የዮሐንስ ወንጌል 7:1-52

  • ኢየሱስ በዳስ በዓል ላይ ተገኘ (1-13)

  • ኢየሱስ በበዓሉ ላይ አስተማረ (14-24)

  • ክርስቶስን በተመለከተ ሰዎች የነበራቸው የተለያየ አመለካከት (25-52)

7  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ መዘዋወሩን* ቀጠለ፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ሊገድሉት ይፈልጉ+ ስለነበር በይሁዳ ምድር መዘዋወር አልፈለገም።  ይሁን እንጂ የአይሁዳውያን በዓል የሆነው የዳስ በዓል+ ተቃርቦ ነበር።  ስለዚህ ወንድሞቹ+ እንዲህ አሉት፦ “ደቀ መዛሙርትህም የምታከናውነውን ሥራ ማየት እንዲችሉ ከዚህ ተነስተህ ወደ ይሁዳ ሂድ።  በይፋ እንዲታወቅ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ሰው የለምና። እነዚህን ነገሮች የምትሠራ ከሆነ ራስህን ለዓለም ግለጥ።”  ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር።+  ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤+ ለእናንተ ግን ማንኛውም ጊዜ ተስማሚ ነው።  ዓለም እናንተን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ እንደሆነ ስለምመሠክርበት ይጠላኛል።+  እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ገና ጊዜዬ ስላልደረሰ+ ወደ በዓሉ አልሄድም።”  ይህን ከነገራቸው በኋላ በገሊላ ቆየ። 10  ሆኖም ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደዚያው ሄደ። 11  በበዓሉም ላይ አይሁዳውያን “ያ ሰው የት አለ?” እያሉ ይፈልጉት ጀመር። 12  በሕዝቡም መካከል ስለ እሱ ብዙ ጉምጉምታ ነበር። አንዳንዶች “እሱ ጥሩ ሰው ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም። እሱ ሕዝቡን ያሳስታል” ይሉ ነበር።+ 13  እርግጥ አይሁዳውያንን* ይፈሩ ስለነበረ ስለ እሱ በግልጽ የሚናገር ሰው አልነበረም።+ 14  በበዓሉም አጋማሽ ላይ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ያስተምር ጀመር። 15  አይሁዳውያንም በጣም ተገርመው “ይህ ሰው ትምህርት ቤት* ገብቶ ሳይማር ቅዱሳን መጻሕፍትን* እንዴት እንዲህ ሊያውቅ ቻለ?” አሉ።+ 16  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው።+ 17  ማንም የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ይህ ትምህርት ከአምላክ የመጣ+ ይሁን ከራሴ ለይቶ ያውቃል። 18  ከራሱ አመንጭቶ የሚናገር ሁሉ ራሱ እንዲከበር ይፈልጋል፤ የላከው እንዲከበር+ የሚፈልግ ሁሉ ግን እሱ እውነተኛ ነው፤ በእሱም ዘንድ ዓመፅ የለም። 19  ሕጉን የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም?+ ሆኖም አንዳችሁም ሕጉን አትታዘዙም። እኔን ለመግደል የምትፈልጉት ለምንድን ነው?”+ 20  ሕዝቡም “አንተ ጋኔን አለብህ። ሊገድልህ የፈለገው ደግሞ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 21  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ነገር ስለሠራሁ ሁላችሁም ተደነቃችሁ። 22  እስቲ ይህን ልብ በሉ፦ ሙሴ የግርዘትን ሕግ ሰጣችሁ+ (ይህ ሕግ የተሰጠው ከአባቶች ነው+ እንጂ ከሙሴ አይደለም)፤ እናንተም በሰንበት ሰው ትገርዛላችሁ። 23  የሙሴ ሕግ እንዳይጣስ ሲባል በሰንበት ቀን ሰው የሚገረዝ ከሆነ እኔ በሰንበት አንድን ሰው መፈወሴ ይህን ያህል ሊያስቆጣችሁ ይገባል?+ 24  የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤* ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።”+ 25  በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፦ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለም እንዴ?+ 26  እሱ ግን ይኸው በአደባባይ እየተናገረ ነው፤ እነሱም ምንም አላሉትም። ገዢዎቹ ይህ ሰው በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ አስበው ይሆን? 27  ሆኖም እኛ ይህ ሰው ከየት እንደመጣ እናውቃለን፤+ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከየት እንደመጣ ማንም አያውቅም።” 