን ኢየሱስ የሚገኘው በባሕሩ በስተ ምዕራብ ይኸውም ቅፍርናሆም አካባቢ ነው። በተአምራዊ መንገድ የመገባቸው ሰዎች አገኙትና “መቼ ወደዚህ መጣህ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ግን እነዚህ ሰዎች ወደ እሱ የመጡት በድጋሚ እንዲመግባቸው ፈልገው እንደሆነ በመግለጽ ወቀሳቸው። ከዚያም “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ” በማለት አሳሰባቸው። እነሱም “ታዲያ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ሥራ ለመሥራት ምን ብናደርግ ይሻላል?” ብለው ጠየቁት።—ዮሐንስ 6:25-28

ይህን ሲሉ በሕጉ ውስጥ የተጠቀሱትን ሥራዎች በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል፤ ኢየሱስ ግን ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ እንዳለ ሲገልጽ “አምላክ የሚቀበለው ሥራማ እሱ በላከው ሰው ማመን ነው” አላቸው። ኢየሱስ ብዙ ነገሮች ቢያደርግም ሕዝቡ በእሱ ላይ እምነት አላሳደሩም። በእሱ እንዲያምኑ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። እንዲሁም ‘ምን ነገር ትሠራለህ?’ አሉት። አክለውም “‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ ምግብ ሰጣቸው’ ተብሎ በተጻፈው መሠረት አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ” አሉት።—ዮሐንስ 6:29-31፤ መዝሙር 78:24

ኢየሱስ ምልክት እንዲሰጣቸው ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሲል የተአምራዊ ምግብ ምንጭ ማን እንደሆነ ገለጸ፤ እንዲህ አላቸው፦ “እላችኋለሁ፣ ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ግን እውነተኛውን ምግብ ከሰማይ ይሰጣችኋል። ምክንያቱም አምላክ የሚሰጠው ምግብ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወት የሚያስገኝ ነው።” እነሱም ነጥቡ ስላልገባቸው “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምግብ ሁልጊዜ ስጠን” ብለው ለመኑት። (ዮሐንስ 6:32-34) ለመሆኑ ኢየሱስ የጠቀሰው “ምግብ” ምንድን ነው?

ኢየሱስ እንዲህ በማለት አብራራ፦ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ፈጽሞ አይራብም፤ እንዲሁም በእኔ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም። ነገር ግን ‘አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም’ ብያችሁ ነበር። . . . ከሰማይ የመጣሁት የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነውና። የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንዱም እንኳ እንዳይጠፋብኝና በመጨረሻው ቀን ሁሉንም ከሞት እንዳስነሳቸው ነው። ምክንያቱም የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።”—ዮሐንስ 6:35-40

አይሁዳውያን ይህን ሲሰሙ ስለተናደዱ በእሱ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። “ከሰማይ የወረደው ምግብ እኔ ነኝ” ብሎ እንዴት ይናገራል? (ዮሐንስ 6:41) እነሱ እስከሚያውቁት ድረስ ወላጆቹ ሰዎች ሲሆኑ ያደገውም በገሊላ በምትገኘው በናዝሬት ከተማ ነው። ሰዎቹ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለም? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለም እንዴ?” በማለት ጠየቁ።—ዮሐንስ 6:42

ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ። የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ። ነቢያት በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ‘ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ከአምላክ ዘንድ ከመጣው በስተቀር አብን ያየ አንድም ሰው የለም፤ እሱ አብን አይቶታል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።”—ዮሐንስ 6:43-47፤ ኢሳይያስ 54:13

ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ከኒቆዲሞስ ጋር ሲወያይ የዘላለም ሕይወትን በሰው ልጅ ከማመን ጋር በማያያዝ በአምላክ አንድያ ‘ልጅ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረው እንጂ እንደማይጠፋ’ ገልጾ ነበር። (ዮሐንስ 3:15, 16) አሁን ለተሰበሰበው ሕዝብ፣ የዘላለም ሕይወት ማግኘታቸው እሱ በሚጫወተው ሚና ላይ የተመካ መሆኑን ተናገረ፤ መናም ሆነ በገሊላ የሚገኝ ማንኛውም ምግብ ይህን  መብት ሊያስገኝ አይችልም። ታዲያ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ” በማለት በድጋሚ ተናገረ።—ዮሐንስ 6:48

ከሰማይ የወረደውን ምግብ በተመለከተ የተካሄደው ውይይት ቀጠለ፤ ውይይቱ የተቋጨው ኢየሱስ ቅፍርናሆም ውስጥ በሚገኝ አንድ ምኩራብ ባስተማረበት ጊዜ ነው።