በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 3

መንገድ የሚያዘጋጅ ሰው ተወለደ

መንገድ የሚያዘጋጅ ሰው ተወለደ

ሉቃስ 1:57-79

  • መጥምቁ ዮሐንስ ተወለደ፤ እንዲሁም ስም ወጣለት

  • ዮሐንስ ወደፊት ምን እንደሚያከናውን ዘካርያስ ተናገረ

ኤልሳቤጥ የምትወልድበት ጊዜ ደርሷል። ዘመዷ የሆነችው ማርያም ላለፉት ሦስት ወራት እሷ ጋ ቆይታለች። አሁን ግን ማርያም፣ ኤልሳቤጥን ተሰናብታ በስተ ሰሜን በናዝሬት ወደሚገኘው መኖሪያዋ ለመመለስ ረጅሙን ጉዞ የምትያያዝበት ጊዜ ደርሷል። ከስድስት ወር ገደማ በኋላ እሷም ወንድ ልጅ ትወልዳለች።

ማርያም ከሄደች ብዙም ሳይቆይ ኤልሳቤጥ ወለደች። ኤልሳቤጥ በሰላም መገላገሏና እሷም ሆነች ሕፃኑ በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ምንኛ የሚያስደስት ነው! የኤልሳቤጥ ጎረቤቶችና ዘመዶች ሕፃኑን ሲያዩ ተደሰቱ።

አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ መሠረት ወንድ ልጅ በተወለደ በስምንተኛው ቀን መገረዝ ነበረበት፤ ስም የሚወጣለትም በዚህ ጊዜ ነው። (ዘሌዋውያን 12:2, 3) አንዳንዶች፣ ልጁ ልክ እንደ አባቱ ዘካርያስ ተብሎ እንዲጠራ ሐሳብ አቀረቡ። ሆኖም ኤልሳቤጥ “አይሆንም! ዮሐንስ ይባል” አለች። (ሉቃስ 1:60) መልአኩ ገብርኤል፣ ልጁ ዮሐንስ መባል እንዳለበት መናገሩን አስታውስ።

ጎረቤቶቻቸውና ዘመዶቻቸው ግን “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” ሲሉ ተቃወሙ። (ሉቃስ 1:61) ከዚያም ዘካርያስን ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስ የእንጨት ጽላት እንዲሰጡት ጠየቀና “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ።—ሉቃስ 1:63

በዚህ ጊዜ የዘካርያስ የመናገር ችሎታ በተአምራዊ መንገድ ተመለሰለት። ዘካርያስ የመናገር ችሎታውን ያጣው፣ ኤልሳቤጥ ልጅ እንደምትወልድ መልአኩ ሲነግረው ባለማመኑ ምክንያት እንደሆነ ታስታውስ ይሆናል። በመሆኑም ዘካርያስ መናገር ሲጀምር ጎረቤቶቹ ሁሉ ተገርመው “የዚህ ሕፃን መጨረሻ ምን ይሆን?” አሉ። (ሉቃስ 1:66) ለዮሐንስ ስም ከወጣበት መንገድ ጋር በተያያዘ የአምላክ እጅ እንዳለበት ተገንዝበው ነበር።

ከዚያ በኋላ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ፊቱን ወደ ሕዝቡ ስለመለሰና ሕዝቡን ስላዳነ ውዳሴ ይድረሰው። ደግሞም በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድ አስነስቶልናል።” (ሉቃስ 1:68, 69) “የመዳን ቀንድ” ሲል በወቅቱ ገና ስላልተወለደው ስለ  ጌታ ኢየሱስ መናገሩ ነው። ዘካርያስ፣ በኢየሱስ አማካኝነት አምላክ ምን እንደሚያደርግ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከጠላቶቻችን እጅ ነፃ ካወጣን በኋላ ለእሱ ያለ ፍርሃት ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ይሰጠናል፤ ይህም ታማኝ እንድንሆንና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ጽድቅ የሆነውን ነገር እንድናደርግ ነው።”—ሉቃስ 1:74, 75

ዘካርያስ ልጁን በተመለከተ ደግሞ የሚከተለውን ትንቢት ተናገረ፦ “አንተ ሕፃን፣ መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በይሖዋ ፊት ስለምትሄድ የልዑሉ ነቢይ ትባላለህ፤ ለሕዝቡም ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸው መዳን እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን እውቀት ትሰጣቸዋለህ፤ ይህም የሆነው አምላካችን ከአንጀት ስለራራልን ነው። ከዚህ ርኅራኄም የተነሳ እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል፤ ይኸውም በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለተቀመጡት ብርሃን ለመስጠት እንዲሁም እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ለመምራት ነው።” (ሉቃስ 1:76-79) ይህ ትንቢት ምንኛ የሚያጽናና ነው!

ይህ በእንዲህ እያለ፣ ገና ያላገባችው ማርያም ናዝሬት ወደሚገኘው መኖሪያዋ ደረሰች። ማርገዟ ሲታወቅ ምን ይደርስባት ይሆን?