28  ከዚያም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔ ማን እንደሆንኩም ሆነ ከየት እንደመጣሁ ታውቃላችሁ። የመጣሁትም በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤+ ሆኖም የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ እናንተም አታውቁትም።+ 29  እኔ ግን የእሱ ተወካይ ሆኜ የመጣሁ ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፤+ የላከኝም እሱ ነው።” 30  በመሆኑም ሊይዙት ፈለጉ፤+ ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።+ 31  ይሁንና ከሕዝቡ መካከል ብዙዎች በእሱ አምነው+ “ክርስቶስስ በሚመጣበት ጊዜ ይህ ሰው ካደረገው የበለጠ ብዙ ተአምራዊ ምልክት ያደርጋል እንዴ?” ይሉ ነበር። 32  ፈሪሳውያን ሕዝቡ በጉምጉምታ ስለ እሱ የሚያወራውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑም ይይዙት* ዘንድ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኩ። 33  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ።+ 34  እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወደምሄድበትም ልትመጡ አትችሉም።”+ 35  በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “ይህ ሰው ልናገኘው የማንችለው ወዴት ሊሄድ ቢያስብ ነው? በግሪካውያን መካከል ተበታትነው ወደሚገኙት አይሁዳውያን ሄዶ ግሪካውያንን ሊያስተምር አስቦ ይሆን እንዴ? 36  ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወደምሄድበትም ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?” 37  የበዓሉ+ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “የተጠማ ካለ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።+ 38  በእኔ የሚያምን ሁሉ ቅዱስ መጽሐፉ እንደሚለው ‘የሕያው ውኃ ጅረቶች ከውስጡ ይፈስሳሉ።’”+ 39  ይሁን እንጂ ይህን ሲል በእሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክብሩን ገና ስላልተጎናጸፈ+ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።+ 40  ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶች ይህን ቃል ሲሰሙ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” ይሉ ጀመር።+ 41  ሌሎችም “ይህ ክርስቶስ ነው”+ ይሉ ነበር። አንዳንዶች ግን እንዲህ አሉ፦ “ክርስቶስ የሚመጣው ከገሊላ ነው እንዴ?+ 42  ቅዱስ መጽሐፉ ክርስቶስ ከዳዊት ዘርና+ ዳዊት ከኖረበት መንደር+ ከቤተልሔም+ እንደሚመጣ ይናገር የለም?” 43  ስለዚህ እሱን በተመለከተ በሕዝቡ መካከል ክፍፍል ተፈጠረ። 44  ይሁንና አንዳንዶቹ ሊይዙት* ፈልገው ነበር፤ ሆኖም አንድም ሰው አልያዘውም። 45  ከዚያም የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ፈሪሳውያኑ ተመልሰው ሄዱ፤ እነሱም ጠባቂዎቹን “ለምን ይዛችሁት አልመጣችሁም?” አሏቸው። 46  ጠባቂዎቹም “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ብለው መለሱ።+ 47  ፈሪሳውያኑ ግን እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተም ተታለላችሁ? 48  ከገዢዎች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእሱ ያመነ አለ?+ 49  ሕጉን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።” 50  ቀደም ሲል ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረውና ከእነሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፦ 51  “ሕጋችን በመጀመሪያ ግለሰቡ የሚለውን ሳይሰማና ምን እያደረገ እንዳለ ሳያውቅ ይፈርድበታል?”+ 52  እነሱም “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህ? ከገሊላ አንድም ነቢይ እንደማይነሳ ቅዱሳን መጻሕፍትን መርምረህ ተረዳ” አሉት።*

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መመላለሱን።”
የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ጽሑፎችን።”
የረቢዎችን ትምህርት ቤት ያመለክታል።
ወይም “መፍረዳችሁን ተዉ።”
ወይም “ያስሩት።”
ወይም “ሊያስሩት።”
በእጅ የተጻፉ በርካታ ጥንታዊና ከፍተኛ ተአማኒነት ያላቸው ቅጂዎች ከዮሐ 7:53 እስከ 8:11 ድረስ ያለውን ሐሳብ አይጨምሩም።