በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ 139

ኢየሱስ ምድርን ገነት ያደርጋል፤ ተልእኮውንም ይፈጽማል

ኢየሱስ ምድርን ገነት ያደርጋል፤ ተልእኮውንም ይፈጽማል

1 ቆሮንቶስ 15:24-28

  • የበጎቹና የፍየሎቹ የመጨረሻ ዕጣ

  • ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ

  • ኢየሱስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ይሆናል

ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ፣ አገልግሎቱን እንኳ ከመጀመሩ በፊት ሊያሰናክለው ቆርጦ የተነሳ ጠላት አጋጥሞት ነበር። በእርግጥም ዲያብሎስ ኢየሱስን ለመፈተን ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ስለዚህ ክፉ አካል ሲናገር “የዚህ ዓለም ገዢ እየመጣ” እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም” ብሏል።—ዮሐንስ 14:30

ሐዋርያው ዮሐንስ “ታላቁ ዘንዶ ይኸውም . . . ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ” ምን እንደሚጠብቀው በራእይ ተመልክቷል። ዮሐንስ እንደገለጸው፣ አረመኔ የሆነው ይህ የሰው ዘር ጠላት ከሰማይ ተባሯል፤ እንዲሁም “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ . . . ወርዷል።” (ራእይ 12:9, 12) ክርስቲያኖች፣ “ጥቂት ጊዜ” እንደሚሆን በተገለጸው በዚህ ወቅት እንደሚኖሩ እንዲሁም ‘ታላቁ ዘንዶ ይኸውም የጥንቱ እባብ’ በቅርቡ ጥልቁ ውስጥ እንደሚወረወርና ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ላይ በሚገዛበት 1,000 ዓመት ውስጥ ይህ ዘንዶ ምንም እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችል ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አላቸው።—ራእይ 20:1, 2

በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ መኖሪያችን በሆነችው ምድር ላይ ምን ይከናወናል? በምድር ላይ እነማን ይኖራሉ? ምን ዓይነት ሁኔታስ ይሰፍናል? ኢየሱስ መልሱን ጠቁሞናል። ስለ በጎቹና ፍየሎቹ በተናገረው ምሳሌ ላይ በበግ የተመሰሉትና ከኢየሱስ ወንድሞች ጋር በመተባበር ለእነሱ መልካም የሚያደርጉት ጻድቅ የሆኑ የሰው ልጆች ምን እንደሚጠብቃቸው ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ በፍየሎች የተመሰሉትና ከበጎቹ ተቃራኒ የሆነ አካሄድ የሚከተሉት ሰዎች ዕጣቸው ምን እንደሚሆን በግልጽ ተናግሯል። ኢየሱስ “እነዚህ [ፍየሎቹ] ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን [በጎቹ] ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” ብሏል።—ማቴዎስ 25:46

ይህ ጥቅስ፣ ኢየሱስ ከጎኑ እንጨት ላይ ለተሰቀለው ወንጀለኛ የተናገረውን ሐሳብ ለመረዳት ያግዘናል። ኢየሱስ ለዚህ ሰው የገባው ቃል ለታማኝ ሐዋርያቱ ከሰጠው ተስፋ ይኸውም የመንግሥተ ሰማያት አባል ከመሆን የተለየ ነው። ኢየሱስ ንስሐ ለገባው ወንጀለኛ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሲል ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 23:43) በመሆኑም ይህ ሰው በገነት ይኸውም ውብ በሆነ  የአትክልት ስፍራ ውስጥ የመኖር ተስፋ ተዘርግቶለታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ እንደ በጎች የሆኑና “ወደ ዘላለም ሕይወት” የሚሄዱ ሰዎችም በዚያ ገነት ውስጥ እንደሚኖሩ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው።

ይህም ሐዋርያው ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በምድር ላይ እንደሚሰፍን ከተናገረው ሁኔታ ጋር ይስማማል። እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4

በእርግጥ ያ ወንጀለኛ በገነት ውስጥ እንዲኖር ከሞት መነሳት አለበት። ከሞት የሚነሳው ደግሞ እሱ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ይህን ግልጽ አድርጓል፦ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።”—ዮሐንስ 5:28, 29

ይሁንና ስለ ታማኝ ሐዋርያቱና በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ስለሚኖሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእሱም ጋር ለ1,000 ዓመት ይነግሣሉ” ይላል። (ራእይ 20:6) ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑት እነዚህ ወንዶችና ሴቶች የሚወሰዱት ከምድር ነው። በመሆኑም ከሰማይ ሆነው ሲገዙ በምድር ያሉትን ሰዎች ስሜት የሚረዱ ከመሆኑም ሌላ በርኅራኄ ይይዟቸዋል።—ራእይ 5:10

ኢየሱስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከእሱ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል፤ እንዲሁም ከወረሱት የኃጢአት እርግማን ነፃ ያወጣቸዋል። እሱና አብረውት የሚገዙት ነገሥታት ታማኝ የሆነው የሰው ዘር ወደ ፍጽምና እንዲደርስ ያደርጋሉ። ከዚያም አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሏት ባዘዛቸው ጊዜ በነበረው ዓላማ መሠረት የሰው ልጆች በደስታ ይኖራሉ። በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣው ሞት እንኳ ይወገዳል!

በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ይሖዋ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ይፈጽማል። በሺህ ዓመት ግዛቱ ፍጻሜ ላይ መንግሥቱንና ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለአባቱ ያስረክባል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ በዚያ ወቅት የሚያሳየውን አስደናቂ ትሕትና ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:28

ኢየሱስ የአምላክን አስደናቂ ዓላማዎች በመፈጸም ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ግልጽ ነው። የአምላክ ዓላማዎች ለዘላለም እየተገለጡ ሲሄዱ ኢየሱስ ምንጊዜም “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ይሆናል።—ዮሐንስ 14:6